FILE-IREX

ዋዜማ ራዲዮ- የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት በጋዜጣ አሳታሚ ደንበኞቹ ላይ ያደረገውን የዋጋ ጭማሪ የሚገልጽ ደብዳቤ ለደንበኞቹ የላከው መጋቢት2፤2014 ነው፡፡ 

ድርጅቱ የዋጋ ጭማሪውን በአንድ ጊዜ ላለመጫንም ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆነው ከሚያዚያ 1፤2014 ጀምሮ እስከ ሰኔ ፤2014 ድረስ መሆኑን በደብዳቤው ላይ ማካተቱን ዋዜማ ተመልክታለች፡፡

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት የገበያ ጥናት ክፍል ዋና ሀላፊ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ሰኢድ ዋጋው የጨመረበት ምክንያት “በአለም አቀፍ ደረጃ የጋዜጣ ወረቀት መቶ ፐርሰንት ጨምሮብናል ስለዚህ በምናስገባው ገቢ ግዢ መፈጸም አልቻልንም” ብለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት መጀመርያ ማተሚያ ቤቱ አለም አቀፉን የጋዜጣ ወረቀትን ዋጋ መጨመር ምክንያት በማድረግ ለመንግስት ወረቀትን ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቶ ከቀረጥ ነጻ አስገብቷል፡፡ 

ድርጅቱ  ከዚህ በፊት በኣሳታሚ ደንበኞቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ ወረቀት ላይ ያለን ሁለት እጥፍ ታክስ እንደ ምክንያት ያቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

አማርኛን ጨምሮ በስድስት የተለያዩ የሀገር እና የውጪ ቋንቋዎች በጋዜጣ አትሞ ለህዝብ የሚያቀርበው “መንግስታዊው” የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያሳትማቸው ጋዜጣዎች ላይ ከ 80-100 በመቶ ጭማሪ እንደተደረገበት ለዋዜማ አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ከመንግስት በጀት ሳይጠይቅ በጋዜጣ ሽያጭ እራሱን እያስተዳደረ የቆየ ቢሆንም አሁን በተደረገው የዋጋ ጭማሪ መቀጠል እንደማይችል የድርጅቱ የህትመት አስተዳደር እና ኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ተክሉ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ 

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከብርሃን እና ሰላም የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ቢሆንም አሳትሞ በሚያወጣቸው ጋዜጦች ላይ ግን የዋጋ ጭማሪ አላደረገም፡፡ 

ላለፉት 26 ዓመታት በብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት አሳታሚነት በሁለት ቋንቋዎች ጋዜጣዎችን የሚያሳትመው “ሪፖርተር”  ጋዜጣ የገበያ ክፍል ዋና ሃላፊ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ይማም “እንዲህ ያለው የዋጋ ጭማሪ ለፕሬስ ዘርፉ በአጠቃላይ ትልቅ ስጋት ነው፤ እኛ በገበያው ላይ ቆይተናል  ነገር ግን ዘርፉን መቀላቀል ለሚፈልጉ አዲስ ገቢዎች አያበረታታም” ሲሉ ስጋታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የዋጋ ጭማሪን ተከትሎ ከሚያዚያ 1፤2014 ጀምሮ  15 ብር ይሸጥ የነበረው “ሪፖርተር”  ጋዜጣ ዋጋ ወደ 20 ብር ከፍ እንዲል መደረጉን ነግረውናል  ፡፡

ከተመሰረተ 24 ዓመት የሆነው የቢዝነስ ዜናዎችን ይዞ የሚቀርበው ካፒታል ሳምንታዊ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ ሌላኛው የብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ደንበኛ ነው፡፡  የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ አንድ ጋዜጣ ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ  ላይ 10ብር በመጨመር 20ብር እየሸጠ ይገኛል፡፡

ካፒታል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ግሩም አባተ  “ በኢትዮጵያ ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤትን የሚያክል ግዙፍ የህትመት ድርጅት በመንግስትም በግሉም ዘርፍ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ይህ አሳታሚዎች ምርጫ አልባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

አማራጭ የላቸውም ብለው ነው ይህንን ያህል ጭማሪ ያደረጉብን” ሲሉ  ቅሬታቸውን ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

ጋዜጣን ከአሳታሚ ሚዲያዎች በጅምላ ተረክበው የሚያከፋፍሉ ግለሰቦች የዚህ የዋጋ ጭማሪ ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥርባቸው የማህበረሰቡ ክፍሎች ናቸው፡፡ 

ይህንን ተጽእኖ ከእነዚህ አነስተኛ ገቢ ካላቸው ግለሰቦች ላይ ለማንሳት ወይንም ለማገዝ እንዲረዳ ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ሴንተር (ሪፖርተር ጋዜጣ) ለጋዜጣ አዙዋሪዎቹ በአንድ ጋዜጣ 3ብር ከ50ሳንቲም ኮሚሽን ሲከፍል ጋዜጣውን ደግሞ በ16ብር ከ 50 ሳንቲም እንደሚያስረክባቸው ተረድተናል፡፡

ብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት 40 ገጽ ያለው ጋዜጣ ሲያሳትም ለአንዱ 18ብር ከ 28 ሳንቲም ያትም የነበረ ሲሆን ከሚያዚያ 1፤2014 በኋላ ግን የማተሚያ ዋጋው 28ብር ከ28 ሳንቲም ሆኖል፡፡

ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶች  ዜናዎችን አሳትመን በጋዜጣው ሽያጭ ከምናገኘው ገቢ ይልቅ ጋዜጣው ላይ ምርት እና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁልን ድርጅቶች ዋና የገቢ ምንጮቻቸው እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ 

በህትመት ዋጋ ጭማሪ ስራውን ለማከናወን ፈተና እንደገጠመውና በሚያቀርባቸው ዘገባዎች ምክንያት አስተዋዋቂዎች ማግኘት አለመቻሉን በትናንትናው ዕትሙ ያተተው ፍትሕ መፅሔት  ከሁለት ወራት በፊት 5 ብር ጭማሪ ቢያደርግም አሁን በድጋሚ 5ብር ለመጨመር መገደዱን አስታውቋል። ከብርሃን እና ሰላም ማተሚያ ቤት ውጪ የሚታተመውና ትናንት ለንባብ የበቃው ፍትሕ 30 ብር ሲሸጥ ውሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]