IMG_0551

የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) ከሀገሪቱ ሀብት እየዘገነ ራሱን ያስፋፋል እንጂ ስባሪ ሳንቲም ወደ መንግስት ካዝና አስገብቶ አያውቅም። እጅ ባጠረው ጊዜ መንግስት ይደጉመዋል፣ የሚተዳደረው በወታደራዊ ህግ ሲሆን ኦዲት አያውቀውም። ይህ በኢትዮዽያ መከላከያ ሰራዊት የቢዝነስ ኢምፓየር ዙሪያ እያቀረብን ካለነው ዘገባ ሶስተኛው ክፍል ነው። በፍሬስብሀት ስዩም የተሰናዳውን ዘገባ ቻላቸው ታደሰ ያቀርበዋል። አድምጡትማ

ማስታወሻ-ቀደም ባሉ ሳምንታት የተላለፉትን የመከላከያ የቢዝነስ ኢምፓየር የተመለከቱ ዘገባዎች ማስፈንጠሪያ (LINK) ከዚህ ገፅ ግርጌ ይገኛል።

በቅርብ እናውቀዋቸዋልን የሚሉ ወገኖች ‹‹ክንፈ ደፋር ነው፤ ምንም የማይሞክረው ነገር የለም›› ሲሉ ሰውዬው አዲስ ነገርን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉትና ለፈጠራ ስራዎች ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት ሲመሰክሩ ይደመጣሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የሰውዬውን ቁጡነትና ኃይለኛነት በመጥቀስ ‹‹ቆራጥ›› እና ‹‹ጀግና›› እያሉ የውዳሴ ካባዎችን ሲደርቡላቸው ይሰማል፡፡ እነዚህ ሁለት የተቃራኑ ባህሪያቸውን ደግሞ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ እስከ ህወሃት ታጋይነት ዘመናቸው ያዳበሯቸው ባህሪያት ሳይሆኑ እንዳልቀረ የሚናገሩ አሉ፡፡ የዚህ ድርብ ባህርያት ባለቤት ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ በግዙፈነቱና በሃብቱ ጡንቻ ተወዳዳሪ የሌለውን በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል “ሜቴክ” (Metal Engineering Corporation/METEC) በመባል የሚታወቀውን የመከላከያ ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከምስረታው ዘመን ጀምሮ እየመሩ ያሉት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ናቸው፡፡

ተቋሙ በመከላከያ ሚንስቴር ስር ሆኖ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትሩ በበላይነት እንደሚመሩት የተቋቋመበት አዋጅ ቢገልጥም አዋጁ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከሰጠው ‹‹የበላይ ተቆጣጣሪነት›› ስልጣን ይልቅ የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ተፅዕኖ እንደሚያይል የተቋሙን አሰራር በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ፡፡

ይህ ድርጅት በመከላከያ ሚንስቴር ስር የብረታብረት ምህንድስና ይሰሩ የነበሩትንና ሌሎች ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የተላለፉለትን የልማት ድርጅቶች በአንድ ተቋም ስር ለማስተዳደርና ሀገራዊ አቅምን ለመፍጠር ተፈልጎ ነበር በ2002 ዓ.ም. በአዋጅ የተቋቋመው፡፡ በመንግስት በተመደበለት 10 ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተመሰረተው ኮርፖሬሽኑ የካፒታል አቅሙንና የሚያስተዳድራቸውን አምራች ድርጅቶች ብዛት እየጨመረና ዓመታዊ ትርፉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ስለመምጣቱም ከድርጅቱ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለአብነትም ያህልም ከሁለት ዓመት በፊት ዓመታዊ ትርፉ 17 ሚሊዮን ብር ያህል የነበርው ድርጅት በዓመቱ ማለትም በ2006 ዓ.ም ትርፉን ወደ 300 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን ስራ አስኪያጁ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት አስታውቀው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ የካፒታል አቅሙም 30 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ይነገራል፡፡ ሲመሰርት አካባቢ ከ20 የማይበልጡ ንዑሥ ድርጅቶችን ያስተዳድር የነበረው ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት 100 ያህል አምራች ድርጅቶችን ያስተዳድራል፡፡

