ዋዜማ ራዲዮ-በቅርቡ በአሜሪካን ሀገር በድንገት ከዚህ አለም በሞት የተለየው አቶ አሰፋ ጫቦን ለሀገር ያበረከተውን ኣስተዋፃኦ በመመልከት በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የቀብር ስነ ስርዓቱን ለማካሄድ  ይሁንታ መገኘቱን የቤተስብ የቅርብ ምንጮች ጠቁመዋል።

የቀብር ስነስርዓቱን በትውልድ ሀገሩ ጨንቻ ለማካሄድ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት ቢያደርግም፣ ጋሽ አስፋ ከትውልድ ቀዬው ባሻገር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጅ በመሆኑ የቀብር ስነስርዓቱ የሚገባውን ክብር ለመስጠት  በቤተሰቦቹ የቀረበው ጥያቄ ከመንግስት ቀና ምላሽ አግኝቷል። የጋሽ አሰፋ አስከሬን በመጪው ሀሞስ አዲስ አበባ ይደርሳል።
የቀብር ስነስርዓቱ የኮሚቴ አባል አቶ ዳንኤል ታደሰ እንደነገሩን በጨንቻ ባለፉት ቀናት በሚያስደንቅ ሁኔታ የሀገሬው ህዝብ ጋሽ አሰፋን በሀገሩ ባህል መሰረት ለመሽኘት ካዳር ዳር ቢንቀሳቀስም የቀብሩ ቦታ መቀየር የዝግጅት ለውጥ እንድናደርግ አስገድዶናል ብለዋል።

በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት በመተቸቱ ከሀገር እንደወጣ እንዳይመለስ ተደርጎ ሀሉት አስርት አመታትን በስደት ያሳለፈው ጋሽ አሰፋ ቅዳሜ ዕለት በሀገረ አሜሪካ አሽኛኘት ተደርጎለታል። በቴክሳስ ዳላስ በተደረገው የሽኝት ስነስርዓት ላይ የቀድሞው የኢህአፓው መሪ ክፍሉ ታደሰ እና የደርጉ አምባሳደርና አማካሪ ካሳ ከበደን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተገኝተዋል።
ጋሽ አሰፋ በሀገሩ አንድነት አብዝቶ የሚያምንና ዕምነቱን በአደባባይ የሚናገር አንድበተ ርቱዕና አውራ ብዕረኛም ነበረ። የፖለቲካ ተሳትፎው በስደት እስከተደመደመበት ጊዜ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሞ የሽግግር መንግስት ምስረታ ውስጥ ተሳትፏል። የዘውጌ ፓለቲከኞችን በአደባባይ በመሞገትም ይታወቃል።