Ethiopia Turkey high delegation -FILE
Ethiopia Turkey high delegation -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ለ7ኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የግንባታ ዘርፍ ኢንዱስትሪ አውደ ርዕይ በግማሽ ሐዘንናና በሩብ የቢዝነስ ተስፋ ለአራት ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ የጎብኚዎች ቁጥር እንደቀድሞዎቹ ጊዜያት አመርቂ የሚባል አልሆነም፡፡ ሚሊንየም አዳራሽም እንደወትሮው አልደመቀም፡፡ ኸረ እንዲያውም ስጋት ሸብቦታል፡፡ ከዋናው መግቢያ በር በስተቀኝ አንድ ግዙፍ እሳት አደጋ ማጥፊያ መኪና፣ ሁለት ፒክአፕ የፖሊስ መኪኖችና ሁለት አምቡላንሶች ቆመው ይታያሉ፡፡ ጎብኚዎች ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍራቸው ተፈትሸው ይገባሉ፡፡ የተሸከርካሪዎች ፍተሻ የሞተር ዘይታቸውን የመጭመቅ ያህል ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ በቂ ምክንያት አለው፡፡

አውደ ርዕዩ እየተካሄደ ያለው በገዢዎቻቸው የተቆጡ ሕዝቦች በቱርካዊያን በተያዙ ኩባንያዎች ላይ ቁጥር ስፍር የሌለው ኪሳራን ባደረሱ ማግስት ነው፡፡ ከፋብሪካዎቻቸው ግንባታ ጎንለጎን የአካባቢውን ኅብረተሰብ ለማባበል ብዙ ርቀት የተጓዙት ቱርኮቹ አሁንም ድረስ ግልጽ ያልሆነላቸው አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ለምን እነርሱ የጥቃት ዓላማ እንደተደረጉ፡፡ ለቀረባቸው ዜጋ ሁሉ እኛ ምን አጠፋን? የሚል ጥያቄን ባዘለ ስሜት What is going on in this poor nation? እያሉ ድምጻቸው ዝግ አድርገው ይጠይቃሉ፡፡ ጮክ ብሎ ሁኔታውን ለማስረዳት የሚሞክር ዜጋ ግን የለም፡፡ ጮክ ለማለት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ አይፈቅድም፡፡

የብሉምበርግ የቅርብ ጊዜ ዘገባ የፍሊንስቶን ኩባንያ ባለቤት የሆኑትን አቶ ፀደቀ ይሁኔን ጠቅሶ እንደሚያትተው አገሪቱ 70 በመቶውን የግንባታ ቁሳቁስ የምታገኘው የዉጭ ምንዛሬዋን ከስክሳ ነው፡፡በየአመቱ 12 በመቶ እያደገ እንደሚገኝ የሚወራለት የግንባታ ዘርፍ ጠቅላላ የአገር ዉስጥ ምርት ድርሻ ከ6 በመቶ አይዘልም፡፡

የንግድ ሚዛን ጉድለቱ ከ3 ቢሊየን ብር ወደ 14 ቢሊየንብር ለማደጉ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ግብአት አቅርቦት ከአገር ዉስጥ አለማግኘቱ አይነተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከኬብል እስከ ኤሌክትሪክ እቃዎች፣ ከበር ቁልፍ እስከ አልሙኒየም ፍሬምአገር ዉስጥ የሚመረት የለም፡፡ ቱርኮቹ እንደነገሩ መንገዱን ጀምረውት ነበር፡፡ ለምሳሌ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት በጁነዲን ባሻ የሚመራው የቱርኮቹ ቤሜት ቴሌኮም ኢንደስትሪያል በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበር፡፡ የፋይበር ኦፕቲክስ ምርት በተለይም ለኢትዮቴሌኮም በገፍ ማቅረብ ጀምሮ ነበር፡፡ የዉጭ ምንዛሬ እንደቁምጣ ለሚያጥረው መንግሥት ይህ መልካም ዜና ነበር፡፡ ኾኖም ፋብሪካውን የሰበታ እሳት በላው፡፡