ሜቴክ በቅርቡ በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቁልፍ ማስፈፀሚያ እንዲሆንና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በግንባር ቀደምትነት በመምራት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ እንዲያሸጋግር ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ሆኖም በመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕቅድ ግን የኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋና አካል የሆነው የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፍ ቀድሞ የታለመለትን ግቦች ካላሳኩት ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ስለመያዙ በመንግስት እየተነገረ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው ሜቴክ የንዑስ ዘርፉን በማጎልበት ሀገሪቱን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ ራሱን ከሚገባው በላይ እየለጠጠና እያገዘፈ ስለመሄዱ ግልፅ እየሆነ መጥቷል፡፡

በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች እንደ ‹‹ልህቀት ማዕከል›› (Center of Excellence) እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ለማድረግ ታሰቦ እንደተቋቋመ ይታወቃል፡፡ በኢኮኖሚው ረገድም ከውጪ አገር በብዙ ዶላር እየተገዙ የሚገቡ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሬን ማስቀረትና የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጎልበት ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ መንግስትም በሀገሪቱ ባለ ሁለት አኃዝ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥም የሜቴክን ሚና እንዳለበትና ለብዙ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል በማለት ይኩራራበታል፡፡

በሀገር ገጽታ ግንባታ ረገድም መንግስት ሜቴክን እንደ ቱሪዝም መዳረሻ ወስዶ በተደጋጋሚ ሲያስጎበኝ ይስተዋላል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ የኡጋንዳውን ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒን፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን የጨምሮ የተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶችን፣ የፓርላማ አባላትን እንዲሁም የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞችን በቢሸፍቱና በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ኢንዲስትሪዎቹንና ፋብሪካዎቹን በተደጋጋሚ ሲያስጎበኝ ታይቷል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በመንግሥት ውዳሴና አድናቆት የሚጎርፍለት ኮርፖሬሽኑ በምርቶቹ ጥራት፣ በሕጋዊ አመሠራረቱና ተጠያቂነቱዙሪያ ብዙ ትችቶችና ወቀሳዎችም ይሰነዘሩበታል፡፡ ለመንግስት አወንታዊ አመለካከት ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች ሳይቀሩ ሜቴክ ከአቅሙ በላይ ውጦ እያኘከ መሆኑን ስመሆኑ የሚከራከሩት ታላላቅ የመንግስት ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከተረከበ በኋላ በጊዜ ገደብ ማስረከብ ያለመቻሉንና የስራዎቹም ጥራት መጓደሎችንም በማንሳት ነው፡፡

በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለመንግሥት አስር የስኳር ፋብሪካ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ቢዋዋልም አንዳቸውንም ሳያጠናቅቅ የዕቅዱ ዘመን ተጠናቋል፡፡ በእርግጥ መንግሥት ለእነዚህ ፕሮጀክቶች መገንቢያ የውጭ ብድሮችን ባሰበው መጠን አለማግኘቱ አንዱ ችግር ቢሆንም ሜቴክ ብድር የተገኘላቸውንም ፕሮጄክቶች ማጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ኦሞ ሸለቆ ሊገነቡ ከታሰቡት አምስት የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች መካከል ሜቴክ አንዱን ብቻ ለማጠናቀቅ መቃረቡን የገለጻው ገና በቅርቡ ነው፡፡ የገጠመውን የአቅም ውስንነትም ግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ኩራዝ ሁለት›› እና ‹‹ኩራዝ ሦስት›› የተባሉት ሁለት ፋብሪካዎች በቅርቡ ከሜቴክ ተነጥቀው ለቻይና ኩባንያዎች ተሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የድንጋይ ከሰልና ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ቢረከብም በተዋዋለበት የጊዜ ገደብ ሳያጠናቅቃቸው በርካታ ወራት ነጉደዋል፡፡

በሌላ በኩልም ሜቴክ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለሕዝብ ትራንስፖርት የሚያገለግሉ ከ500 በላይ አውቶብሶችን ገጣምሞ ለማቅረብ ቢዋዋልም በተፈለገው ፍጥነት አጠናቆ ማቅረብ ባለመቻሉ አስተዳድሩ በቅርቡ ከውጭ ሀገር ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት ውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምርት ጥራት በኩልም የሚታዩ ችግሮች ኮርፖሬሽኑን ከመስተዳድሩ ጋር ውዝግብ ውስጥ ስገባው ሲሆን በተለይ ለአንበሳ አውቶብስ ድርጅት የገጣጠማቸው ተሽከርካሪዎች የፍሬን ችግሮች ያሉባቸው መሆናቸውን መስተዳድሩ ይወቅሳል፡፡ ሆኖም ግን የሜቴክ ሥራ አስኪያጅ ስለ ጉዳዩ ፓርላማው ውስጥ ሲጠየቁ በሰጡት መልስ ‹‹እኛ የገጣጠምናቸው አውቶብሶች የፍሬን ችግር የላቸውም፡፡ ችግሩ የእኛ አውቶብሶች አሽከርካሪዎቹ ቀድሞ ሲያሽከረክሯቸው ከነበሩት የተለየ ቴክኖሎጂ ስላላቸው ብቻ የተከሰተ ችግር ነው›› በማለት አስተባብለዋል፡፡

