ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር ተያይዞ በተነሳ ሁከት በግድያና የንብረት ውድመት ወንጀል የተጠረጠሩት ይልቃል ጌትነት እንዲሁም ለሽብርተኞች የሀገር ምስጢር በማወበል የተጠረጠሩ የሕወሐት አመራሮችና ሌሎችም ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 21 2012 ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የዋዜማ ሪፖርተር በችሎቱ ተገኝታ ዘግባለች።


ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ጋር ተያይዞ በተለይ በአዲስ አበባ ከ5 በላይ በሚሆኑ ክፍለ ከተሞች በተፈጠረው ግድያ ና የንብረት ውድመት የተጠረጠሩት የኢትዩጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት ߹ የምክር ቤት አባል አቶ ወንድአለ አስናቀና በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩት አቶ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ላይ የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል። ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮው ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለፊታችን ዓርብ ቀጠሮ ይዟል።

የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን ምርመራዬን ለመጨረስ የተሰጠኝ ጊዜ ስላልበቃኝ ተጨማሪ የ14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ያመለከተ ሲሆን በእስካሁኑ ምርመራ 10 የነበረው የአስክሬን ምርመራ ወደ 14 ከፍ ማለቱን እና የወደመው ንብረት ከ15 ሚሊዩን ብር ወደ 54 ሚለዩን ብር ከፍ ማለቱን ለችሎት አስረድቷል። ከተጠርጣሪዎቹ የተወሰደው የሞባይል እና የኤሌክትሮኒክስ ንብረቶችን ለኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ )እና ለኢትዩ ቴሌ ኮም (ቴሌ) ልኬ መልስ እየጠበኩ ነው ሲል ለችሎት ተናገሯል፡፡


የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የተከሳሾች ተሳትፎ በጥቅል የቀረበ ነው እንጂ በተናጠል አልቀረበም ፖሊስ ድርጊቱ መቼ ߹ የት߹ እንዴት እንደተፈፀመ አልቀረበም ስለዚህ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
“ከተያዝኩ 27 ቀን ሆኖኛል አያያዜ እራሱ ህገወጥ ነው፤ ከምሽቱ 3፡30 ላይ ነው። ከመንግስት መስሪያ ቤት መላሽ ለማምጣት ይህን ያህል ቀን ሊሰጥ አይገባም” ሲሉ ኢንጅነር ይልቃል ለችሎት ተናግረዋል፡፡
ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤት መዝገቡን ተመልክቶ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለ ሀምሌ 24 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል፡፡

የሕወሐት አመራሮች

የሀገር ሚስጠርን ለሽብርተኞች በመስጠት አገሪቷ ላይ ብጥብጥ እና ግርግር እንዲነሳ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩት የአዲስ አበባ የሕውሀት ፅህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ተወልደ ገ/ፃዲቅ ፤ የህግ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሚኒሰተር ዴኤታ አቶ ተስፋለም ይሕደጉ እንዲሁም 2 የፅህፈት ቤቱ ሹፌሮች ለ3 ተኛ ጊዜ አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ ቀርበው ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ግዜ ተጠይቆባቸዋል።


መርማሪ ፖሊስ በአቶ ተስፋለም ይሕደጉ ላይ የተገኘውን መሳሪያ (ክላሽ) ፌደራል ፖሊስም ሆነ አዲስ አበባ ፖሊስ እንደማያውቀው ለችሎት አስረድቶ በመሳሪያው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ቀሪ ምርመራዎችን እንዳልጨረሰ ለችሎት አስረድቷል። ምርማሪ ቡድኑ ከተጠርጣሪዎች የተወሰዱትን የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ምርመራ መልስ በከፊል ያመጣ ሲሆን የሚቀሩ ምርመራዎች መልስ እየጠበኩ ነው ߹ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን መያዝ ߹ ምስክሮችን ቃል መቀበል እና ለባንኮች የላኩትን ደብደቤ መልስ ስላልመጣለት 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል ።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ፖሊስ የጠየቀው የግዜ ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።


የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለሀሙስ ነሀሴ 23 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]