ዋዜማ ራዲዮ- የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በሽብርተኝነት” የተፈረጀው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረባቸው ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት “ያለ አግባብ ተወስዶብኝ ነበር” ያለውን አንድ ቀበሌ አሁን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ማስተዳደር መጀመሩን የክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ሻለቃ ኢብራሒም ሑመድ ለዋዜማ ራዲዮ ተናግረዋል።
“ሳውኔ” የምትባለዋ ይህቺ ቀበሌ በአፋር ክልል ዞን ሁለት፣ ዳሎል ወረዳ እና በትግራይ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን በሳጺ ጸዓዳ አንባ ወረዳ መካከል የምትገኝ ናት።
ቀበሌዋ አፋርኛም ትግርኛም የሚነገርባት ሲሆን አሁን የአፋር ክልል መንግስት የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ማስተዳደር መጀመሩን ሻለቃ ኢብራሒም ነግረውናል።
ሳውኔ የምትባለው ቀበሌ ሸክ አደም ቡራ እና ካላክ በመባል የሚታወቁ አካባቢዎች ያሉባት ሲሆን አብዛኛው የአካባቢው አየር ሁኔታ ደጋማ የሚባል ነው።
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ በትግራይ ክልል በማዕከላዊ ዞን በሳጺ ጸዓዳ አንባ ወረዳ ስር ስትተዳደር ነበር።
የቀበሌው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ የማንነት ጥያቄ በማንሳት በአፋር ክልል ውስጥ እንተዳደር የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን ያነጋግርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ያሰረዳሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ከሰባት ዓመት በፊት ጥያቄውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበው እንደነበር ለመረዳት ችለናል። በቀበሌው ይነሳ በነበረ የማንነት ጥያቄ ሳቢያም የአካባቢው ነዋሪዎች ከትግራይ ክልል የልማት ሴፍቲኔት : የጤና እና መሰል አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ እንዳያገኙ አድርጓቸው እንደቆየ ይናገራሉ።።
አካባቢው ወደ አፋር ክልል የተጠቃለለውም ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሀት በኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ የአፋር ክልል ልዩ ሀይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋራ በመሆን የአጸፋ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ ቀበሌው አልፎ አልፎ ሰርገው እየገቡ ጥቃት እንደሚፈጽሙ የተነገረ ቢሆንም የክልሉ መንግስትም ጥቃቱን እየተከላከለ መሆኑን የክልሉ ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ ሻለቃ ኢብራሒም ሑመድ ተናግረዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]