ይኼው ኮርፖሬሽን ከሚያከናውናቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ ነገር ግን የግድቡን ግንባታ የሚያከናውነው የኢጣልያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን በሜቴክ የሥራ ፍጥነት ደስተኛ አለመሆኑን የዋዜማ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ ግድቡ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 700 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደነበረበት በእቅዱ ቢቀመጥም ዕቅዱ ላለመሳካቱ ሳሊኒ ሜቴክን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ምንጮቻችን ይጠቁማሉ፡፡

የጥራት ችግር ኮርፖሬሽኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋርም ውዝግብ ውስጥ ከቶት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኤሌክትክ ሃይል ሜቴክ ባመረታቸው ትራንስፎርመሮች ላይ ከፍተኛ የጥራት ችግሮች እንዳባቸው ቢያነሳም ሜቴክ በበኩሉ ደንበኛዬ ‹‹ያመረትኩትን ትራንስፎርመር ጥራት የመመርመር ብቃት የለውም›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ ደንበኛዬ ለምርቱ ያወጣሁትን 380 ሚሊዮን ብር ይክፈለኝ ሲልም ክስ መስርቶ ጉዳዩ እስከ ፓርላማው አፈጉባዔና ጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት ድረስ ደርሶ የነበረ ሲሆን መንግስትም ገንዘቡ ለሜቴክ እንዲከፈል ትዕዛዝ በመስጠቱ ተከፍሎታል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ለሜቴክ ከገደብ ያለፈ ድጋፍ ስለሚያደርግለት ብቻ ከምርት በፊት የቅድመ ገበያ አዋጭነት ጥናት፣ የምርት ተጠቃሚዎችን የመግዛት አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአመራረት በኩል ያሉበትን ችግሮች እንዳይቀርፍ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ሜቴክ ባለፉት ሁለት ዓመታት የአርሶ አደሮችን የማምረት አቅም ለመሳደግ ታስቦ በገፍ ብዙ ሺሕ ትራክተሮችንና ባለሁለት ተሽከርካሪ ጎማ ያላቸውን የማረሻ መሣሪያዎችን አምርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የአብዛኛው አርሶ አደር አቅም አነስተኛ በመሆኑ ምርቶቹን ገዝቶ ለመጠቀም ውድ ስለሆነበት ኮርፖሬሽኑ ያመረታቸውን ወደ 20 ሺሕ የሚጠጉ ትራክተሮችና የማረሻ መሣሪያዎች በመጋዘን ለማቆየት መገደዱን ሃላፊዎቹ ሲገልፁ ይሰማሉ፡፡

