ዋዜማ ራዲዮ- መስከረም 28፣2009 የተደረገው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ አቶ የሺዋስ አሰፋን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ በከፍተኛ ድምጽ መምረጡን ተከትሎ ‹‹ምርጫው ተጭበርብሯል፣ የፓርቲው ደንብ በሚያዘው መሠረት ምርጫ አልተካሄደም፣ የፓርቲው ሕጋዊ መሪ እኔ ነኝ›› ሲሉ ልዩነት ያሳዩት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ወደ ፓርቲው ዳግም ለመመለስና ከአዲሱ የፓርቲው ሊቀመንበር ጋር የተፈጠሩ ልዩነቶችን ለማጥበብ ላለፉት ወራት ሽምግልና የተቀመጠው ቡድን ሰላም ለማውረድ ጫፍ መድረሱ ተሰምቷል፡፡

‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ሕዝቡ ተስፋ እንዲቆርጥ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ይህን የመሰሉ ዉስጣዊ ሽኩቻዎች ናቸው›› ያሉ አንድ ስማቸውን መግለጹ የማይሹ የአስታራቂ ቡድን አባል ‹‹የሺዋስንና ይልቃልን ካጨባበጥን ለሌሎች ፓርቲዎች አርአያ የሚሆን ተግባር እንደፈጸምን እቆጥረዋለሁ›› ብለዋል፡፡ ሽምግልናው በከፍተኛ ምስጢር እንዲያዝ የተደረገ ቢሆንም ሂደቱን የተከታተሉ አባላት ‹‹ተስፋ ሰጪ›› እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የሽምግልናውን ቡድንን የሚመሩት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያምና ጠበቃ ተማም አባቡልጉ እንደሆኑም ታውቋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋን በመረጠበት ጠቅላላ ጉባኤ ሹም ሹር ከማካሄዱም በላይ በሥነ ምግባርና በገንዘብ ምዝበራ ኢንጂነር ይልቃልንና ምክትላቸውን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ቡድን የተላከን ገንዘብ ለፓርቲው ሳያሳውቁ ወደኪሳቸው አስገብተዋል የሚል ክስም በወቅቱ ቀርቦባቸው ነበር፡፡
ከዛሬ 8 ወራት በፊት አዲስ የተመረጠው የአቶ የሺዋስ አሰፋ አመራር ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በተሰበሰበበት መድረክ ኢንጂነር ይልቃልን የሚደግፉ ወጣቶች ጸያፍ የስድብ ናዳ በአዲሱ አመራር ላይ በማዝነብ መድረኩን ማወካቸው በወቅቱ ከፍ ያለ የሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር፡፡
አምስት አባላት ያሉት የሽምግልና ቡድን ለወራት በዘለቀው ጥረቱ ሁለቱንም አመራሮች በተናጥል በማግኘት ለማግባባት የሞከረ ሲሆን ጥረቱ ፍሬ ካፈራ ኢንጂነር ይልቃል የአቶ የሺዋስን ቡድን ሕጋዊነት ተቀብለው በአባልነት ለፓርቲው እገዛ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሠረተ ረዥም ዓመታትን ያላስቆጠረ ቢሆንም በአዲስ አበባና በባርህርዳር ሕዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን በማካሄድ የተሻለ የተቃውሞ ድምጽ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ፓርቲው እንደገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ነሐሴ 7 በአዲስ አበባ መነሻውን ምንሊክ አደባባይ፣ መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገ ታላቅ የተቃውሞ ሕዝባዊ ሰልፍ ለመጥራት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