ቱርኮች ኩባንያዎቻቸውን ወደ ሀበሾች ምድር ለመላክ ሦስት ቁልፍ ነገሮች ያነሷሷቸዋል፡፡ በአፍሪካ ሁለተኛው ሰፊ የሕዝብ ቁጥርና ይህን ተከትሎ የሚገኝ አዲስ የአፍሪካ ገበያ፣ እምብዛምም ያልሰለጠነ ርካሽ ጉልበት፣ እንዲሁም አንጻራዊ መረጋጋት ያደላት አገር፡፡ ከዚህ ሌላ በዚች አገር ዉስጥ ባለሀብትን የሚማርክ ቅንጣት ነገር ማግኘት 100% ትርፍ የማግኘት ያህል ከባድ ነው፡፡ ቢሮክራሲው ክፉኛ ያንገሸግሻቸዋል፤ ጉምቱ ባለሥልጣናት የእውቀት ቅጥነትና የዉሳኔ ድኩማን መሆን ያስገርማቸዋል፡፡ ኾኖም ችግሩን በሁለት መልክ ይወጡታል፡፡ አንዱ መንገድ አግባብተው ወደ አገር ቤት የጋበዟቸውን እነ አባዱላ ገመዳን፣ እነ አያሌው ገበዜን በተለይም ደግሞ የቀድሞው የቱርክ አምባሳደርና የአሁኑ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ያስቸግራሉ፡፡ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሳይቀር መደወልና ማለቃቀስ እለታዊ ተግባራቸው እንደሆነ በረዳትነት አብረዋቸው የሚሰሩ ሁሉ የሚናገሩት ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ የበታች ቢሮክራሲውን በገንዘብ ማባበል ነው፡፡ ቻይናዎች በዚህ ረገድ ይልቋቸዋል፡፡ ለአፍሪካ ሙስና ብለው በተለየ ቋት የሚይዙት በጀት እንዳላቸው ይነገራል፡፡

ዞሮ ዞሮ ለቱርኮቹ አሁን ጥሩ ጊዜ አይደለም፡፡ የአስራ አንድ ፋብሪካዎችን ቃጠሎ ተከትሎ ባለሀብቶቻቸው ቆም ብለው ማሰብ ጀምረዋል፡፡ በአውደ ርዕዩ ተሳታፊ የነበሩት የቱርክ ኩባንያዎች አገር ዉስጥ ገብቶ በቀጥታ ግዙፍ ፋብሪካ ከመትከል ይልቅ ምርቶቻቸውን በወኪል ማስነገድ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ በማመናቸው ስለዚሁ ማውጠንጠን ይዘዋል፡፡ አውደርዕዩ ላይ የነበሩት ቱርካዊያን የወኪል ያለህ ሲሉ የነበረውም ለዚሁ ነው፡፡

ኮንክሪት ማሟሻ (Batching Plant) በመገንባት፣ በመትከል፣ በማቅረብና በመሸጥ የሚተዳደሩ ሦስት ኩባንያዎች በዚህ 7ኛው አለማቀፍ አውደ ርዕይ ቀርበው ነበር፡፡ ከነዚህ ዉስጥ መካ ኢንደስትሪያል አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ገበያ አዲስ አይደለም፡፡ ደረጃ አንድ ተቋራጭ ለሆኑት ለባማኮን ባለቤት ለአቶ ግርማ ገላው፣ እንዲሁም ለጀስቲስ ኮንስትራክሽን ባለድርሻ ለአቶ የሱፍ እና ለአሰር ኮንስትራክሽን ዉስብስብ የኮንክሪት ማላወሻ ማሽን አቅርቧል፡፡ ይህ የኮንክሪት ማሟሻ ማሽን (Batching Plant) ማንኛውንም ግንባታ በ40 በመቶ የሚያፋጥን ነው፡፡ አንድ ግዙፍ ኮንክሪት ማሟሻ እስከ 40 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያስወጣል፡፡ ከደረጃ አንድ ተቋራጮች ቋሚ ኮንክሪት ማላወሻ (Batching Plant) ያላቸው ከአምስት አይበልጡም፡፡