የሜቴክ ዘርፎች በመለጠጣቸው በግሉ ዘርፍ ላይም ጡንቻውን ማሳረፉን የሚጠቅሱ በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ በተሽከርካሪ መገጣጠምና መለዋወጫ ዕቃዎች ምርት ላይ ተሰማርተው የነበሩ የግል ኩባንያዎች ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ በተለይ በአገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ የመንግሥት ድርጅቶች የሜቴክን ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲገዙ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እያስገደደ በመሆኑ የነጻ ገበያ ውድድሩን እየጎዳው እንደሆነ ታዛቢዎች በአስረጂነት ያነሳሉ፡፡ ‹‹ድርጅቱ ተሽከርካሪ ወይም ማሽነሪ ማምረቱ ቢበረታታም አነስተኛዋን ቡሎን ሳይቀር በማምረት የጉልበት ሽሚያ ውስጥ ገብቷል›› በማለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ባለሃብት ሰሞኑን ለዋዜማ ሬዲዮ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬን ለመቆጠብ እንዲያስችል ተብሎ ቢመሰረትም ሜቴክ ስር የሰደደ የእውቀት ውስንነት ስለሚታይበት ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል ከውጪ አገራት ባለሙያዎችን ማስገባቱ ከሚነሱበት ትችቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከክፍያውም በላይ ሙያተኞቹ ቆይታቸውን አጠናቀው እስኪሄዱ ድረስ የሚያወጣው የሆቴልና ተያያዥ ወጪዎች አሳሳቢ ሆኖበታል፡፡ ለዚህም ነበር ታላላቆቹን ኢምፔሪያልና ሪቬራ ሆቴሎችን ለእንግዳ ማረፊያ እንዲሆኑ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የገዛው፡፡ ሆኖ ግን ሆቴሎቹ ከሁለት ዓመት በላይ ስራ ፈትተው ተቀምጠዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑን ‹‹የልማት ድርጅትነት›› ጥያቄ ውስጥ የሚከቱና የወታደራዊ ተቋሙነቱን ብቻ የሚያሳዩ እውነታዎች ፈጠው እየወጡ ነው፡፡ ለምሳሌ የሜቴክ ሰራተኞች ከጦር ሰራዊቱ የተውጣጡና በመከላከያ ሚንስቴር ህግ ብቻ የሚታዳደሩ በመሆናቸው ከልማት ድርጅትነት ይልቅ ወታደራዊ ኢንዱስትሪነቱ እንደገዝፍ ያሳያል፡፡ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ በፓርላማውም ሳይቀር ‹‹የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች በሀገሪቱ የሰራተኛ ህግ መሰረት ካልተዳደሩ የልማት ድርጅትነቱ ምኑ ላይ ነው?›› የሚል ጥያቄ ለጄኔራል ክንፈ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም በሰጡት መልስ ‹‹ተቋሙ የጦር መሳሪያን ጨምሮ ለሀገር ደህንነት መጠበቂያ አጋዥ መሳሪየዎችን የሚያመርት ተቋም ስለሆነ ሠራተኞችም ወታደሮች ናቸው፡፡ ስራው ደግሞ በባህሪው ከሀገር ደህንነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ፣ ሰራቶኞቹን ከሰራተኛ አዋጁ ይልቅ በወታደራዊ ዲስፕሊን መመራት ስላለበት ነው›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

የሜቴክን የ‹‹ልማት ድርጅትነት›› ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው ሌላው ጉዳይ የቁጥጥርና ተጠያቂነት ስርዓቱ እንደሆነ የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ከመንግስት በጀት የሚመደብለት መስሪያ ቤት በሀገሪቱ ህግ መሰረት በኦዲት፣ በስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ህግ እንዲሁም በመንግስት ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግበት ቢደነገግም ሜቴክ ግን ከዚህ ነፃ ነው፡፡

ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሜቴክ በየዓመቱ ከሚያስገባው ትርፍ ምንም ዓይነት ገንዘብ ወደ መንግስት ግምጃ ቤት አለማስገባቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን በማንኛውም ጊዜ ሜቴክ ተጨማሪ በጀት ካስፈለገው በፓርላማ ተፈቅዶ ማግኘት እንዲችል በህግ ተፈቅዶለታል፡፡ በትርፋማ ስራ ለተሰማራ ድርጅት ይህንን መብት መፍቀድ ተቋማዊና ህጋዊ ተጠያቂነትን አደጋ እንደጣለው የሚያነሱ በለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለዚህም ይሆናል ሜቴክ በፈለገው ዘርፍ ሁሉ ለመሰማራት ያስቻለው፡፡ ከላይ በተነሱት አንገብጋቢ ጉዳዮች ዙሪያም ጠንከር ያለ ጥያቄ ሳይነሳበት እነሆ የ30 ቢሊዮን ብር ካፒታል ባለቤት መሆኑን በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ መንግስትም ሜቴክ ‹‹የአገር አለኝታ›› ስለመሆኑ ለህዝቡ መለፈፉን የሚያቋርጥ አይመስልም፡፡

ቀደም ባሉ ሳምንታት የተላለፉትን የመከላከያ የቢዝነስ ኢምፓየር የተመለከቱ ዘገባዎች ማስፈንጠሪያ LINK below
ሰራዊቱ ለመፈንቅለ መንግስት ሊቋምጥ ይችላል-http://wazemaradio.com/?p=877
የሰራዊቱ የቢዝነስ ኢምፓየርና መጪው ጊዜ (ክፍል ሁለት)-http://wazemaradio.com/?p=903