TPLF-leaders

  • የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ የአማርኛና የኦሮምኛ የቴሌቭዥን ስርጭት በቅርቡ ይጀምራል

ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይን ክልል የሚመራውና እስከቅርብ ጊዜ በሀገሪቱ የፖለቲካ አመራር የፈላጭ ቆራጭነት ሚና የነበረው ሕወሐት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አመራር ላይ ሁለት የተለያዩ አቋሞችን ለማስታረቅ መቸገሩ ተሰማ።

በድርጅቱ በመካከለኛ ሀላፊነት ላይ ያሉና (የለውጥ ሀሳብ ደጋፊ የሆኑ) ሶስት አባላቱ እንደነገሩን አንዳንድ የሕወሐት አመራሮች
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚከተሉት “መርህን ያልተከተለ” የፖለቲካ መንገድ ራሳቸውንም ሆነ ሀገሪቱን ለከፋ አደጋ ያጋልጣታል ብለው ያምናሉ። ሌሎች አመራሮች በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እየሄዱበት ያለው መንገድ ጉድለቶች ቢኖሩበትም በሂደት እያረሙ መሄድ እንጂ ለውጡን መቃወም ከህዝብ ጋር ያላትመናል ብሎም ወዳልተፈልገ የድርጅት መሰነጣጠቅ እንገባለን ብለው ያምናሉ።

ዶ/ር አርከበ ዕቁባይንና ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ በድርጅቱ ተሰሚነት ያላቸው አመራሮች በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥ ውስጥ ሀገሪቱን ወደተሻለ መረጋጋትና ስላም በመመለስ ርዕዮተ አለማዊ ልዩነቶችን በውስጠ ድርጅት መድረኮች በማንሳትና በመከራከር አስፈላጊ ከሆነም በማሻሻል መጓዝ አማራጭ የለውም ብለው ያምናሉ።
በርካታ የቀድሞ አመራሮችን በያዘው ሌላኛው ወገን ግን የትግራይ ህዝብና ሕወሐት መስዋዕትነት የከፈሉለት ዓላማ ሲካድና “በህዝበኝነት” ሲተካ ዝም ብሎ መመልከት “የሰማዕታቱን ደም መካድ” ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
ሕወሐት የድርጅቱን መስመር ማስከበር ካልቻለ ከገዥው ፓርቲ ግንባር መውጣት አለበት አለበለዚም ይህን የመስመር ክህደት በአደባባይ ልንዋጋው ይገባል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

ሁለቱም ወገኖች “ትግሬ ጠል”  የሆኑ አስተሳሰቦችና ዘመቻዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስፋት ስራ መሰራት አለበት የሚል ዕቅድ ነድፈዋል።
በዕቅዱ መሰረት በተለያዩ ክልሎችና በዲያስፖራ የሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ይኖራሉ።

በትግራይ ህዝብ ላይ የሚነዙ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቀልበስ በማለም የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሀን ኤጀንሲ የአማርኛና የኦሮምኛ የቴሌቭዥን ስርጭት በቅርቡ ይጀምራል።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለሕወሐት አመራሮች በተበተነው የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ ላይ የትግራይ ህዝብ በአዲሱ የፖለቲካ ለውጥ ሳቢያ የገጠመውን ፈተና በፅናት እንደሚታገልና ማናቸውንም ገንቢ ለውጦች እንደሚደገፍ አብራርቷል።
ወጣት የሕወሐት አባላት ግን ድርጅቱ ተተኪ ማፍራት አልቻለም፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ለውጥ የሚመጥን አመራር መስጠት ተስኖታል፣ ስለዚህም ከክልሉ ህዝብ ጋር ስፊ ውይይት በማድረግ ራሱን ከስረ መሰረቱ ካልቀየረ ሕወሐት ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የትግራይ ተወላጅ ሆነው ስለመነጠልና ስለጥላቻ እያወሩ የክልሉን ህዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያ የሚያቃቅሩትን መምከርና መገሰፅ አስፈላጊ መሆኑንም ድርጅቱ ያምናል።
ሕወሐት የልዩነት ሀሳቡን ለማስታረቅ ተከታታይ ስብሰባዎችን እንደሚያደርግና በኢህአዴግ መድረኮች ላይም “የአመለካለት ጥራት” እንዲመጣ እታገላልሁ ብሏል።