Bole Sub City
Bole Sub City

በሳምንት ረቡዕና ቅዳሜ የሚታተመው ‹‹አዲስ ልሳን›› ጋዜጣ ከታላቅ ወንድሙ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ በቁመት ካልሆነ በይዘት እምብዛምም ልዩነት የለውም፡፡ ኾኖም እንደ ቆሎ የሚቸበቸበውን የሸገር መሬት ጉዳይ በብቸኝነት የሚያውጀው ታናሽየው ‹‹አዲስ ልሳን››  በመሆኑ ጋዜጣው የመሬት ቀበኛ ባለሀብቶች ዘንድ ልዩ ሞገስ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

የሚሸጡ ቁራሽ መሬቶችን ዝርዝር ይዘው የሚወጡ የአዲስ ልሳን እትሞች ሁልጊዜም ቢሆን በሰዓታት ጊዜ ዉስጥ ከገበያ እልም ብለው ያልቃሉ፡፡ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ የወሰዱ የጎዳና ልጆች የጨረታ ዝርዝር የያዙ ገጾችን ለይተው በፎቶ ኮፒ ካባዙ በኋላ በዋና ዋና የከተማዋ አደባባዮች ይቸረችራሉ፡፡ ለገሀር፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ መገናኛ…፡፡

ካሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ የታየውም ይኸው ነው፡፡ ‹‹መሬት ሦስሦሰት ብር›› እያሉ የሚጣሩ ታዳጊ ልጆች በማዘጋጃ ቤት የታችኛው በር በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ ፒያሳ የአላሙዲንን አጥር ተደግፈው ራሳቸውን የሚጦሩ ጎልማሶችም በዚሁ ሥራ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ የ4ኪሎ የኪራይ ጋዜጣ አስነባቢዎችም በአጋጣሚው ተጠቅመዉ ገቢ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በመሬት ማሻሻጡ ላይ የሚሳተፉት ዜጎች እንዲህ መልከ ብዙ ድኩማን ቢሆኑም መሬቱን ጠቅልለው የሚገዙት ግን ጥቂት ባለፀጎችና ቤተሰቦቻቸው ብቻ ናቸው፡፡

የቦሌ መሬት

አዲስ ልሳን ባለፈው ሳምንት ዕትሙ 231 ቦታዎች ለወርኀዊው የሊዝ ገበያ መቅረባቸውን ይፋ አደረገ፡፡ ከነዚህ ውስጥ 141ዱ የሚገኙት በቦሌ ክፍለከተማ በመሆኑ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት ለመሳብ ችሏል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ምሥራቃዊ ድንበሩ የሚያበቃው በተለምዶ ‹‹አያት ፀበል›› በሚባል ቦታ ነው፡፡ ለሊዝ ጨረታ የቀረቡት ሁሉም ቁራሽ መሬቶች የሚገኙትም በዚሁ ስፍራ ነበር፡፡ ለጨረታ የቀረቡት ሁሉም ቦታዎች በዚህ ስፍራ እጅብ ብለው መገኘታቸው የ20ኛው ዙር አዲስ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በአንድ ቦታ እጅብ ብለው የሚገኙ መሬቶች እምብዛምም በአንድ ጨረታ ላይ በአንድ ጊዜ ለተጫራች አይቀርቡም፡፡ የተለመደው አሰራር በተለያየ ሰፈር ተበታትነው የሚገኙ ጥቂት ኪስ ቦታዎችን በተናጥል በተለያየ ዙር ለጨረታ  ማቅረብ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ቦታዎቹ ዐይን እንዲበዛባቸው፣ በተጫራቾች ልዩ ትኩረት እንዲያድርባቸውና እንዲሁም ለቦታዎቹ ከፍተኛ ፍላጎትን እንዲያሳድሩ ስለሚያስገድድ የመሬት ዋጋ የማናር አሉታዊ አጋጣሚን ሲፈጥር ሰንብቷል፡፡

