- በአዲሱ ህግ መሰረት የሚለምንም የሚሰጥም ተጠያቂ ይሆናሉ
ዋዜማ- የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተስፋፋ የመጣውን ልመና ያስቀራል የተባለ “የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀ ነው ።
በፌደራል ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው “የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ረቂቅ አዋጅ በአገር አቀፍ ደረጃ የተባባሰ የመጣውን ልመና፣የወሲብ ንግድን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ ቀውሶችን “እንደሚፈታ” ተስፋ ተጥሎበታል።
በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ደረጄ ታዬ ለዋዜማ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ልመናን ለማስቀረት በአዲስ አበባ ደረጃ እና በክልሎች ሰፊ ጅማሮዎች ተደርገው የነበሩ ቢሆንም የህግ ማዕቀፍ ባለመዘጋጀቱ ጉዳዩ የአንድ ወቅት ስራ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።
ልመናን “ለማስቀረት” የሚያስችለው የህግ ማዕቀፉ ሲጠናቀቅ በአንድ ቋት ሰዎችን መርዳት የሚያስችል ስርዓት ይዘረጋል ። ከዚህ ስርዓት ውጪ የሚደረግ መፅዋት ሰጪም ሆነ ተቀባይ ተጠያቂ ይደረጋሉ።
“የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ረቂቅ አዋጅ ስራ ላይ ሲውል አሁን ያለውን የልመና መበራከት “መፍትሄ እንደሚያገኝ” በመንግስት በኩል እምነት ተጥሎበታል።
የሐይማኖት ተቋማት ጋር በጉዳዩ ዙርያ በጋራ ለመስራት ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኝም ሰምተናል።
በተለይ የኢትዮጲያ መንግስት ለጎዳና ሕይወት የተዳረጉትን እንዲረዳ በተለያዮ ጊዜያት ከአለም ባንክ ድጋፍ ማግኘቱ የተነገረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ዛሬም ድረስ ተመፀዋች የሆኑ ጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በእጥፍ እየጨመረ ነው ።
በአዲስ አበባ 88,960 በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን፣ 50,000 ያህሉ በዋና ከተማዋ ጎዳናዎች እንደሚኖሩ በ2015 መጀመሪያ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀለት ” የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ” ልመናን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንዳለው ተነግሯል። ይህም ረቂቅ ሰዎች በየመንገዱ የመስጠት ልምዳቸውን የሚያስቀር ሲሆን በልመና የተሰማሩ ወገኖችንም አደብ የሚያስዝ ነው ተብሏል።
”ልመና እንደ ሀገር ልምድ እየሆነ እየመጣ ነው ” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ደረጄ ታዬ ተቀባዮንም በዘላቂነት የማያግዝ እና ገፅታን የሚያበላሽ ነውም ብለዋል።
በቅርቡ በሚፀድቀው ህግ የሀገር ውስጥና የውጪ ረጂ አካላት በአንድ ቋት ድጋፍ አድርገው ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰቡ ክፍል እንዲደርስ የሚደረግበት ስርዓት እየተዘረጋ ነው።
ልመናን የሚጠላ ዜጋ ለመፍጠርም የስነ ልቦና ግንባታና ድጋፍ የሚሰጥ የስራ ክፍል ተቋቁሟል።
በ2015 በሚኒስቴሩ ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባው ”የቤተሰብ ዲፓርትመንት” ልጆች ወደ ጎዳና ወጥተው በልመና እንዳይሰማሩ ብሎም ለሱስ እንዳይጋለጡ ቤተሰብ ላይ የሚሰራ ነው ። በቀጣይም በየክልሉ፣በዞን ብሎም እስከ ወረዳ ባሉ ቢሮዎች ክፍሉን በማቋቋም በዘርፉ ለመስራት ታቅዷል።
አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ተጠናቆ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ፍትህ ሚኒስቴር መላኩን ዋዜማ ሰምታለች።
በፍትህ ሚኒስቴር ዝርዝር የህግ ማዕቀፎች እየተዘጋጀ መሆኑንም ከፍትህ ሚኒስቴር የሰማነው መረጃ ያመላክታል። የሕግ ማዕቀፎች ተካተው ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኮ እንደሚፀድቅም ይጠበቃል።
ለጎዳና ሕይወት ተጋላጭ የሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች አምራች የሚባሉት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ክልል ያሉት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። [ዋዜማ]