social media icons

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በድረገጽ የሚቀርቡ ጽሑፎች ያላቸውን የጥላቻ ንግግር  (hate speech) ባህርይና የጥላቻ ንግግሮቹን መጠን ጉዳዩ ያደረገው በአዲስ አበባና በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥምረት የተሰራው ጥናት ውጤት ታትሞ ለንባብ በቅቷል። ይህም የጥናት ውጤት የድረገጽ አጥቃቀምን በተመለከተ ገደብ የሚያስቀምጥ ፖሊሲና ሕግ ለማውጣት ለሚጣደፈው የኢትዮጵያ መንግስት የሚጠቁመው ነገር የንግግር ነፃነትን ለመገደብ የሚያበቃ እዚህ ግባ የሚባል የአደገኛ ንግግር (dangerous speech) ተግዳሮት አለመኖሩን ነው።

 [የመዝገቡ ሀይሉ የድምፅ ዘገባን እዚህ ያድምጡ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

“መቻቻል” በሚል አጠቃላይ ርዕስ የቀረበው ይህ ጥናት ከ 2007 ምርጫ ጀምሮ ለሁለት ዓመት የነበረውን የማኅበራዊ ድረ ገጾች የፖለቲካ ውይይትና ክርክር የሚዳስስ ነበር። ጥናቱ ለ ሁለት ዓመት በቆየው በዚሁ የጥናት ጊዜ ውስጥ የነበሩትን ፖለቲካን፥ ሐይማኖትንና ብሔርን የተመለከቱ የማኅበራዊ ድረገጽ ውይይቶች የዳሰሰ ነበር። የጥናቱም ትኩረት በሶስት ክፍል የተመደቡ የማኅበራዊ ድረገጽ አስተያየቶችና ንግግሮች ነበሩ። ተሳዳቢ(offensive) ፥ ጥላቻ አዘልና (hateful)፥ አደገኛ (dangerous) በሚል መደብ የተመደቡትን እነዚህን አስተያየቶች የገመገመው ጥናት አደገኛ በሚል ክፍል ሊመደብ የሚችለው የፌስቡክ አስተያየት መጠን በመንግስት እንደሚነገረው የተጋነነ ሳይኾን ከአጠቃላይ ውይይቱ 0.3 % ብቻ ያህል እንደኾነ አሳይቷል።   ከዚህም በላይ እነዚሁ አደገኛ የሚባሉት ንግግሮችና አስተያየቶች የጽንፈኝነት ጥግ ነክተው እንኳን ግጭት ለመቀስቀስ በሚያበቃ ስጋት የማይፈጥሩ መኾናቸውን አሳይቷል።

ጥናቱ በዳሰሳቸው የኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ባህርያት ውስጥ ቀደም ሲል በብዙዎች ዘንድ ያለጥናት በግምት ብቻ ተወስደው የነበሩ አመለካከቶችን የሚቃረኑ አዲስ ግኝቶችን አሳይቷል። ከነዚህም መካከል የጥላቻና አደገኛ ንግግሮች በሚል የተመደቡት የማኅበራዊ ድረ ገጽ በተለይም የፌስቡክ መልዕክቶች ያላቸውን መጠን የተመለከተው ውጤት ነው። በዚህም ጥናት መሰረት ከዚህ በፊት ተጋነው ይታሰቡ የነበሩት ጥላቻና አደገኛ ንግግር ያዘሉ የፌስቡክ መልዕክቶች መጠን እንደሚታሰበው ብዙ አለመኾናቸውን ማሳየቱ ነው። በነዚህ ሁለት መደቦች የተመደቡት የንግግር አይነቶች በታዋቂ ሰዎች ላይ ከሚሰነዘሩ ትችቶች አንስቶ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እስከመደገፍና መቃወም እንደዚሁም የሐይማኖትና የብሔር ልዩነቶችን የተመለከቱ ንግግሮችን የያዘ ነው።