የሊዝ ጽሕፈት ቤት በዚህኛው ዙር የቦሌን መሬት በአንድ ሰፈር ለዚያውም በአንድ ቦታ እጅብ ብለው የሚገኙ እንዲሆኑ ማድረጉ የሊዝ ዋጋን ሊያረግብ ይችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አሳድሮ ነበር፡፡ ሆኖም የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ለጨረታ የቀረቡት መሬቶች በትክክል የሚገኙበትን ቦታ ለመጠቆም ያህል የሲኤምሲንና የአያት አደባባዮችን አልፎ በተለምዶ አያት ፀበል የሚባል ቦታ ለመድረስ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩ በስተግራ የሚታይ አውላላ ሜዳ ነው፡፡ ይህ ስፍራ ከአዲስ መንደር ሪልስቴት አለፍ ብሎ አዲሱ ባልደራስ ፈረስ መጋለቢያ ግቢ አጠገብ የሚገኝ ሲሆን 141ዱም ቦታዎች የፈረስ መጋለቢያውን አጥር ታከው የሚገኙ ናቸው፡፡ ወይም ደግሞ ለመቄዶኒያ የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር ከተሰጠው 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ የሚጎራበቱ ሥፍራዎች ናቸው፡፡ በአካባቢው ስፖርት ኮሚሽን ግቢና ፈረስ መጋለቢያ ግቢ ካልሆነ በቀር በቅርብ ርቀት የሚታይ ምንም አይነት ግንባታ የለም፡፡ አካባቢው ታርሶ ያልተዘራበት መሬት እንደሆነ አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡ የአካባቢው ሰዎች ለዚህ ዘጋቢ እንደነገሩት መሬቱ ጥቂት የኦሮሚያ ገበሬዎች ለዓመታት እያረሱ ይተዳደሩበት የነበረ ማሳቸውነው፡፡ መሬት ሸማቾች ቦታውን ሊጎበኙ መጥተው በነበረበትም ወቅት ይህነኑ የሚያረጋግጥ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ባለፈው ማክሰኞ ስፍራው በተጫራች ባለሐብቶች በሚጎበኝበት ወቅት ጥቂት የገበሬ ልጆች ከአስጎብኚዎች ጋር ለፀብ የመጋበዝ ሁኔታን ያሳዩ እንደነበረ የዚህ ዜና ዘጋቢ መታዘብ ችሏል፡፡ ኾኖም ከክፍለ ከተማው የተወከሉ አስጎብኚዎች  ወደ እርሻ መሬቱ ሳይዘልቁ ፈንጠር ብለው በመቆም ቦታዎቹን በአመልካች ጣት እየጠቆሙ ማስጎብኘት በመምረጣቸው ሁኔታው ወደ ከፋ ግጭት ሳያድግ ረግቧል፡፡

የመሬት ጨረታ በማዕከል ደረጃ የሚወጣ ሲሆን መሬቱን የማስጎብኘት ኃላፊነት ግን ሁልጊዜም በክፍለከተሞች ላይ የተጣለ ኃላፊነት ነው፡፡ ክፍለከተሞች የራሳቸውን የጉብኝት ፕሮግራም በማዘጋጀት እጩ ተጫራቾችን በተሸከርካሪ በማስከተል ስፍራዎቹን በሦስት ዙር አመላክተዋል፡፡ በጉብኝት መርሀግብሩ ወቅት መሳተፍ ያልቻሉ ባለሀብቶች ግን ለክፍለከተማው ሰራተኞች ጉርሻ እየሰጡ እስከ ሰኞ ረፋድ ድረስ ቦታውን መመልከት ችለው ነበር፡፡

ቅይጥ ወይስ መኖርያ?

