Omot

UPDATE- ከአዲስ አበባ በደረሰን መረጃ መሰረት ኦሞት አግዋ ማምሻውን ከእስር ተፈተዋል።

 

ዋዜማ ራዲዮ- ኦሞት አግዋ በዋስ እንዲፈቱ ጠቅላይ ፍርድቤት ቢወስንም ቅሊንጦ እስረኞች ማቆያ የፍርድ ቤቱን የፍቺ ትዕዛዝ እስካሁን አልፈፀመም።

የመሬት መብት ተሟጋች  ኦሞት አግዋ በጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም በ50 ሺህ ብር ዋትስና ከእስር እንዲፈቱ እና አቃቤህግ ያቀረበባቸውን የሽብር ክስ፣ በወንጀል ህጉ  በውጪ ሆነው እንዲከላከሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ቢወስንም እስካሁን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቅሊንጦ እስረኞች ማቆያ የፍቺውን ትዕዛዝ አልፈፀመም።
ኦሞት በጋምቤላ ክልል በፌደራል መንግስት አማካኝነት የጥብቅ ደኖችን ጨምሮ ለኢንቨስተሮች አላግባብ መሬት መቸርቸሩን፣ የክልሉ ነዋሪዎችም ከመሬታቸው ተፈናቅለው የበይ ተመልካች መሆናቸውን  በመቃወም እና የክልሉ ነዋሪዎችን የእሮሮ ድምፅ በማሰማት የሚታወቁ ቢሆንም የፌደራል አቃቤ ህግ ግን የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን)አባል በመሆን ክልሉን ከፌደራል መንግስቱ ለመገንጠል አሲረዋል በሚል ሽብር ክስ መስርቶባቸውል።
ከስድስት ወራት በላይ ያለምንም ክስ በማዕከላዊ የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቆይተው በነሐሴ ወር 2007 የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ኦሞት አግዋ አብረዋቸው የተከሰሱት ሁለት ተከሳሾች አሽኔ ኦስቲን እና ጀማል ኡመር ክሳቸውን መከላከል ሳያስፈልጋቸው ከአንድ አመት ከ ስምንት ወር እስራት በኋላ የከፍተኛው ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19 ችሎት በባለፈው ህዳር 2009 ዓ.ም ወር በነፃ አሰናብቷቸዋል።
ኦሞት አግዋ በከፍተኛው ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበባቸውን ክስ እየተከላከሉ በጎን በኩል የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጪ ሆኖ እንዲከላከሉ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ላቀረቡት ይግባኝ ጠቅላይ ፍርድቤት በ50 ሺህ ብር ዋስትና እንዲወጡ የከፍተኛውን ፍርድቤትን የዋስትና ክልከላ ውሳኔ በመሻር ፈቅዶ ነበር።
ይሁንና ከነሐሴ 2007 ጀምሮ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስራት የተረከባቸው የቅሊንጦ የእስረኞች ማቆያ ግን የጠቅላይ ፍርድቤቱን የፍቺ ትዕዛዝ ወደጎን በማለት ኦሞትን እስካሁን ከእስር አልፈታም።
በጋምቤላ ክልል ውስጥ በተለያዮ የማህበረሰብ ስራዎች ረጅም አገልግሎት በመስጠት በማህበረሰቡ ከፍተኛ እውቅና እና አክብሮት ያላቸው  ኦሞት አግዋ የሶስት ልጆች አባት ናቸው። ኦሞት የደም ብዛት እና በስኳር በሽታ ታማሚ ሲሆኑ በእስር ቤት ቆይታቸው አግባብ የሆነ ህክምና ባለማግኘታቸው የደም ብዛት  ህመማቸው ከቀን ወደቀን እየተባባሰባቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ በፍርድቤት ችሎት ፊት ተናግረዋል።
ኦሞት አግዋ አቃቤህግ ባቀረበባቸው የሽብር ክስ ሳይሆን በወንጅል ህጉ ክሱን እንዲከላከሉ በ ህዳር 2009ዓ.ም ከፍተኛው ፍርድቤት መወሰኑን ተከትሎ በመጪው መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም የመከላከያ ምስክሮች እንዲያሰሙ ፍርድቤቱ ተቀጥሯል።