President Isayas Afeworki May 22/2018

ዋዜማ ራዲዮ- ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው ጥቃት በርካታ ፊልሞች ሊወጣው የሚችል ክስተት እንደነበር ያወሱት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቡድኑ አስመራ ላይ የመንግስት ለውጥ የማድረግ ውጥን ነበረው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሀገራቸው ቴሌቭዥን ጋር ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ዘለግ ያለ ቃለ-ምልልስ ሕወሓት ሰሜን ዕዝን በማጥቃት መጀመርያ አዲስ አበባን በመቆጣጠር በመቀጠል አስመራ ላይ የመንግስት ለውጥ የማድረግ ፍላጎት ነበረው ብለዋል።
በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በተመለከተ በቀጣይነት ረጃጅም ፊልሞች ሊሰሩበት እንደሚችል በመግለፅም ስለ ክስተቱ ገና ለህዝብ ያልተነገሩ እውነቶች ብዙ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ፖለቲከዊ ችግር ምንጩ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን ሕወሓት የፈጠረው ብሄር ላይ ትኩረት ያደረገ ፖለቲካ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ህገመንግስቱ ከመፅደቁ በፊት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ረቂቁን ሰጥቶኝ አንብቤ ለኢትዮጵያ እንደማይሆን ነግሬው ነበር ነገር ግን ሊሰማኝ አልቻለም ብለዋል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው ህገ መንግስት ሀገሪቷን ወደ ግጭትና መበታተን የሚያመራ እንደሆነ ፣ የተመሰረቱ ክልሎች እየቆዩ የሚፈነዱ ቦምቦች እንዲሆኑ ተደርገው መመስረታቸው አብራርተዋል በቃለመጠይቁ።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነት የድንበር ችግር ሳይሆን ወደ ግጭት እንድናመራ ያደረገን የሕወሓት የሀያላን ሀገራት ወኪል በመሆን ቀጠናው ሲያምስ ስለ ነበር ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡

በሁለቱም ሀገራት ባለፉት ሶስት አመታት መልካም የሚባል ግንኙነት የተጀመረ ቢሆንም ሕወሓት ማንም ያልጠበቀው ጥቃት በሰሜን ዕዝ በመፈፀሙ የኢትዮጵያ መንግስት እርምጃ መውሰዱን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ የኤርትራ ሚና ምን እንደነበር በግልፅ አላስቀመጡም፡፡

አሁንም ቢሆን ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ማለት እንደማይቻልና ኤርትራ ጉዳዩን በንቃት እንደምትከታተለው የገለፁ ሲሆን እዚህም እዛም የሕወሓት ቅሪቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ሀይላችን አሰባስበን ወደ ፀረ-ማጥቃት ተግባር እንመለሳለን የሚሉ ድምፆች ከሕወሓት ቅሪቶች እንደሚሰሙ አስታውሰዋል፡፡

ከናይል ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ጉዳዩ የውጭ ሀገራትና ሀያላን መንግስታት በማስገባት ለመፍታት ከመስራት ይልቅ በአከባቢው የሚገኘ እስከ 250 ሚሊዮን የሚገመት ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብር መሆን እንዳለበት ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል የተፈጠረው የድንበር ውጥረት ለምን አሁን ወደ ከፋ ደረጃ ደረሰ? ተብሎ በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የኢትዮጵያና ሱዳን ጉዳይ ብቻ አይደለም ፡፡ ሁለቱም ሀገራት በሽግ ግር ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ጉዳዩን በስክነት ማየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን የሚታየው ውጥረት አስፈሪ ቢሆንም ጉዳዩ በቅንነት ከታየ በቀላሉ መፍታት ይቻላል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ በኤርትራ ስላለው የፖለቲካ፣ የስብዓዊ መብትና ተያያዥ ጉዳዮች አላነሱም። ሀገራቸው የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ያደረገችውን ጥረት አብራርተዋል። በኢኮኖሚ መስክ አዳዲስ ጥናቶችን በማድረግ ወደተግባር ለመግባት እየተዘጋጁ መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]