ዋዜማ ራዲዮ- በሀገሪቱ ያሉ የንግድ ባንኮች ያለባቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ሳብያ ወደተለያዩ ሀገራት ለሚጓዙ መንገደኞች የሚሸጡት የውጭ ምንዛሬንም ማቅረብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ዋዜማ ራዲዮ ባደረገችው ቅኝት መረዳት ችላለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ንግድ ባንኮች ለተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተለያዩ ሀገራት ለሚሄዱ ግለሰብ ደንበኞቻቸው እንደየባንኮቹ አሰራር ከ200 እስከ 5000 የአሜሪካን ዶላር ይሸጡላቸዋል።የሌሎች ሀገራት ገንዘቦችንም በተለያየ መልኩ ያቀርቡላቸዋል።

 ከሰሞኑ ደግሞ በምንዛሬ እጥረት ምክንያት በአንጻሩ አነስተኛ ለሚባለው የውጭ ሀገር ጉዞም ምንዛሬ ለመስጠት ፈተና እየሆነባቸው ነው። ዋዜማ ራዲዮ እንዳረጋገጠችው ሁለት ባንኮች ለጉዞ ምንዛሬ እንዳይሸጡ ለቅርንጫፎቻቸው ከየፕሬዚዳንቶቻቸው ታዘዋል።

እጃችን የገባው የህብረት ባንክ ደብዳቤ ከሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 አ.ም ጀምሮ ቅርንጫፎች ለጊዜው ለውጭ ሀገራት ተጓዦች የውጭ ምንዛሬ እንዳይሸጡ አዟል። በባንኩ ፕሬዚዳንት ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንዳመለከተው ፣ ባንኩ ከባድ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ውስጥ ገብቷል።

የውጭ ምንዛሬ አስቀማጮች ዲያስፖራዎች ሙሉ ለሙሉ ምንዛሬያቸውን ምርቶች ለማስገባት እየተጠቀሙበት በመሆኑና ፣ ባንኩ በወር ውስጥ ካገኘው ምንዛሬ 30 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ ለመሸጥ በመገደዱም እጥረት ውስጥ ስለገባ ለባንኩ ዋና ዋና ደንበኞች ካልሆነ በስተቀር ለውጭ ጉዞ ምንዛሬ እንዳይሸጡ ታዟልም ይላል ደብዳቤው።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ባደረግነው ምልከታም የውጭ ተጓዦች የትኛውንም ያክል መጠን የውጭ ምንዛሬ ቢጠይቁም ከ200 የአሜሪካ ዶላር በላይ እየተፈቀደላቸው አለመሆኑንም አውቀናል።

ከግል ባንኮች በግዝፈቱ የሚታወቀው ዳሸን ባንክ  ፣ ከሳምንታት በፊት ለውጭ ሀገራት ተጓዦች እስከ አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር መስጠት ሲፈቅድ የቆየ ቢሆንም ለሁሉም ቅርንጫፎች ለውጭ ተጓዦች ከ400 የአሜሪካ ዶላር በላይ እንዳይሰጡ ማዘዙን ከምንጮቻችን እና በባንኩ ቅርንጫፎች ባደረግነው ቅኝት ተረድተናል።

አንዳንድ ባንኮች ደግሞ ለህክምና ጉዞም ጭምር በዚህ ሳምንት የቀጠሯቸውን ደንበኞቻቸውን እንዴት እንደሚያስተናግዱም ግራ ገብቷቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሀገሪቱ ማስገኘታቸውን እና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችትም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ተናገረው ነበር። የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ያመጡትን ምንዛሬ በድጋሜ ካላመጡ ከነዳጅና መድሀኒት ውጭ ምንዛሬን ማቅረብ እንደሚከብድ መግለጻቸው ይታወሳል።

 ሆኖም በበጀት አመቱ ስምንት ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘው 1.64 ቢሊየን ዶላር ነው። ይህም በሁሉም መመዘኛ ዝቅተኛ በመሆኑ ምንዛሬን ለማቅረብ ዋነኛ የሆነው መንገድ አሁንም በብዙ ችግር የተሞላ ነው። የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጉዳይ አሁንም ግዙፉ የሀገሪቱ ችግር ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]