Yesuf Getachew -Photo by EHRP
Yesuf Getachew -Photo by EHRP

ዋዜማ ራዲዮ-“ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል በእነ አቡበከር አህመድ መዝገብ በሽብር ተከስሰው ከተፈረደባቸው እስረኞች መካከል ሶስቱ ከቀናት በኋላ እንደሚፈቱ የዋዜማ ምንጮች ገለጹ፡፡

አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ቅዳሜ ዕለት በምህረት እንደሚፈቱ የሚጠበቁት ሶስቱ እስረኞች ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው፣ ኑሩ ቱርኪ እና ሙራድ ሹኩር ናቸው፡፡ ሶስቱ እስረኞች ለእስር የተዳረጉት በአንድ መዝገብ አብረዋቸው እንደተከሰሱት ሙስሊሞች ሁሉ በሐምሌ 2004 ዓ.ም ነበር፡፡

እነ ዩሱፍ ሶስት ዓመታት ከፈጀ የፍርድ ቤት ምልልስ በኋላ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር የተፈረደባቸው፡፡ በዕለቱ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከ22 ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርሱ የእስር ቅጣቶች አስተላልፎ ነበር፡፡ ውሳኔው ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖችን አስደንግጦ እና አሳዝኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ከፍርዱ ጥቂት ቀናት በኋላ ከመንግስት ዘንድ የተሰማው ዜና ግን ያልተጠበቀ ነበር፡፡ እንግዳው ዜና መንግስት የ2008 ዓ.ም አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ይቅርታ እና ምህረት ካደረገላቸው እስረኞች መካከል በዚሁ መዝገብ የተፈረደባቸው አምስት ሙስሊሞች መካተታቸው ነበር፡፡

በእስልምና አስተምህሮቱ ይበልጥኑ በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው እና 22 ዓመት ተፈርዶበት የነበረው ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ከተፈቺዎች መካከል ነበር፡፡ እያንዳንዳቸው 18 ዓመት የተፈረደባቸው ጋዜጠኛ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን እና ሳቢር ይርጉ እንደዚሁም ሰባት ዓመት የተፈረደበት ሼክ ባህሩ ኡመር በወቅቱ በምህረት ከእስር የተለቀቁ ናቸው፡፡

ከዓመት በኋላ ደግሞ የሰባት ዓመት ፍርደኞች የነበሩት ዩሱፍ፣ ኑሩ እና ሙራድ እንደሚለቀቁ ለቤተሰቦቻቸው ተደውሎ እንደተነገራቸው ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ የዩሱፍ ባለቤት መረጃውን የሰሙት በእስር ላይ ከሚገኝበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር እንደሆነ ለቤተሰቡ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

በመጀመሪያው የስልክ ጥሪ “ነገ ሐሙስ ይፈታል” ተብሎ ቢነገራቸውም በስተኋላ ላይ በድጋሚ ተደውሎ ለቅዳሜ መዛወሩን እንደተገለጸላቸው ያብራራሉ፡፡ እንደ ዩሱፍ ቤተሰቦች ሁሉ የኑሩ እና ሙራድ ቤተሰቦችም ተመሳሳይ የስልክ ጥሪ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት እንደደረሳቸው ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ለቢ.ቢ.ኤን ሬድዮ ይሰራ የነበረ ጋዜጠኛ ሲሆን ከ2002 ዓ.ም እስከ 2004 ዓ.ም በህትመት ላይ የቆየችው እና በተለይ በሙስሊም ወጣቶች ዘንድ ተነባቢ የነበረችው “የሙስሊሞች ጉዳይ” መጽሔት ዋና አዘጋጅም ነበር፡፡

የእዚህ መጽሔት መስራች የነበረው እና በጻፋቸው ታሪካዊ መጽሐፎች ይበልጥ የሚታወቀው አህመዲን ጀበልም በተመሳሳይ መዝገብ ተከስሶ 22 ዓመት ተፈርዶበት በቃሊቲ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት በምህረት የተፈታው ጋዜጠኛ አቡበከር ከመጽሔቱ አምደኞች እና መስራቾ እንዱ ነበር፡፡ ሌላኛው መስራች እና የመጽሔቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበረው ሰለሞን ከበደም በሌላ መዝገብ ተከስሶ ከተፈረደበት በኋላ እስራቱን ጨርሶ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ሶስቱ ተፈቺዎች “ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል ቢፈረድባቸውም አንዳቸውም የኮሚቴው አባል አልነበሩም፡፡