ዋዜማ ራዲዮ-

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ጉዳይ ገዳይ ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡

ዉሎ-አዳሬ ብሔራዊ፣ አመሻሼ አብዮታዊ፣

ላየን ባር ቤቴ፣ ቴሌ ባር ግዛቴ…

ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ!! ድሮስ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!

እርስዎ ግን እንዴት ከርመዋል?

አይታዘቡኝ….የሥራዬ ጠባይ ኾኖ ላለው ሸብረክ እላለሁ፡፡ ኪሰ-እርጥባንን ኹሉ ጌታዬ እያልኩ እጠራለሁ፡፡ እጁ ለማይፈታ ግን የእግዜር ሰላምታን እነሳለሁ፡፡ “ገረመው ጠገበ! የእግዜር ሰላምታን ነሳን” እያሉ ስሜን ያጠፋሉ፡፡ እነርሱ ሰርቀው ያመጡትን ሀብት ሁላ እየነሱኝ፡፡

ብቻ ጠባዬ ኾኖ ንፉግ ሰው አልወድም፡፡ እግዜር ጤና፣ ሀብት ንብረት ሰጥቶት ሲያበቃ ንፉግ የሚኾን ሰው ደስታ እንዲርቀው ኾኖ የተረገመ ከንቱ ፍጡር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በዚህ የተነሳ ሰሞኑን ለቆሼ ወገኖች ለመመጽወት ያቅማሙ ደንበኞቼ ኹሉ አስጠልተውኛል፡፡ ሰው እንዴት በገዛ ወገኑ ይጨክናል?

የአገሬ ደናቁርት ሀብታሞች በአንድ ቅዳሜ ምሽት በሸራተኑ ኦፊስ ባር የሚያጠፉት ገንዘብ ቢደመር ለሁሉም የቆሼ ሰዎች ቤት ገዝቶ የኪስ ገንዘብ እንደሚተርፍ እንኳን ካሸሪዋ እኔ ተጋባዡ አውቃለሁ፡፡ ሁሉም ግን ያን ማድረግ አይሹም፡፡ ከዚያ ይልቅ የደነዝ ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ “ለምንድነው ይሄ ሁሉ ኪስ መሬት ባለበት ከተማ እዛ ቆሻሻ ሰፈር ሄደው ቤት የሚሠሩት” እያሉ፡፡ እኒህ ሙት ወቃሾች!

ይሄ ቆሼ ግን ስንቱን ቆሻሻ አሳየን ባካችሁ!

የከል ጭምብል የለበሱ አስመሳዮችን፣ ከንፈር የሚመጡ የድሀ ድሀ ደም መጣቾችን፣ በፈጣሪ ስም የተከለሉ ገንዘብ አምላኪዎችን! ራስ ወዳዶችን! ቆሻሻንና ቆሻሻ ልብስ የለበሰን ሰው አንድ አድርገው የሚመለከቱ ሞጃዎችን…ኸረ ስንቱን!

ዉነቴን እኮ ነው…

እንደው ስግብግብነት ኾኖ እንጂ በዚች አገር የሚገኝ ይሄ ሁሉ ሙልጭልጭ ሀብታም መቶ ሰው ማቋቋም እንዴት ብሎ ያቅተው ነበር? የልጃቸውን ልደት አሜሪካ ዲስኒ ላንድ (Disney Land) የሚያከብሩ እንዴት ከቆሻሻ የተደባለቀ ሕጻን ነፍስ ግድ አትሰጣቸውም?

ከሁሉ ከሁሉ ደግሞ የዚህ የትልቁ ሞኝ ነገር ይባስ!! የዚህ የኢህኤደግ ነገር፡፡ ምድረ ቱልቱላ ካድሬ ሁላ ንፉሮ እየዘገነ ቲቪ መቀረጽ ቁምነገር መስሎታል፡፡ ሰው እንዴት በሰው ሐዘን መሐል ሞገሱን ይሻል?

ቆይ ግን…ዜጎቼን ወደ መካከለኛ ገቢ እያምዘገዘግን ነው ስትሉን አልነበር እንዴ?…እንዴት ነው መቶ የማይሞሉ ተፈናቃዮችን ሕይወት መልክ ለማስያዝ ይሄን ያህል የተንደፋደፋችሁት?!

ውነቴን ነው እኮ!  መቼም እግዜርና ደላላ የማይታዘበው የለም፡፡

ብቻ ይሄ ይሄ ሁሉ ተደማምሮከ ሰሞኑ…ወላ ገዥ፣ ወላ ሻጭ፣ ወላ ኢንቨስተር፣ ወላ ባለሐብት፣ ወላ ከንቲባ፣ ወላ ድርጅት፣ ወላ አርቲስት ሁሉ አስጠልተውኝ ነው የሰነበትኩት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያዊነቴን የረገምኩበት ሳምንትም ይኸው ያለፈው ሳምንት ነው፡፡

እንዴት አልጥላ! በቆሻሻ አየር በከልኳችሁ ብሎ ቢሊዮን ዶላር ካሳ የሚከፍል መንግሥት ባለበት ዓለም እንዴት ከቆሻሻ ጋር ደባልቆ የሚገድል ሥርዓት ይፈጠራል?

