Eritrea's President Isaias Afwerki listens to a question during an interview with Reuters in the capital Asmara May 20, 2009. President Afwerki believes the financial crisis is a welcome restructuring of the global economic order and vindication of Eritrea's much-vaunted principles of self-reliance and sustainability. Picture taken May 20, 2009. REUTERS/

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያን የኤርትራን ግንኙነት ለማሻሻል በሁለቱም ሀገሮች በኩል ፈቃደኝነት በተገኘበት በአሁኑ ሰዓት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመነጋገር ወደ አስመራ ያቃናሉ ተብሏል።
ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች እንደሰማችው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በአስመራ ቆይታቸው የድንበር ጉዳይን ጨምሮ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የአለመግባባት ምክንያት ናቸው ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል። የጠቅላይ ሚንስትሩ ጉብኝት ቀን ይፋ አልተደረገም።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ  የኢትዮጵያ ሰራዊት ለኤርትራ እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ከተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም ከባድመ ለቆ የሚወጣበትንና አጠቃላይ ግንኙነትን ማሻሻል ስለሚቻልባቸው መንገዶች ዝርዝር ይነጋገራሉ ተብሏል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጀርሱን የሰላም ስምምነት ያለቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎ ኤርትራ የልዑክን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰኗን አስታውቃለች።

የኤርትራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ እንደሚገባ እየተጠበቀ ሲሆን በቆይታውም ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የአስመራ ጉብኝት ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
እስካሁን ሁለቱ ሀገሮች በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ውይይት ያላደረጉ ሲሆን በውይይቱ ልዩነቶቻቸውንም ሆነ ፍላጎታቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኤርትራ በአዲስ አበባ ለአፍሪቃ ህብረት ተጠሪ ከሆኑ ዲፕሎማቶቿ መካከል አንጋፋውን አምባሳደር አርአያ ደስታን ታሳትፋለች ተብሏል።
ኤርትራ ማናቸውንም ዝርዝር ድርድር ከማድረጓ በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች “ከግዛቴ” መውጣት አለባቸው የሚል ቅድመ ሁኔታ ስታቀርብ መቆየቷ ይታወቃል።
ከሁለቱ ሀገሮች ጀርባ ዩናይትድ ስቴትስ ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትና ሳዑዲ አረቢያ በአግባቢነት ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።