ዋዜማ ራዲዮ- ላለፉት ሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ የስነፅሁፍ ዘርፍ ስመጥር የነበረውና በአወዛጋቢ ፅሁፎቹ የሚታወቀው ደራሲና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረአብ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን ዋዜማ ከቅርብ ቤተሰቦቹ ስምታለች።

ተስፋዬ ያለፉትን ወራት በፅኑ ታሞ ሕክምና ሲከታተል የቆየ ሲሆን ዓርብ ታህሳስ 15 ቀን 2014 በ54 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ቢቢሲ አማርኛ የቅርብ ቤተሰቦቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ ደራሲው በኬንያ ናይሮቢ ህክምና ሲደረግለት ነበር ።

ከኤርትራዊ ወላጆች በቢሾፍቱ ከተማ የተወለደው ተስፋዬ በመጀመሪያ የደርግ ሰራዊት አባል በመሆን ኋላም የኢሕአዴግን የትጥቅ ትግል በመቀላቀል ተሳታፊ ነበር።

ለአስር ዓመታት የሕወሓት አባል የነበረው ተስፋዬ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት “ለኤርትራ መረጃ ያቀብላል” በሚል ውንጀላ በደረሰበት ማዋከብ ኢትዮጵያን ለቆ በስደት በኬንያ በሆላንድና በኤርትራ ይኖር ነበር።

በኢሕአዴግ የመጀመሪያ የስልጣን ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምሪያ ሀላፊ የነበረው ተስፋዬ በኋላ በገዥው ፓርቲ ስር ይታተም የነበረውን “እፎይታ” መፅሔት በዋና አዘጋጅነት መርቷል።

ተስፋዬ ከአስር በላይ የአማርኛ መፅሀፍትን ያበረከተ ሲሆን በተለይ “የቡርቃ ዝምታ” ና “የጋዜጠኛው ማስታወሻ” የተሰኙት መፅሀፍቱ ከፍተኛ ተነባቢነት አትርፈዋል። ተስፋዬ “የቡርቃ ዝምታን” ለፖለቲካዊ ተልዕኮና በኢትዮጵያውያን መካከል መከፋፈል ለመፍጠር ያሴረበት ስራው ነው በሚል ከፍተኛ ተቃውሞና ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]