ይሄ ምድረ ስስታም የፊንፊኔ ሀብታምስ ቢኾን…

ዱዲ ሳንቲም ለተጎጂዎች ሳይሰጡ በቀለም ያበደ የሐዘን መግለጫ በየጋዜጣው፣ በየሬዲዮው መቶ ሺዎችን ከፍለው ሲያስነግሩ ማየት መስማት በውነትም ያማል፡፡ በሰው እንባ ድርጅታቸውን የሚያስተዋውቁ የመቃብር ላይ ቁማርተኞች ብያቸዋለሁ፡፡

ይሄ ጥላቢስ አርቲስትስ ቢባል…

በቲቪ ቀርቦ የአዞ እንባ ሲያነባ ባይ ጊዜ ራሴን ጠላሁ፡፡ እኒህ የኪነት ሰዎች ደግሞ ከሐዘኑ በላይ ስለለበሱት ጥቁር ሱፍ ማማር እንደተጨነቁ ያስታውቃሉ፡፡ ቆሻሻ ተጭኗቸው ከሞቱት ዜጎች በላይ ነጭ ሸሚዛቸው ቆሻሻ እንዳይነካው የፈሩ ይመስላሉ፡፡ አነጋገራቸው ሁሉ የተጠና ነው፡፡ ድራማ!  ማስመሰል ይበዛዋል፡፡

ምናለ ግን የሐዘን ቃላት ላይ ከሚራቀቁ ካላቸው ቢያካፍሉ፡፡ የኛን አገር ከታፊ አርቲስቶችን አንድ ቃል ጠቅሎ ይገልጣቸዋል፡፡ “ኤ…ጭ!” የሚለው ቃል!

አላሙዲ እንኳ በአቅሙ 40 ሚሊዮን ሲሰጥ!! አላህ በአሁን እድሜህ ላይ 40 ይጨምርልህ!

እርግጥ ነው እሱም ቢኾን በጥሬው ባያደርገው መልካም ነበር፡፡ አንዳንዱ መካሪ አጥቶ ይሳሳታል፡፡ አንዳንዱ መካሪ አብዝቶ ይሳሳታል፡፡ እንደኔ…በጥሬው ከሚሰጥ የዛሬ 25 ዓመት ለሸራተን ተነሺዎች እንዳረገው አልታድ ቁጠባ ቤት ገንብቶ ቢያድል ስሙም ከመቃብር በላይ ለዝንታለም በኖረለት፡፡ ኾኖም ካለመስጠት 40 ሚሊዮንም ቢኾን መስጠት የተሻለ ነው ባይ ነኝ፡፡

እኔምለው…

ሌሎች ሀብታሞች ግን ዝምታን ለምን መረጡ? ከነርሱ ቤት የወጣ ቆሻሻ አይደለም እንዴ ተከምሮ ተከምሮ ሰው የጨረሰ?!! መቼስ ቆሻሻው ከሰማይ አልዘነበ፡፡ ወይ ከድሀ ቤት አልወጣ! ቆሻሻ እኮ ድሀ ቤት ይኖራል እንጂ ከድሀ ቤት አይወጣም፡፡

ጌታዬ! አንድ ነገር ልንገርዎት!?

በቆሼ ጉዳይ እንደ ቤተክህነት አንገቴን ያስደፋኝ የለም፡፡ በቢሊዮን እየሰበሰበች በመቶ ሺህ ስትመጸውት አፈርኩ፡፡ ቀኝህ ሲሰጥ ግራህ አይወቅ እያለች ስታስተምር ኖራ ምነው እዩኝ እዩኝ አበዛች፡፡

ቤተክህነት ለሟቾች ጸሎተ ፍትሀት አደረገች፤ ለተጎጂዎች 2መቶ ሺህ ሰጠች” የሚለውን ዜና ለመጀመርያ ጊዜ ስሰማ የኾነ የቁጥር ስህተት ያለው መስሎኝ ነበር፡፡ እውነቴን ነው፡፡ ምነው ግን ገንዘቡ ቀርቶባት ጸሎተ ፍትሀቱ ላይ ብቻ ብትበረታ! ንፉግነት ከሃይማኖት ተቋም ሲኾን ደግሞ በፍጹም ደስ አይልም፡፡ በፍጹም!! ኸረ እንዲያውም ያስቆጣል!

ምነውሳ…! የአባታችን የአልባሳትና የፕሮቶኮል የወር ወጪ 250 ሺህ ብር በደረሰበት በዚህ ጊዜ ለወገን ከዚያ ያነሰ ገንዘብ ይለገሳል? በየቀኑ ከየአድባራቱ የምንሰማው የምዝበራ ዜና እንኳ ከዚህ  በብዙ እጥፍ የበዛ ነው እኮ፡፡

ምን ነካት ግን ቤተክህነት?