ይህን ማሽን በ60 አገራት ዉስጥ የተከለ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለትልልቅ ተቋራጮች ማሽኑን ያቀረበ፣ በትእዛዝም የገነባና የሚገነባው የመካ ኢንደስትሪያል ሰዎች እኛ ወደ ኢትዮጵያ የምንገባው አሁን አይደለም፤ ቀስ በቀስ ነው፤ ግዙፍ ግንባታዎች በስፋት መስራት ስትጀምሩ ይላሉ ወደ አገሪቱ በሙሉ ጉልበት ገብተው ለምን ኢንቨስት እንደማያደርጉ ሲጠየቁ፡፡ ሁነኛው ምክንያት ግን የአገሪቱ መረጋጋት አስተማማኝ ስላልሆነ እንደሆነ ከልብ ለቀረቡት ሰው ብቻ ትንፍሽ ይላሉ፡፡

ሦስት ሚሊዮን ስኩዌርሜትር የሚሸፍን እጅግ ግዙፍ ግንባታን በአልጄሪያ እያካሄደ የሚገኘው ክሪቲካል ዲዛይን ስቱዲዮ ከኢስታንቡል ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ለመጀርያ ጊዜ ነው፡፡ የዚሁ አውደ ርዕይ ተሳታፊ ነው፡፡ በኪነ ሕንጻ ዝግጅትና ግንባታ ማማከር ላይ የተሰማራ ተቋም ሲሆን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ እየተመነደገ ከተማዋም ፈርሳ እየተሰራች ስለመሆኑ በአዘጋጆቹ ተነግሯቸው ወደ አውደ ርዕዩ መምጣቱን ይናገራል፡፡ በሁለት ወጣት አርክቴክቶች የተወከለው ይህ ኩባንያ ብዙም ጎብኚ አልነበረውም፡፡ እስካሁን ተስፋ የጣልንበትን ገበያ አላገኘንም ባይ ናቸው፡፡ ከተማዋን ተዘዋውረው መመልከታቸውን፣ በኪነ ሕንጻ ደረጃ አንድም አይነ ግቡ ሕንጻ ለማየት እንዳልታደሉ ከዚያ ይልቅ ምስቅልቅሉ የወጣ ነገር መመልከታቸውን ከትህትና ጋር ይናገራሉ፡፡ “ከተማችሁን መልክ ለማስያዝ ትንሽ ሳትዘገዩ አልቀራችሁም” ይላል ኩባንያውን ወክሎ የመጣ አንደኛው አርክቴክት፡፡ የተበጣጠሱና ጉራማይሌ ግንባታቸዎችን እዛም እዚም መመልከቱ ስለ አዲስ አበባ ከሰማውና ከጠበቀው ነገር ጋር እንዳልሄደለት ይመሰክራል፡፡

ሮያል ቦሌ ጄኔራል ኮንትራክተርን ያቀፈው ሜትሮፖሊታን ሪልስቴት በአሜሪካዊ ቱርካዊ የተቋቋመ ኩባንያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዉስጥ በግማሽ ልብ ሆኖ ግንባታ ላይ ተሰማርቷል፡፡ እንደማሳያ (ፓይለት ፕሮጀክት) ሳርቤት ገብሬል ከደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ገባ ብሎ ባለ 6 ፎቅ ቅንጡ አፓርትመንት እየገነባ ነው፡፡ ሁሉም ባለ ሦስት መኝታ ሲሆኑ ዋጋቸው 10 ሚሊየን ይጠጋል፡፡ ገንብተን ሳንጨርስ አንሸጠውም ይላሉ ቱርካዊያኑ፣ የሪልስቴት ቢዝነስ መልካም ስም በአገሪቱ ከመጉደፉ ጋር ተያይዞ፡፡ ይህ ኩባንያ በከፊል ድርሻው ኢትዮጵያዊያን ባለሐብቶችን በማሳተፉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ዋና መስሪያ ቤቱን አሪዞና አድርጎ በአሪዞናና ፍሎሪዳ ብቻ 400 ቤቶችን ገንብቶ እንደሸጠ ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያ ለመሥራት ተልሞ የተነሳው በከተማ ሰፋ ያለ መሬት የያዙ ባለሐብቶችን አሳትፎ አፓርትመንቶችን ከቦታው ባለቤቶች ጋር በጋራ የቢዝነስ ቁርኝት እየፈጠሩ ለመገንባት ነው፡፡

