ዋዜማ ራዲዮ- ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሚያዚያ 23 አለም አቀፉ የላብ አደሮች ቀን እየተከበረ በዋለበት ዕለት፣ ማለዳ 4 ሰአት ከሚኖርበት አያት ባቡር ጣቢያ አካባቢ ባልታወቁ የጸጥታ ሃይሎች ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል መወሰዱ የተሰማው በነጋታው ሚያዚያ 24 የዒድ አልፈጥር ዕለት ማህበራዊ ድረገጽ ላይ በተለጠፈ መልዕክት ነበር።
ጋዜጠኛው በጸጥታ ሃይሎች መወሰዱን ያሳወቀው ጠበቃው አዲሱ አልጋው ሲሆን መታሰሩን ማወቅ የቻለውም ከጋዜጠኛው ታናሽ ወንድም በደረሰው የስልክ ጥሪ መሆኑን ለዋዜማ ተናግሯል። ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነው።
ጋዜጠኛው በቅርቡ የተመሰረተው የራያ ልማትና ሰላም ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገለ ነበር። ከመታሰሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከማህበሩ አባላት ጋር ስብሰባ ቢኖርበትም በአስቸኳይ ጉዳይ መገኘት እንዳልቻለ በስልክ እንዳሳወቃቸው የማህበሩ አባላት ለዋዜማ ተናግረዋል። አባላቱ በቀጣዩ ቀን ማለትም ሚያዚያ 23 ረፋድ ላይ የተመካከሩባቸውን ጉዳዮች ለማሳወቅ ቢደውሉም ስልኩ አልነሳ እንዳላቸውም ያስታውሳሉ።
በዓለም ፕሬስ ነጻነት ቀን የጋዜጠኛውን እስር አስመልክቶ ጉዳዩ እንደሚያሳስባቸው ከተናገሩት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን ኮምሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዲሁም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማህበር ይጠቀሳሉ።
በጋዜጠኛው መሰወር ምክንያት ቤተሰብ መጨነቁን በመግለጽ የት አለ? ስትል ዋዜማ የጠየቀቻቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምንጮች ምንም መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የህግ ባለሙያዎች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ በርካታ መብቶቹ እንደተጣሱበት ይናገራሉ። ከተጣሱበት መብቶች መካከልም በህገመንግስቱ አንቀጽ 17 መሰረት ከህግ አግባብ ውጭ መያዙ፣ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ(3) እና በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህጉ አንቀጽ 29 መሰረት በቁጥጥር ስር ከዋለበት ቀን ጀምሮ ባሉት 48 ሰዓታት በአቅራቢያው በሚገኝ ፍርድ ቤት አለመቅረቡ፣ ጠበቃውን እንዲያማክር አለመፈቀዱ፣ ቤተሰብ ጓደኛ ወይንም የሃይማኖት አባት እንዲጎበኘው አለመፈቀዱ በጋዜጠኛው ላይ ከተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ይላሉ።
በስራ ላይ ያለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 28 ንጹስ አንቀጽ (1) ለምንም አላማ ይሁን በሃይል አስገድዶ ሰውን መሰወር ወይም ደብቆና ከእይታ አርቆ በተወሰነ ስፍራ ማስቀመጥን ይከለክላል። ጋዜጠኛው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በቅርብ ቤተሰብም ይሁን በጠበቃ ያለበት አለመታወቁ ሌላኛው ጋዜጠኛው ላይ የተፈጸመ የመብት ጥሰት ተደርጎ ይወሰዳል።
ጋዜጠኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ፣ የክስ ዝርዝር ቀርቦለት፣ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ዋነኛው ጉዳያችን ጋዜጠኛውን ያሰረው አካል የት እንደሰወረው መጠየቅ ነው ይላሉ ሃሳባቸውን ለዋዜማ የሰጡ የህግ ባለሙያዎች።
ጎበዜ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ ሰሜን ወሎ በማቅናት የሰራውን ዘገባ ተከትሎ ከቀድሞ ድርጅቱ ኢሳት ቴሌቪዥን የስንብት ደብዳቤ እንደደረሰው በግል የፌስቡክ ገጹ ማጋራቱ ይታወሳል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ አዲሱ አልጋው ለዋዜማ እንደተናገሩት የፊታችን ግንቦት 5 ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ የመሰረተውን ክስ ተከትሎ ምስክርነት ለመስጠት የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነበረው።
ጋዜጠኛው በተከታታይ ከሰራባቸው ኢሳት ቴሌቪዥን እና የኛ ቴሌቪዥን ከተለያየ በኋላ በዩቲዩብ “የአማራ ድምጽ” የሚል ቻናል በመክፈት መረጃ ሲያደርስ ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በተመሳሳይ ማንነታቸውን ይፋ ባላደረጉ የፀጥታ ሃይሎች ከአዲስ አበባ መኖሪያው ተወስዶ በድብቅ ታስሮ ቆይቷል። ከብዙ የቤተሰብ እንግልትና የህዝብ አቤቱታ በኋላ አሳሪው የኦሮምያ ክልል እንደነበር ታውቋል። ታምራት ነገራ ከወራት የግፍ እስር በቅርቡ በዋስ ተፈቷል።[ዋዜማ ራዲዮ]