abdi lieyዋዜማ ራዲዮ- በፌደራል መንግስትና በሶማሌ ክልል መካከል ባለፉት ሁለት ቀናት በተደረገ ውይይት የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ መግባባት ላይ መደረሱ ተሰማ።
በፌደራሉ መንግስትና በሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) መካከል ቅዳሜ በስልክ፣ እሁድ ዕለት ደግሞ በፊት ለፊት በተደረገ ውይይት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን ጉዳዮች በንግግር ለመፍታትና የተፈጠረውን ቀውስ ለማረጋጋት የጋራ እርምጃ ለመውሰድ ከመግባባት ተደርሷል።

አሁንም ቢሆን ግን በክልሉ ፕሬዝዳንትና በፌደራሉ መንግስት መካከል መቃቃርና ያለመተማማን ስሜት ጎልቶ ይታያል። ወሳኝ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ላይ ገና ውይይት አልተደረገም።

ውይይቱ የአካባቢውን መረጋጋት በመመለስ ላይ ያተኮረ እንደነበር የነገሩን የመንግስት ከፍተኛ ሚኒስትር ለውዝግቡ መነሻ የሆኑ ፖለቲካዊ ምክንያቶችና የመፍትሄ እርምጃዎችን በዝርዝር ለመነጋገር ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል።
የፌደራሉ መንግስት ወታደሮች በሶማሌ ክልል ቁልፍ አካባቢዎች ተሰማርተው የነበረው የተከሰተውን ቀውስ ለማረጋጋትና ህግ መንግስታዊ ተልዕኮ ለማስፈፀም ያለመ እንደነበር የሚናገሩት የፌደራሉ ባለስልጣናት ለደረሰው ስብዓዊ ቀውስ፣ መፈናቀልና ሞት ተጠያቂ የሆኑ አካላት በህግ ይጠየቃሉ ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ዑመር አብዲ ኢሌ ከሚቃወሟቸው የክልሉ የህዝብ እንደራሴዎችም ጋር ውይይት  እንዲያደርጉ ለማግባባት እየተሞከረ ነው።

“የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ከክልሉ ህዝብና ፖለቲከኞች የገጠማቸውን ተቃውሞና በፌደራል መንግስቱ ገሸሽ ተደርጌያለሁ በሚል ፍራቻ አደገኛ የፖለቲካ ድራማ መተወን ችለዋል”  ይላል በብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት የትንተና ባለሙያና መምህር።
የክልሉ ፕሬዝዳንት ያለፉትን አመታት የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባርን ድል አርድጌያለሁ ቢሉም አማፂ ድርጅቱ እንዳይጠፋ በማድረግ፣ ለአማፂው ድርጅት አመራሮች መረጃ በመስጠትና ገንዘብ በመደጎም በሁለት ቢላ ሲበሉ ከርመዋል።
አብዲ ኢሌ ይህን የሚያደርጉት ለፌደራሉ መንግስት አስፈላጊ ሰው ሆነው ለመቆየት መሆኑን የሚያሰምሩበት የመረጃ ምንጫችን በተለይ ከህወሀት ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ባላቸው ግንኙነት ከስልጣን እነሳለሁ የሚል ብርቱ ስጋት አላቸው ይላል።

“የሶማሌ ክልል ራሱን ከኢትዮጵያ ይገነጥላል” የሚለው ዛቻም የፕሬዝዳንቱን አስፈላጊነት ለማጉላት የተቀነባበረ የፖለቲካ ድራማ ነው። ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ከስልጣን ከተነሳሁ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ህግ ፊት እቀርባለሁ የሚል ስጋት አላቸው።
ቅዳሜ ስለተደረገው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት በስልክ ጥያቄ ብናቀርብም በይፋ ካወጡት መግለጫ ተጨማሪ የሚሰጡት ማብራሪያ አለመኖሩን ነግረውናል።

ወታደራዊ ባለሙያዎች ግን ጣልቃ ገብነቱ በቅጡ ዝግጅት ያልተደረገበትና በማረጋጋትና ድንገተኛ ስራ ላይ ያተኮረ ነበር። የክልሉ ልዩ ሀይል ግን የፌደራል ስራዊቱን ለመውጋት በመሰናዳቱ ስራዊቱ ወደ ካምፑ መመለሱን ይናገራሉ። በህዝብ መኖሪያ አካባቢ ውጊያ ማድረግ ለከፍተኛ ስብዓዊ ጉዳት የሚዳርግ በመሆኑ የመከላከያ ሰራዊቱ ውሳኔ ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎቹ በአድናቆት ይናገራሉ።