ዋዜማ ራዲዮ-ከመስከረም 23 ጀምሮ መቀሌ ከትሞ የነበረው የሕወሓት ማዕከላዊ ምክር ቤት ጉባኤ በደኢህዴን ምስረታ በዓል ስብሰባና በማዕከላዊ መንግሥቱ ዙርያ ባጋጠሙ ሌሎች አጣዳፊ ጉዳዮች ምክንያት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን በዚህ ሳምንት ይቀጥላል ተብሏል፡፡

የዶክተር ደብረጽዮን ቡድን እያየለ እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ጉባኤ ሕወሓት አሁን አገሪቷ ካለችበት ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ለማውጣት ከየትኞቹ አጋር ድርጅቶች ጋር መሰለፍ እንዳለበት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫን ይይዛል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ በፌዴራል መንግሥቱ መዋቅር የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ ጭምር ይገባኛል የሚል ጥያቄ ውስጥ ውስጡን ማንሳቱና ከማዕከላዊ መንግሥቱ ትዕዛዝ እያፈነገጠ መሆኑ በሕወሓቶች ዘንድ እምብዛምም እንዳልተወደደለት ይነገራል፡፡

የድርጅቱ ብሔርተኛ ካድሬዎች ካልሆኑ በስተቀር እምብዛምም የሕዝብ አለኝታና ድጋፍ የላቸውም የሚባሉት አቶ አባይ ወልዱ የሕወሓትን የሊቀመንበርነት ቦታ ይዞ የመቀጠል እድላቸው ጠባብ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ዶክተር ደብረጺዮን ቦታውም ለመያዝ ግልጽ ፍላጎት እንዳሳዩም ተወርቷል፡፡ ምናልባት አቶ አባይ በዚህ ወንበር ላይ የሚቆዩት እስከሚቀጥለው የኢህአዴግ ጉባኤ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡
በአንጻሩ ዶክተር ደብረጺዮን ውስጥ ውስጡን ከፍተኛ የካድሬ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሕወሓት ሊቀመንበር አቶ አባይና ምክትላቸው ዶክተር ደብረጺዮን የሻከረ ግንኙነት እንዳላቸውና ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ስብሰባዎች ኃይለቃል መለዋወጣቸው ይነገራል፡፡ አቶ አባይ ወልዱ በአካባቢው ተወላጆች በአቅም ማነስ ክፉኛ የሚተቹ ቢሆንም ‹‹የትግራይን ጥቅም አሳልፈው አይሰጡም፣ በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ጭምር ታማኝ ታጋይና አታጋይ ስለመሆናቸው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ተመስክሮላቸዋል›› ስለሚባል ስልጣናቸውን ማቆየት እንደቻሉ ይነገራል፡፡