ዋዜማ ራዲዮ-  የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይልና የሶማሊያ መንግስት ባቀረቡት ጥያቄ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ዳግም ወደ ሶማሊያ አንዳንድ ግዛቶች ማንቀሳቀስ መጀመሯን የዋዜማ ምንጮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲሰማሩ የተደረገው ከዚህ ቀደም በሌሎች የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪዎች ስር የነበሩ ግዛቶች- ሰላም አስከባሪዎቹ ሲለቁ በአልሸባብ እጅ በመውደቃቸው ነው።
አልሸባብ ሞቃዲሾና ደቡባዊቷን ባይዶዋ ከተማ የሚያገናኘውን ሌጎ ከተማ ጨምሮ አራት የተለያዩ ይዞታዎችን ዳግም መቆጣጠር ችሏል።
ኢትዮጵያ ያሰማራችው ከአንድ ባታሊዮን ያነሰ ተወርዋሪ ሀይል ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ ወታደሮች ይንቀሳቀሳሉ የሚል ግምት እንዳላቸው አንድ የአፍሪቃ ህብረት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ለዋዜማ ጠቁመዋል።

ለዚሁ ተልዕኮ ይንቀሳቀስ በነበረው የኢትዮጵያ ሀይል ላይ አልሸባብ ድንገተኛ የደፈጣ ጥቃት አድርሶ አርባ ወታደሮችን ገድሏል ሲሉ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። አልሸባብ ሀምሳ ዘጠኝ ወታደሮች መገደላቸውን ተናግሯል። የኢትዮጵያ መንግስት ያለው ነገር የለም።
ኢትዮጵያ አብዛኛውን ወታደሮቿን ወደ ድንበር በመመለስ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ታቅባ ብትቆይም በተከታታይ በአፍሪቃ ህብረትና በሶማሊያ መንግስት ወተደሮች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ እንድትመለስ ፍላጎት ማሳደሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እየተናገሩ ነው።
ይሁንና ኢትዮጵያ ወታደሮችን ለረጅም ጊዜ ለማሰማራት የሚያስፈልገው ወጪን መቋቋም ስለማልችል ድጋፍ የሚያደርግ አካል ካልተገኘ አልሳተፍም ማለቷ ይታወሳል።