ምንም እንኳን በነዚህ ጉዳዮች ላይ በሚጻፉ የፌስቡክ መልዕክቶችና ለነዚህም መልዕክቶች በምላሽነት የሚቀርቡ አስተያየቶች ማጥላላትንና ስድብን ያዘሉና በአጠቃላይም የጥላቻ ንግግሮች (hate speech) ተብለው ሊመደቡ የሚችሉ መልዕክቶች ቢኖሩባቸውም በመጠናቸው ትንስ መኾናቸውን ጥናቱ ያሳያል። በጥናቱ ከተዳሰሱት የፌስቡክ መልዕክቶችና አስተያየቶችም መካከል የጥላቻ ንግግር የሚባሉት በመጠናቸው 0.4% ብቻ የሚኾኑት ናቸው።  በአደገኛ ንግግሮች መደብ ተከፍለው ማጥላላቱን ወደተግባራዊ ርምጃ ለማምጣት የሚቀሰቅስ መጠነኛ ይዘት ያላቸው የፌስቡክ መልዕክቶች መጠን  0.3% ብቻ መኾናቸውንም ጥናቱ ጨምሮ አሳይቷል። ከዚህም በላይ እነኚሁም ጥቂትየጥላቻ መልዕክቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን አሉታዊ ውጤት በመገምገም ምንም አይነት ስጋት ሊፈጥር የሚችል ግምት እንደማያሳድር ጥናቱ ጠቁሟል።

 ሌላው የጥናቱ አዲስ ግኝት ኾኖ የሚታየው ጉዳይ ከዚህ በፊት በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውን የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተጽዕኖ የሚመለከተው የጥናቱ ክፍል ነው።

የብዙዎችን ግምት በተቃረነ ኹኔታ የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን በድረገጽ የሚደረገውን የፖለቲካ ውይይት የሚመሩና የዳያስፖራው አስተሳሰብ አብዛኛውን የማኅበራዊ ድረገጽ ይዘት እንደሚሸፍን ግምት ሲሰጠው ቆይታል። ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው ግን ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት የፖለቲካ ውይይት አስተዋጽኦ እንደሚታሰበው ትልቅ አለመኾኑንና የተቃውሞ ድምጽ ከሚያሰሙ የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያንም መካከል በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ኾነው አስተያየት የሚሰጡቱ በቁጥር እንደሚበልጡም አሳይቷል። የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን አመለካከት በአንድ መደብ ወስኖ ለማስቀመጥ የሚደረገውም ሙከራ የተሳሳተ መኾኑንም ያሳየው የጥናቱ ውጤት የዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን አመለካከት እስከ ዛሬ ሲታሰብ ከነበረው በተቃራኒ የበለጠ የተሰባጠረ እንደኾነ ጠቁሟል።

ጥናቱ ከደረሰባቸው 10 የመደምደሚያ ውጤቶችም መካከል በሐይማኖት ጉዳይ የሚነሱ ውይይቶችን የዳሰሰበት ክፍል አንዱ ነበር። በዚህም የጥናቱ ክፍል እንደታየው ሐይማኖታዊ ጉዳዮች የክፍፍል ምክንያት ከመኾን ይልቅ በአብዛኛው የፌስቡክ መልዕክቶች የሚንጸባረቀው ጉዳዩ በተለያየ የሐይማኖት ክፍል ውስጥ የሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች የጋራ አቋም ከሚያሳዩባቸውና በጣም ዝቅተኛ የጥላቻ ንግግር ከሚገኝባቸው የፌስቡክ መልዕክቶች ውስጥ ትልቁን ስፍራ እንደሚይዙም አሳይቷል። ጥናቱ እንደምሳሌ ወስዶ ከተነተናቸው ሐይማኖት ነክ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች መካከልም በሊቢያ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያን የሚመለከተው ዜና የፈጠረው ስሜት ይገኝበታል። ጉዳዩ በሁሉም የሐይማኖት ተቋማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ አቋም ያሳዩበት እንደነበረም ተጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚደረጉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ከፋፋይና ጽንፈኛ ባህርያቸው በጣም ዝቅተኛ እንደኾነ የሚጠቁመው ይኸው ጥናት በተለመዱት የመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ቀደም ሲል ይታይ የነበረው ሐሳብን በሰከነ ኹኔታ አቅርቦ መወያየት ላይ ይታዩ የነበሩ ችግሮች በአብዛኛው እንደማይታዩበትም ጥናቱ አሳይቷል። ብዙ ተከታዮች ያሏቸውን የፌስቡክ ገጾች ባህርይም በማጥናት ከጥላቻ ንግግር ጋር ያላቸውን ተዛማጅነት በዳሰሰበት ክፍልም ጥናቱ እንደሚያሳየው ብዙ ተከታዮች ያሏቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ጥቂት ተከታይ ካላቸው ይልቅ ዝቅተኛ የጥላቻና አደገኛ ንግግር የሚገኝባቸው ገጾች መኾናቸውን አሳይቷል።

