- ወታደራዊ ክንፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል
ዋዜማ ራዲዮ-ከኦሮሚያ ህዝባዊ አመፅ አስተባባሪዎች ግንባር ቀደሙ ጃዋር መሀመድ በሚኒሶታ በቢሾፍቱ የደረሰውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ መስከረም 23 ቀን የኦሮሞ ማህበረሰብ ባደረገው ስብሰባ ላይ እንደጠቆመው የኦሮሞ የመብት ትግል በቅርቡ ወደ አዲስ ምዕራፍ ይሸጋገራል።
ከአዳዲስ ዕቅዶቹ መካከል የኦሮሚያን የነፃነት ቻርተር ማዘጋጀት ብሎም በሽግግር መንግስት ምስረታወቅት የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን ማድረግ ይገኝበታል። ህዝባዊ አመፁን የበለጠ ለማጠናከር ህዝባዊ ድጋፍ አስፈላጊ በመሆኑ በተበታተነ መልኩ እየተካሄደ ያለውን ድጋፍ በማዕከላዊነት የሚያስተባብር አካል ያስፈልጋል ብሏል ጃዋር።
“ስዎች ሀብት ንብረታቸውን ሸጠው ትግሉን ለመደገፍ እየጠየቁን ነው፣ ይህን ሁሉ የህዝብ ድጋፍ በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል” ሲል ተናግሯል በኦሮምኛ።
የኦሮሞ ወጣቶች ለትግሉ እየከፈሉ ያለውን መስዋዕትነት ያወሳው ጃዋር ለነዚህ ወጣቶች ድጋፍ ማድረግ ቀዳሚ ስራ መሆን አለበት ብሏል።
የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት ምስረታና የሚያስፈልጉ ተቋማትን በተመለከት ከሁለት ሳምንት በኋላ የኦሮሞ ህግ ባለሙያዎች ማህበር ተሰብስቦ የሚያስፈልጉ የህግ ሰናዶችን ያሰናዳል።
የኦሮሞ ህዝባዊ አመፅ አንደኛ አመትም ከአንድ ወር በኋላ (November 12) በመሆኑ በአትላንታ አሜሪካ በሚደረግ ጉባዔ የትግሉ አዳዲስ ስትራቴጂዎች ይፋ ይደረጋሉ።
የኦሮሚያ ወታደራዊ ክንፍ ማቋቋም እጅጉን አሰፈላጊ መሆኑን ያሰረዳው ጃዋር ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጠው ነው ብሏል።
በኦሮሚያ ከአምስት መቶ ሺ በላይ መሳሪያ የታጠቀ ህዝብ መኖሩንና አሁን ባለው መንግስት ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ትግሉ ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጃዋር የሚደርሱትን ጥሪዋች ዋቢ አድርጎ ተናግሯል።
“ከአስር አለቃ እስከ ጀነራል ያሉ የኦሮሞ ልጆች አፈ ሙዙን ወደ አምባገነን ገዥዎች ለማዞር እንደሚፈልጉ እየነገሩን ነው”
ወታደራዊ ሀይል ማቋቋም ለኦሮም ህዝብ ደህንነት ወሳኝ መሆኑን አክቲቪስቱ አስምሮበታል።
“ይህን ወታደራዊ ሀይል የማቋቁመው እኔ አይደለሁም እኔ ያለሁት እዚህ ሴንተራል ጎዳና(United States) ነው…. ወታደራዊ ክንፉ ሙሉ በሙሉ በሀገር ቤት የሚንቀሳቀስ ነው”
“የኦሮሞን ትግል ለማገዝ አስፈላጊ የዲፕሎማሲ የደህንነት መረጃ ድጋፎችን ከዓለም አቀፍ ማህበረስብ እያሰባሰብን ነው …እስካሁን ጥሩ ደረጃ ደርሰናል፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች አንፃር በዲፕሎማሲው ብዙ ርቀት ሄደናል”ሲል ተናግሯል ጃዋር።