የለም ሆቴሉን ሾላ ገበያን በሦሰት እጥፍ የሚያስከነዳ የገበያ ማዕከል በጉርድ ሾላ ሰሞኑን አይደለም እንዴ የገነባችው፡፡ ለዚያውም የራሷን ቤተክርስቲያን አጥር አፍርሳ! ንግዱ እኮ አሰከራቸው!! በዚህ ከቀጠሉ እኮ የቤተክርስቲያን አገልግሎትን በትርፍ ሰዓት ሊያደርጉት ምንም አልቀራቸውም!!

እንዴ ጌታዬ! ወደ ሲኤምሲ መስመር ሄደዋል ሰሞኑን?

ሰአሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን በንግድ ሱቆቹ መበርከት ስሙን ቀይሮ ሰአሊተ ምህረት ሞል እየተባለ መጠራት ጀመረ እኮ?

ዛሬ የት አስቀደስክ?

ሰዓሊተ ምህረት ሞል፡፡

አያሳፍርም?!

በየከተማው እምብርት ያሉ አድባራትን ወደ መርካቶነት የቀየረች ቤተክህነት ናት እንግዲህ 2 መቶሺ የሰጠች፡፡ ደላላ ባንሆን ይቆጨን ነበር ጌታዬ!

አስፈላጊ ከሆነ እኮ እያንዳንዱ የሰዓሊተ ምህረት ሱቅ ስንት እንደተቸበቸበ መዘክዘክ ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ደብር ስንት እንደቦጨቀም ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ደላላ ባልሆን ይቆጨኝ ነበር!!

እንዴ! ለያንዳንዱ ሱቅ የቁልፍ ብቻ ስድስት ስድስት መቶ ሺህ ብር አይደለም እንዴ ስትሰበስብ የከረመችው? ወርሃዊው ኪራይ አምሳ ሚሊዮን አይደለም እንዴ የተቀበለችው፡፡ ታዲያ በአንድ ጀንበር ሁለት መቶ ሚሊዮን ወደ ኪሷ እያስገባች በቆሻሻ ክምር ዓለሙ ለተደፋበት ምዕመን 2መቶ ሺህ መለገስ አያሳፍርም ጎበዝ?

እናንተ የትርፍ ጊዜ ካድሬ ፈሪሳዊያን!! ምናለ በሙስና የምትሰበስቡትን እንኳ ለወገናችሁ ለግሳችሁ የሀጥያታችሁን ክምር ብታራግፉ!

ኸረ ጎበዝ! መመጽወትን ያስተማረች፣ ቸርነትን የሰበከች፣ እንደምን ገንዘቧን ሰሰተች?

ደላላ ባንሆን ይቆጨን ነበር!! ብዙ እናውቃለን! ብንናገር እናልቃለን!

ደግሞስ…ለደብር አገልጋይ ደመወዝ ጭማሪ የወር ደመወዛችሁን ጉቦ ካልሰጣችሁኝ ብላ በሙስና እስከ ጥምጣሟ የተዘፈቀች ቤተክህነት አይደለችን? የኔ የገረመውን ጉሮሮ የዘጋች፣ ራሷ ድለላ ዉስጥ ገብታ ደላላን በሕዝብ ዘንድ ያስጠላች፣ በማያገባት ገብታ ፖለቲካን የምታቦካ፣ በፈጣሪ ስም ንግዷን የምታጧጧፍ  ቤተ ክህነትም አይደለችን?

እኛ አማኞች እኮ በናንተ ድርጊት አፈርን!!

መምጽወትን ሰብካ ንፉግ የኾነችስ ቤተክህነት አይደለችምን? እንዴት ሁለት መቶ ሺ ሰጠሁ ብላ ለያዥ ለገናዥ ታስቸግራለች? እውነቴን እኮ ነው!

የባልንጀራን ገመና ማውጣት እንዳያስቀስፈን ሰግተን እንጂ ስንቱን ምስጢር እናውቃለን ጎበዝ፡፡ ደላላ ባንሆን ይቆጨን ነበር፡፡

በየምሽቱ ስንቱን ጉድ እያየን ነው ባላየ የምናልፋችሁ!!

ከ4ኪሎ እስከ 5ኪሎ ከኛ ከደላሎች ጋር ተጋፍተው፣ ባለጌ ወንበር ላይ እስከነቀሚሳቸው ፊጥ ብለው፣ ከስብከት መልስ ዉስኪ የሚያስወርዱ ቀሳውስት እንዳሉ ጠፍቶን አይደለም እኮ ዝም ያልነው፡፡ ደላላ ባንሆን ይቆጨን ነበር፡፡ ደላላና እግዜር ሁሉን ይመለከታል!

ንስሀ እንዲገባ የምትወተውቱት አሕዛብ ባይመለከታችሁ፣ ፈጣሪ ይመለከታችኋል፡፡ ፈጣሪ ወዲያው ቁጣውን ባይገልጽ የለም ብላችሁ አትታበዩ፡፡ ሕሊናችሁን አዳምጡ፡፡

እናንተ የአራት ኪሎ ፈሪሳዊያን!! ከቆሼው ክምር እጅግ የሚረዝም የሀጢአት ክምር እናንተ ትከሻ ላይ ይታየኛል፡፡

ገረመው ነኝ ለዋዜማ ራዲዮ