ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት ያገለጉሉ መኪናዎች ከውጭ ሲገቡ ያደርግ የነበረውን የቀረጥ ስሌት ቅናሽ ከትላንት ጀምሮ አቆመ።
መንግስት ከዚህ ቀደም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ላለማበረታታት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።ከትላንት ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል በተባለ የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ መመሪያም ያገለገሉ መኪናዎች ሀገር ውስጥ ሲገቡ ለመኪናዎቹ ቀረጥ ሲከፈል ፣ ከተሽከርካሪዎቹ ዋና ዋጋ ላይ የአገልግሎት ዋጋ ተብሎ እስከ 30 በመቶ ተቀንሶ የይደረግ የነበረውን የቀረጥ ስሌት እንዲተው አድርጓል።


በዚህም መሰረት ከአሁን በሁዋላ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሚከፍሉት ቀረጥ የሚሰላው ከዋና ዋጋቸው ላይ መኪናው ላገለገለበት እስከ 30 በመቶ ተቀንሶ ሳይሆን በዋና ዋጋቸው ይሆናል ማለት ነው።ይህም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡበት የነበረውን ማበረታቻ በእጅጉ ይጎዳዋል።የሀገር ውስጥ የመኪና ዋጋም ላይ ከፍተኛ ጭማሬን ሊያስከትል እንደሚችል ይጠበቃል።


መመሪያው ከመውጣቱ በፊት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን አዘው መመሪያው እስኪወጣ ያልገባላቸው አስመጪዎች በምን እንደሚታዩ ገና ግልጽ አልሆነም።መንግስት ይህን የታክስ አሰራር በማስቀረት ለነዳጅ ግዥ የሚያወጣውን ምንዛሬ ለመቀነስ እንዳሰበም ይነገራል።

እስካሁን ባለው አሰራር መሰረት መኪናው ለንግድና ለቤት ነው የሚለው ከግምት ውስጥ ገብቶ ማለት ነው የሚጣለው ትንሹ ቀረጥ 125 በመቶ ሲሆን ትልቁ ደግሞ እስከ 174 በመቶ ይደርሳል። መኪና ሀገር ውስጥ የገባበት አመት ሞዴል ወይንም አዲስ ተሽከርካሪ ከሆነ መኪናው አዲስ ሆኖ ከሚኖረው ዋጋ እንደ ተሽከርካሪው አይነት ቀረጥ ይጣልበታል። መኪናው ያገለገለ ከሆነ ግን እንዳገለገለበት አመት ፣ ከመኪናው የአዲስነት ምርት ዋጋ ላይ እስከ 30 በመቶ ተቀንሶ ቀረጥ ይጣልበታል ማለት ነው። ሱር ታክስና ተጨማሪ እሴት ታክስም በተሽከርካሪ ላይ የሚጣሉና ዋጋውን በእጅጉ የሚያንሩ የቀረጥ አይነቶች ናቸው።
አሁን ተግባራዊ የሆነው መመሪያም መኪናው አገለገለም አላገለገለም ተሽከርካሪው በአዲስነቱ የነበረው ዋጋ ተወስዶ ነው ቀረጥ የሚጣልበት። ይህም በኢትዮጵያ በሰፊው ገበያ ያላቸው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ዋጋን ያንረዋል ብለውናል ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ አስመጪዎች።


የኢትዮጵያ መንግስት ይህን እርምጃ ለመውሰዱ ሌላ አላማም አለው።አንዱ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነ ቮልስ ዋገንና ኒሳንን የመሳሰሉ አለማቀፍ መኪና አምራቾች ምርቶቻቸውን እንዲያመርቱ ከስምምነት መድረሱ ተሰምቷል።እንደነዚህ አይነት ኩባንያዎች ደግሞ ሀገር ውስጥ መጥተው በማምረት እንዲሰማሩ የቀረጥ ህጉ እንዲስተካከል መጠየቃቸው አልቀረም።ነባሩ የኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ቀረጥ ደግሞ አሮጌ ተሽከርካሪን የሚያበረታታ በመሆኑ አምራቾች በገበያ የበላይነት ያስወስድብናል እያሉ ሲተቹት የቆየ ነው።አሁን የተደረገው ማስተካከያም የአምራቾችን ፍላጎት ለማሟላት ነው።

ከእሮብ ጀምሮ እንዲቀር የተደረገው ያገለገለ መኪና የእርጅና ቀረጥ ቅናሽ ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን አዲስም ሆኒ የተነዱ ዋጋቸውን ቢያቀራርበው ; አምራቾች በረጅም ጊዜ ገብተው ሲያመርቱ ምናልባት የመኪና ዋጋ ሊረጋጋ ይገባል።ይህም ቢሆን ግን ለአምራቾችና ለአዲስ ተሽከርካሪ አስመጭዎች ማበረታቻ ሊደረግ ይገባል። [ዋዜማ ራዲዮ]