በዚህ 20ኛው ዙር ሽያጭ ላይ በቦሌ ክፍለከተማ የቀረቡት መሬቶች ሙሉ በሙሉ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሲሆኑ አንድም ለመኖርያ ቤት መስሪያ የሚኾን መሬት ለጨረታ አልቀረበም፡፡ ይህ በሁለት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ አንደኛው መላምት አካባቢውን ሰንጥቆ የሚያልፍ ከለገጣፎ ተነስቶ ከደብረዘይት መንገድ የሚገጥም ባለ 50 ሜትር የፍጥነት መንገድ በመቀየሱና በዚህም ምክንያት አካባቢው ወደፊት ከመኖርያነት ይልቅ ለቅይጥ አገልግሎት የሚመች ተደርጎ መታሰቡ ሲሆን ሁለተኛው መላምት መስተዳደሩ የገቢ እጥረት ስላጋጠመው ቦታዎቹን ለመኖርያነት ቤት መስሪያነት ቢያውላቸው ተጫራቾች ከሚከፍሉት ቅድመ ክፍያ የሚያገኘውን ገንዘብ ዝቅ ስለሚያደርግበት ነው የሚል ነው፡፡ በሊዝ አዋጁ የመኖርያ ቤት መስሪያ ቦታ አሸናፊዎች ቅድመ ክፍያ የሚፈጽሙት ያሸነፉበትን የገንዘብ መጠን 10 በመቶ ብቻ ሲሆን ለቅይጥ ግንባታ የታለሙ መሬቶችን የሚገዙ አሽናፊዎች ግን የዚህን እጥፍ እንዲከፍሉ ያስገድዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለቅይጥ አገልግሎት የታቀዱ ቦታዎች ለሚገዙ ግለሰቦች ለመኖርያና ለንግድ ስራ የሚሆኑ ሕንፃዎችን በተሰጠው ይዞታ ላይ አመጣጥነው እንዲገነቡ ያስገድዳል፡፡

በዚህ ስፍራ ከቀረቡት 141 ቦታዎች ውስጥ ከፍተኛ ስፋት የነበረው መሬት 640 ካሬ ሜትር ስኩዌር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 244 ካሬ ሜትር ነው፡፡ በሁሉም ቦታዎች ላይ እንዲገነቡ  የሚጠበቅባቸው የሕንጻ ከፍታ ግን ከወለል በላይ 2 ፎቅ ብቻ ነው፡፡

በስንት ተሸጡ?

በዚህ 20ኛው ዙር ጨረታ ላይ የነበሩ ጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ መመናመን በመሬት ዋጋ መናር ምክንያት ብዙዎች ተስፋ እየቆረጡ መምጣታቸውን የሚያመላክት ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ ለአንዳንዶችም ሁኔታው በአነስተኛ ዋጋ የሚሸጡ መሬቶች እንደሚኖሩ ፍንጭ የሰጠ አጋጣሚ ተደርጎም ተወስዶ ነበር፡፡ ኾኖም ግን ይህ ግምት ግምት ብቻ ኾኖ ቀርቷል።

በዚህ ዙር ለአንድ ካሬ ሜትር የተሰጠው ከፍተኛ ዋጋ 31ሺ 500 ብር ሲሆን ይህም አቶ አስፋው በተባሉ ግለሰብ አንድ ጥግ ላይ ለምትገኝ 398 ካሬ ስፋት ላላት አነስተኛ ቦታ የቀረበ ዋጋ ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ዋጋ ተደርጎ ይታሰብ እንጂ ከ20 የማያንሱ ተወዳዳሪዎች ለተመሳሳይ ቦታዎች ከዚህ የማያንስ ዋጋ አቅርበው ነበር፡፡ ለምሳሌ አቶ ስንታየሁ ሀበን የተባሉ ግለሰብ ለዚሁ መሬት አጎራባች ለሆነ ስፍራ በካሬ ሜትር 30ሺ ብር በማቅረብ 2ኛውን የዙሩን ሪከርድ የያዙ ሲሆን ከ25ሺ ብር በላይ ለካሬ ሜትር ያቀረቡ ተጫራቾች በቁጥር በዛ ብለው ታይተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ በጨረታው ተሸናፊ የነበሩ ተወዳዳዎች ለካሬ ሜትር ያቀረቡት አማካይ ዋጋ ከ12ሺ እስከ 15ሺ ብር የሚገመት ነበር፡፡

