AU comission chair Dlamini-Zuma
AU comission chair Dlamini-Zuma

አፍሪካን በመዋሃድ አንድ መንግስት የመመስረት ሃሳብ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል፡፡ በርግጥም አንድ የተባበረ አፍሪካ መንግስት ቢፈጠር በግዛት ስፋት ረገድ የዓለማችን ግዙፉ ሀገረ-መንግስት ይሆናል፡፡ አህጉሪቱ ግን አሁንም ውህደትን አስቸጋሪ በሚያደርጉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ውስብስብ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተተብትባለች፡፡ አፍሪካ ህብረት  ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ ባካሄደው የመሪዎች ጉባዔው አህጉራዊ ፓስፖርት ይፋ ማድረጉም የውህደቱ አጀንዳ አካል ነው፡፡

ህብረቱ ፓስፖርቱን መስጠት የሚችለው ለመሪዎች፣ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እና የህብረቱ ባለስልጣናት ብቻ ሲሆን በመጭዎቹ ሁለት ዓመታት ግን አባል ሀገራት የህብረቱን ውሳኔ በህግ አውጭ አካሎቻቸው አፅድቀው ፓስፖርቱን ለተራው ዜጋ እንዲያድሉ ተጠይቀዋል፡፡ አባል መንግስታት ይህን ማድረግ ካልቻሉ ወይም ካልፈለጉ ግን የህብረቱ ህልም ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡

የሰሞኑን የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ፓስፖርት ጥንስስ መነሻ በማድረግ አህጉራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያ ውህደትን ዕውን ለማድረግ አፍሪካ ህብረት ምን ምን ዕርምጃዎች ወስዷል? የተዋሃደችዋ አፍሪካ መንግስት ሊሳካ የሚችል ተጨባጭ ሃሳብ ወይንስ ከንቱ ቅዠት? ለውህደት ዕንቅፋት የሚሆኑት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያ ችግሮችስ ምንድን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሸ ያሻል፡፡ ቻላቸው ታደሰ ዝርዝሩን አዘጋጅቷል፣እዚህ ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

አፍሪካዊያን መሪዎች ስለ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አህጉራዊ ውህደት የሚያወሩትን ያህል አካሔዱ ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለማቀፋዊ እና አህጉራዊ ሁኔታዎች ተቀያይረዋል፡፡ ለአህጉራዊ ውህድት አመቺ የሆኑ ወይም ውህደትን የሚጋብዙ መልካም ዕድሎች የተፈጠሩትን ያህል አዳዲስ ውስጣዊ እና ዓለማቀፋዊ መሰናክሎችም በውህደቱ አጀንዳ ላይ ጋሬጣ ፈጥረዋል፡፡

ባሁኑ ጊዜ ያለ ቪዛ ወይም ለተጓዦች በአየር ማረፊያ ቪዛ የመስጠት ስምምነት ያላቸው ሀገራት 13 ብቻ ናቸው፡፡ ባንፃሩ አሜሪካዊያን ያለ ቪዛ ወደ ሃያ አፍሪካዊያን ሀገራት መጓዝ መቻላቸው አፍሪካዊያን በመካከላቸው ያሉትን ፖለቲካዊ አለመተማመን ወይም ኢኮኖሚያዊ እና ፀጥታነክ ስጋቶች ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ለአፍሪካዊያን ላላ ያለ ቪዛ ህግ ያላቸው ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሪሺዬስ እና ጋና ብቻ መሆናቸውም መሪዎች በህብረቱ ጉባኤ ለሚወስኑት ውሳኔ ምን ያህል ተገዥ እንዳልሆኑ ያረጋግጣል፡፡ ነፃ ቢዛ ዕቅድን ለማሳካት የቀሩት ሁለት ዓመታት ብቻ መሆናቸውን ታሳቢ ያደረጉ ወገኖች ህብረቱ ሊሳካ በማይችል ቅዠት ውስጥ ተዘፍቋል በማለት ክፉኛ የሚተቹትም ለዚህ ነው፡፡ ሌሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዮች የሚያነሱ ታዛቢዎችም ከፈረሱ የቀደመ ጋሪ አድርገው ያዩታል፡፡