በአጠቃላይ የጥናቱ ትንታኔም እንደሚያሳየው በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚታየው የጥላቻ ንግግር መጠን እጅግ ዝቅተኛና አደጋ ያስከትል ይኾናል የሚል ስጋት የምሚያጭር ባይኾንም የጥላቻ መልዕክቶቹ የሚያገኙት ምላሽ ግን ብዙ እንደኾነ ይጠቁማል። በአብዛኛው ማንነታቸውን በሚደብቁ ግለሰቦች የሚጻፉት እነኚህ የጥላቻ ንግግሮች በታዋቂ ግለሰቦች፥ በብሔረሰቦችና በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚሰነዘሩ እንደኾኑም ጥናቱ ጠቁሟል። ያም ኾኖ ግን እነኚህ ስድብ አዘልና ጥላቻን የሚገልጹ ንግግሮች ካሌሎች አጠቃላይ ውይይቶች ጋር ሲነጻጸሩ ባላቸው  ቁጥር  ጥቂቶች ከመኾናቸውም በላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ዝቅተኛ መኾኑን ጥናቱ አሳይቷል።

ይህ ጥናት በማጠቃለያው ላይ በጥናቱ ግኝቶች ላይ የተመሰረቱ አስተያየቶችን አስምጧል። በዚህም የባለሙያዎቹ አስተያየት መሰረት በአሁኑ የኢትዮጵያ የማኅበራዊ ድረገጽ አጠቃቀም ባህርይ ለአገር ደኅንነት ስጋት ሊኾን የሚችል አደጋ የሚፈጥር ነገር እንደማይታይ በማሳየት ፖሊሲ አውጪዎች የንግግር ነፃነትን የሚገድቡ ሕጎችን ለማውጣት እንደማያስፈልጋቸው መክሯል። ጥናት ላይ ባልተመሰረተ ስጋት ላይ ተነስቶ ማኅበራዊ ሚዲያዎችንም ይኹን ሌሎች የድረገጽ መገናኛ ብዙኀን ሳንሱር ማድረግ አስፈላጊ እንዳልኾነም ጠቁሟል።

ጥናቱ ይህ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በስጋት የመመልከት ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰት ጉዳይ እንዳልኾነ አስታውሶ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ የኾነ ጥናት በሌሎችም አገሮች ላይ ቢደረግ ይህን ስጋት ተሚቀርፍ መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል ይጠቁማል። ይህ ኢትዮጵያን የሚመለከት ጥናት በግልጽ እንዳሳየው በአብዛኛው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚንሸራሸሩ ሐሳቦች ላይ የሚታየው ስጋት መሰረት የለሽ እንደኾነ ነው። ፀኢትዮጵያም መንግስት ይህንኑ መሰረት የለሽ ስጋት ተገን በማድረግ በአገሪቱ ያለውን የመናገር ነፃነት ገደብ እስከ መጨረሻ ለመዝጋት ባለመ መልኩ አዲስ አዋጅ አሳልፏል። “የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ” በሚል ርእስ የወጣው አዲስ አዋጅ በይዘቱ ከዚህ ቀደም ወጥተው ከነበሩ ፕሬስን የሚመለከቱ አዋጆች ባልተለየ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ሊጋፋ እንደሚችል በብዙዎች ላይ ስጋት አሳድሯል። ከዚህ ጥናት ጋር ተነጻጽሮ ሲታይም የዚህ አዋጅ አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ መውደቁ አልቀረም።