በግለሰብ እጅ የሚዘዋወር ጥሬ ብር በሌለበት ሁኔታ እንዲህ የተጋነኑ ዋጋዎች ለጨረታ መቅረባቸው ለብዙዎች ጥያቄ መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ የአዲስ አበባ መሬት ከዚህ በኋላ መቼም ቢሆን ወደ ጤናማ የጨረታ ዉድድር ሊመለስ አይችልም የሚል ግምትም እንዲወሰድ ምክንያት የሆነ ይመስላል፡፡

ለምን የተጋነኑ ዋጋዎች ይቀርባሉ?

ተወዳዳሪዎች ለአዲስ አበባ መሬት ለምን የተጋነነ ዋጋን ያቀርባሉ የሚለው ጥያቄ ለብዙዎች አሁንም ትንግርት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ “ለአንድ በከተማዋ ጠረፍ ላይ ለሚገኝ 500 ካሬ ቦታ በአንዲት ካሬ ሜትር 31ሺ ብር ማቅረብ በማንኛውም የሂሳብ ስሌት ቢሆን አዋጪ ሊሆን አይችልም” ይላሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች፡፡ ይህ ማለት አሸናፊው ግለሰብ አያት የሚገኘውን 5መቶ ካሬ ቦታ የገዛበት ዋጋ 15 ሚሊዮን ብር ሲሆን የዚህን ዋጋ 20 በመቶ ወይንም 3ሚሊዮን ብር ስሙ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ በወጣ በ10 ቀናት ዉስጥ ለመስተዳደሩ ገቢ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ቀሪውን በ60 ዓመት እንዲከፍል የሚፈቀድ ቢሆንም ጫን ያለ የወለድ መጠን ለመክፈል ይገደዳል፡፡

መሬት በማሻሻጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚናገሩት ሊዝ ከወጣበት ስፍራ ብዙም ሳይርቅ በአያትና በአካባቢው  ከዚሁ መሬት ተመሳሳይ የኾነ ባዶ ቦታ ከ4 እስከ 5 ሚሊዮን ብር መግዛት ይቻላል፡፡ በሌላ ቋንቋ በዚህ የተጋነነ የሊዝ ዋጋ ያሸነፈው ግለሰብ በጥቂት ዓመታት ዉስጥ ለሊዝ የሚከፍለውን ወለድ ለመሬት ግዢ ቢያውለው አምስት የተለያዩ ተመሳሳይ ስፋት ያላቸው መሬቶችን በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች መግዛት ያስችለዋል፡፡

ከዚህ ስሌት በመነሳት ነው እንግዲህ ብዙዎች ገንዘባቸውን ባልተገባ መንገድ መሬት ግዢ ላይ የሚያዉሉ ግለሰቦችን ጤንነት እንዲጠራጠሩ የሚገደዱት፡፡ ሌሎች ለጉዳዩ የቀረቡ ግለሰቦች በበኩላቸው ይህ አይነቱ ክስተት ጤናማ የሆነ ኢኮኖሚና ንግድ በራቀው አገር የሚታይ የተለመደ ደዌ ነው፡፡

ለ141ዱ የቦሌ ክፍለ ከተማ መሬቶች ከአንድ ሺ በላይ የጨረታ ተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡ በጨረታው በዝቅተኛ ዋጋ በማሸነፍ ቦታ የገዙት ግለሰብ አቶ ዳንኤል አሰፋ ሲሆኑ ለአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ያቀረቡት የገንዘብ መጠን 6ሺ 6መቶ ስድሳ ብር ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ መሬት ለካሬ ሜትር 15ሺህ ብር አቅርበው ካሸነፉት ግለሰብ ቦታ ጋር የቅርብ ተጎራባች መሆኑ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ አድርጎት ነበር፡፡

የመሬት ችብቻቦው በመጪዎቹም  ሁለት ቀናት ቀጥሎ ይዉላል፡፡