ህብረቱ እኤአ 2028 አህጉራዊ ማዕከላዊ ባንክን፣ አህጉራዊ ፓርላማን እና አንድ የጋራ መገበያያ ገንዘብን ለማስተዋወቅ አቅዷል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደሞ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና እንዲታወጅ አደርጋለሁ ይላል፡፡ ሆኖም አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ ስድስት አስርት ዓመታት በኋላም እንኳ በመካከላቸው ትርጉም ያለው የንግድ ልውውጥ የላቸውም፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል የንግድ ልውውጣቸው ከአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ ወይም እስያ ሀገራት ጋር ብቻ ሆኖ ኖሯል፡፡ በወጭ ንግዳቸው መጠን ማነስ ሳቢያ ያልተመጣጠነ ንግድ ያላቸው አፍሪካዊያን ሀገራት ገና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችል አቋም ላይ ለመድረስ ዓመታት ይወስድባቸዋል፡፡ ከንግድ ሚዛኑ ጉድለት ተጠቃሚ የሆኑት በተለይ የበለፀጉት አውሮፓዊያን ሃገሮች ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ቻይና ያሉ በአፍሪካ ግዙፍ ንግድ እየጀመሩ ያሉ የንግድ ሸሪኮች ግን ከተዋሃደች አፍሪካ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ አህጉሪቱ ያላት ዕምቅ ሃብት እና ግዙፍ የሰው ኃይል ያላት በመሆኗ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ውህደትን ዕውን ብታደርግ የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ማዕከል መሆኗ አይቀሬ መሆኑ ውህደቱ በውጭ ጣልቃ ገብነትም ጭምር ሊጓተት እንደሚችል አመላካቺ ነው፡፡

የሀገሮች ኢኮኖሚም ዕድገት ደረጃ፣ ንግድ መጠን፣ ቀረጥ ምጣኔ እና ሌሎች ህጋዊ አሰራሮችም እንዲሁ ከሀገር ሀገር ይለያያሉ፡፡ የንግድ ማነቆ የሆነው ከፍተኛ ቀረጥ ቢቀር የአርስበርስ ንግድን እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያፋጥናል፡፡ ችግሩ ግን አነስተኛ የቀረጥ መሰረት ያላቸው ድሃ መንግስታት ከድንበር ንግድ ቀረጥ የሚያገኙትን ገቢ ማጣት አለመፈለጋቸው ነው፡፡

የአውሮፓ ህብረት ልምድም የሚያሳየው ፖለቲካዊ ውህደት ተመጣጣኝ እና የተረጋጋ ኢኮኖሚ በሌለበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ ለአብነት አህጉራዊ ነፃ የሰዎች ዝውውር ዕውን ቢሆን እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ አንጎላ እና ቦትስዋና ያሉ ያደጉ ኢኮኖሚዎች በስራ ፈላጊዎች መጥለቅለቃቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ በአውሮፓ ህብረት ላይ ሳይቀር ችግር ፈጥሮ እንግሊዝ ከህብረቱ እንድትወጣ አስገድዷታል የሚባልለትን ያለተገደበ ፍልሰት በአፍሪካ ደረጃ ማሰብ በራሱ ናላ የሚያዞር ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ያደገ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገሮች በነፃ ንግድ እና ያለ ቪዛ እንቅስቃሴን ሊፈቅዱ ይችላሉን? የሚለውን ጉዳይ አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡  ገና ካሁኑ በህገ ወጥ መንገድ በገቡ በርካታ ጥቁር ስራ ፈላጊ ስደተኞች በተጥለቀለቀችው ደቡብ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዘረኝነት ስር ሰዷል፡፡ ስደተኞችም ለዘረኝነት ጥቃቶች ተዳርገዋል፡፡ጥቁር አፍሪካዊያን ስደተኞች ከሀገራችን ይውጡልን!” የሚለው ግፊት እየጎለበተ መምጣቱ የውህደቱ አጀንዳ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

ነባራዊ ሁኔታዎች የሚያረጋግጡት ስራ አጥነት፣ ፍልሰት እና ዘረኝነት ለመጭዎቹ ዓመታትም ዋነኛ የአህጉራዊ ውህደት እንቅፋት ሆነው እንደሚቀጥሉ ነው፡፡ ስለሆነም ውህደትን ዕውን ለማድረግ በቅድሚያ ሁሉም መንግስታት ስራ ዕድሎችን የሚፈጥር የተረጋጋ ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ መረጋጋትንም ማስፈን መቻል እንዳለባቸው ጠቋሚ ነው፡፡ በሀገራት መካከል ግን በዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ያሉት ሰፊ ልዩነቶች ገና አልጠበቡም፡፡ አሁንም አይቮሪኮስት፣ ናይጀሪያ፣ ሱማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ኮንጎ፣ ማሊ፣ የሰሜን አፍሪካ ዐረብ ሀገራት ወዘተ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንደራቃቸው ነው፡፡ በተለይ ለህብረቱ ከፍተኛውን መዋጮ ሲያዋጡ የኖሩት ሊቢያ እና ግብፅ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ ውስጥ መግባታቸው ህብረቱን ጎድቶታል፡፡

መንግስታት ከአህጉራዊ ትስስር በላይ ለሀገራዊ ሉዓላዊነት የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ መሆኑም ሌላኛው እንቅፋት ነው፡፡ ብዙ አፍሪካዊያን መሪዎች ለአፋዊ ታይታ ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ውህደትን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገውት አያውቁም፡፡

