DBE President Esayas Bahre
DBE President Esayas Bahre

ከተቋቋመ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከተበዳሪዎች የሚጠብቀውን የሰላሳ በመቶ የገንዘብ ድርሻ ወደ አስር በመቶ ሊያወርድ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ የዋዜማ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚገልፁት አዲሱ ረቂቅ መመሪያ በልማት ባንክ ከተገመገመ በኋላ ለተጨማሪ ማሻሻያ ወደ ብሄራዊ ባንክ ተመልሷል፡፡

ልማት ባንክ ሊወስደው የተዘጋጀው እርምጃ ሀገሪቱ በፋይናንስ ዘርፍ የገባችበትን አጣብቂኝ የሚጠቁም ሲሆን፣ የብድር ማሻሻያው ደግሞ መንግስት ላቀደው የኢንደስትሪ ልማት ፕሮጀክት ባለሀብቶችን ለመሳብ ያለመ ነው። በሀገሪቱ የተከሰተው የረሀብ አደጋ ይህን የመንግስት ዕቅድ ሊያደናቅፈው ይችላል የሚል ስጋትም ተደቅኗል።

(እህተ ፋሲካ እና ቻላቸው ታደስ ያዘጋጁትን ዘገባ መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች። እነሆ የተሟላ የድምፅ ዘገባውን አድምጡ)

አሁን እየተዘጋጀ ያለው አዲሱ የህግ ማዕቀፍ ትልመ-ሃሳብ አቅራቢ ባለሃብቶች የጠቅላላ ኢንቨስትመንታቸውን አስር በመቶ ብቻ በማቅረብ ብድር እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ባንኩ ለበርካታ ጊዚያት ሲተገብረው የነበረው ፖሊሲ የሰባ/ሰላሳ ፖሊሲ ቢሆንም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መጀመሪያ ላይ ግን የሀገር ውስጥ ተበዳሪ ባለሃብቶች ገንዘብ ድርሻ (equity) ወደ ሃያ አምስት በመቶ ዝቅ እንዳለላቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ግን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የግል ባለሃቶች ከነሱ የሚጠበቀው የገንዘብ ድርሻቸ ወደ አስር በመቶ እንዲወርድላቸው በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አምነው ያንን ማድረግ ግን ለባንኩ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር ተናግረው ነበር፡፡ በእርግጥ እሳቸው ካሉት በተቃራኒው ማሻሻው ከተደረገ የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ወይም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ መሰማራት ሊነቃቃ ይችል ይሆናል፡፡

በመንግስት በኩል ለማሻሻያው ምክንያት የሆነው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ትላልቅ የማምረቻ (ወይም ማኑፋክቸሪንግ) ኢንዱስትሪዎችን በበለጠ ለማበረታታትስለፈለገ ነው። በባንኩ ትኩረት የሚደረግባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አምራች ኢንዲስትሪዎች (ማኑፋክቸሪንግ)፣ ግብርና እና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ (Agro Processing) ናቸው፡፡

ከባንኩ ሃላፊዎች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከተጠናቀቀው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በፊት የባንኩ የማበደር አቅም ከአስር ቢሊዮን ብር አይበልጥም ነበር፡፡ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ግን ለብድር አርባ አራት ቢሊዮን ብር መድቦ እንደነበር የጠቀሱት የባንኩ ፕሬዝዳንት ፣ ሃያ ስድስት ቢሊዮን ብር ያህል ለተበዳሪዎች ተለቆሥራ ላይ መዋሉን ገልፀዋል፡፡ ለሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ባንኩ አንድ መቶ አስራ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማበደር እቅድ መያዙን ተናግረው ነበር፡፡DBE

የዘርፉ ባለሙያዎች ግን ባንኩ በየዓመቱ የሚፈቅደውን የብድር መጠን ለባለሃብቶች አይለቅም በማለት ይተቻሉ፡፡ ከሚፈቅደው የብድር መጠን ውስጥም በየዓመቱ ለተበዳሪዎች ሲያስተላልፍ የቆየው በአማካይ ሃምሳ በመቶውን ብቻ እንደሆነ ከባንኩ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ባንኩ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በነበሩት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከፈቀደው ስምንት ነጥብ ዘጠኝቢሊዮን ብር ውስጥ የለቀቀው አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ አራት በመቶ ብቻ መሆኑ ነው። ለዚህም የባንኩ ሃላፊዎችበምክንያትነት የሚጠቅሱት ባለሃብቶቹ የሚጠበቅባችውን የገንዘብ ድርሻ (equity) ማቅረብ አለመቻላቸውን ነው።

የመንግስት ባለስልጣናት ግን ቦንድ ግዥው ያስፈለገው የግል ባንኮች በረዥም ጊዜ አትራፊ ለሚሆኑት ለትላልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር መልቀቅ ስለማይችሉ ወይም ስለማይፈልጉ ብቸኛው አማራጭ የልማት ባንኩን የገንዘብ አቅም ማጎልበት እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከሀገር ውስጥ ፋይናንስ ተቋማት ከአንድ ነጥብ ሰባት ትሪሊዮን ብር ያህል እንደሚፈልግ ዕቅዱ ከሁለት ወራት በፊት ይፋ በሆነበት ተግልጿል፡፡ ይህንንም ለማሳካት ይመስላል ብሄራዊ ባንክ በያዝነው ዓመት ንግድ ባንኮች እንዲመሩባቸው መልካም አስተዳደር፣ ቅርንጫፎች ብዛት እና የተከፈለ ካፒታል መጠን ጣሪያን አስመልክቶ አዳዲስ መመሪያዎች ያወጣው፡፡