ላዲን ኢንተርናሽናል በሚያዘጋጀው በዚህ አለማቀፍ የግንባታ ዘርፍ አውደ ርዕይ ከዚህ ቀደም ከጆርዳን፣ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፣ ከጀርመን፣ ከጣሊያን በርከት ያሉ የግንባታ ግብአት አቅራቢዎች ተገኝተው ነበር፡፡ 6ኛውን አውደ ርዕይ አምና 6ሺ የሚሆኑ ጉብኚዎች እንደተመለከቱት ላዲን ኢንተርናሽናል ይናገራል፡፡ በዚህኛው ዙር ግን የዚህን ግማሽ እንኳ ጎብኚ ለማግኘት ፈተና ሆኗል፡፡ ለ20 ካሬ የአውደ ርዕይ ቦታ እስከ 150 ሺ ብር ኪራይ የከፈሉት ኩባንያዎቹ አሁን የሚያስቆዝማቸው የቦታ ኪራይ ወይም የጎብኚ ማነስ አይደለም፡፡ በአገሪቱ በቅርቡ የሆነውና የተደረገው ነገር አልገባቸውም፡፡ለአፍታ ቁጭ ብሎ ከልብ ለሚያወጋቸው ሰው ሁሉ እነ ሳይገንዲማ ለምን እሳት እንደተለኮሰባቸው፣ እነ ኤልሴ አዲስ ስለምን ሠራተኛ በትነው እንደተዘጉ፣ አይካአዲስ ስለምን “አልተቀበርኩም እንጂ ሞቻለሁ” እንደሚል ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ አይካ አዲስ የአዋሳን ያሕል የኢንደስትሪ መንደር ገንብቼ አገሪቱን ፋብሪካ በፋብሪካ ላድርጋት እያለ ሲፎክር የነበረ ተቋም መሆኑ አይዘነጋም፡፡ አሁን የራሱ ሕልውናም አደጋ ተደቅኖበታል፡፡

በአገሬው የከረሙ ቱርኮች ደግሞ መንግሥትን ባቅም ማነስ ይተቻሉ፡፡ Your government dreams big but full of bad ministers ይላሉ ለተግባቧቸው ሀበሾች፡፡ ርካሽ የሰው ኃይሉ ደግሞ አንድም አይነት የሥራ ዲሲፕሊንና ፍቅር የሌለው፣ ልግምተኛ፣ የሥራ ተነሳሽነት ብቻም ሳይሆን የሥራ ክህሎት (Skill) የሌለው እንደሆነ አምርረው ያወራሉ፡፡ የጥሬ እቃ አቅርቦት ማነስ እምባቸውን ያመጣዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የምታጓጓ ነገር ግን መልካም የቢዝነስ ቦታ መሆን ያልቻለች ምስኪን አገር እንደሆነች ያስባሉ፡፡

የዉስጥ ፖለቲካችንን እንደ አገሬው አብጠርጥረው የሚያውቁ ቱርኮችም አጋጥመውኛል፡፡ አዲስ ሰው ሲገጥማቸው ከየትኛው ብሔር እንደሆነ ደፈር ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ለየትኛው ብሔር አባል ምን ማውራት እንዳለባቸው ሁሉ ጠንቅቀው የተረዱ ይመስላል፡፡ አመጹ በኦሮሚያ በኩል እንደከፋ፣ የኦሮሞ ሕዝብ በፖለቲካ የበላይነት የበይ ተመልካች እንደሆነ ጃዋር መሐመድ የሚባል መሪ እንዳለ ለቀረቡት ሰው ሲያወሩ አፍ ያስከፍታሉ፡፡ Jawar is like Fetulah Gullan of Turkey, Ha! ብለው የኮረኮሯቸውን ያህል በራሳቸው ማወቅ ይስቃሉ፡፡