ውህደት ብዙ ቢሰበክለትም ገና በተራው ህዝብ፣ ምሁራን፣ ንግድ ማህበረሰቡ እና ሲቪል ማህበረሰቡ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ በርካታ ታዛቢዎች ደጋግመው ያሉት እና ህብረቱም የማይክደው ዕውነታ ቢኖር እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በህብረቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት ያላዳበሩ መሆናቸው ነው፡፡ አስራ አራት ኣመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ህብረቱ በመዋቅራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባጀት ዕጥረት ሳቢያ ከመሪዎች እና ቢሮክራቶች ክለብነት አልፎ ወደ ተራው ህዝብ አልወረደም፡፡ አህጉራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት በመሪዎች ፍቃደኝነት ላይ ካለው ጥገኝነት ተላቆ በህዝብ ፍላጎት የሚወሰንበት አጀንዳ መሆን አልቻለም፡፡

ለአህጉራዊ ንግድ ዕድገት ማነቆ የሆነው ሌላኛው ችግር መሰረተ ልማት አለመኖር ነው፡፡ ብዙዎቹን አፍሪካ ሀገራት ቀርቶ ባህል እና ቋንቋ የሚጋሩ ጎረቤታሞች እንኳ በመኪና መንገድ፣ ባቡር ሃዲድ ወይም አየር ትራንስፖርት አልተሳሰሩም፡፡ ለአብነትም ምዕራብ አፍሪካን መውሰድ ይቻላል፡፡ ከሴኔጋል ወደ አይቮሪኮስት በአውሮፕላን ለመብረር ያሰበ ነጋዴ መጀመሪያ ከዳካር ወደ ፓሪስ መጓዝ ሊጠበቅበት ይችላል፡፡ ባንድ በኩል ብዙዎች አፍሪካዊያን ሀገራት የራሳቸው አየር መንገዶች የላቸውም፡፡ ያላቸውም ቢሆኑ እጅግ ደካማ ናቸው፡፡ ከውጭ አየር መንገዶች ጋር ተወዳዳሪ መሆን የቻሉት እንደ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ በጣት የሚቆጠሩት አየር መንገዶች ብቻ ናቸው፡፡ የአየር መጓጓዣው ውድነትም ለተራው ዜጋ በቀላሉ የማይቀመስ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች በአፍሪካዊያን መካከል ሊኖር የሚገባውን የሸቀጥም ሆነ ጎብኝዎች ዝውውር አዳጋች አድርጎታል፡፡

በየጊዘው የሚነሱ ገዳይ ወረርሽኞች እና ሽብርተኝትም አህጉራዊ ውህደትን አጓታች ናቸው፡፡ በተለይ ሽብር ዋነኛ የትብብር እና ውህደት ጠንቅ ሆኗል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ብቻ እንኳ የናይጀሪያው ቦኮሃራም እና የሱማሊያው አልሸባብ በመካከለኛውና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ደህንነት ላይ አደጋ እንደደቀኑ ቀጥለዋል፡፡ ያለ ቢዛ ዝውውር በተከለከለበት ሁኔታም እንኳ ሽብርተኞችእና የተደራጁ ወንጀለኞች ልል በሆኑ ድንበሮች በቀላሉ እየተዘዋወሩ በደህንነት ላይ ስጋት ይፈጥራሉ፡፡ ኮንትሮባንድ ንግድም ተጧጡፏል፡፡ ህገ ወጥ ገንዘብ፣ መሳሪያ፣ መድሃኒት እና የሰዎች ዝውውርም የመንግስታት ራስ ምታት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስጋቶች መንግስታትውህደትን በሩቁእንዲሉ ማስገደዳቸው አልቀረም፡፡

የህብረቱን ኮሚሽን African Union Authority (አፍሪካ ህብረት ባለስልጣን) በተባለ አዲስ ጥርስ ያለው የበላይ አካል እንዲተካ ከተወሰነ ሰባት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ በሌላ በኩል የመሪዎች ጉባዔ ከሁለት ዓመት በፊት ህብረቱ ባጀቱ በለጋሾች መደጎሙ ቀርቶ በአምስት ዓመት ውስጥ ራሱን እንዲችል ወስኖ ነበር፡፡ እስካሁንም ግን አንዳችም ተስፋ ሰጭ ፍንጭ ዕርምጃ አልታየም፡፡

ህብረቱ እየተገበረ ያለው ስትራቴጂ በምዕራብ፣ ምስረቅ፣ ሰሜን፣ ደቡብባዊ እና መካከለኛው አፍሪካ የሚገኙትን አምስቱን ክፍለአህጉራዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች እንደ ማዕዘን ድንጋይ በመጠቀም አዝጋሚ ሂደታዊ ውህደት ማምጣት ነው፡፡ ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ግን እምብዛም ቅንጅት የላቸም፡፡ ዕድገታቸውም የተራራቀ ብቻ ሳይሆን ዘገምተኛም ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በባጀት የሚደጎሙትም በምዕራባዊያን ለጋሾች ነው፡፡

በርግጥ ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ታንዛኒያን፣ ሩዋንዳን እና ደቡብ ሱዳንን ያቀፈው የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የጋራ ገበያ እና ካስተምስ ስምነቶች ላይ ከደረሰ ሰነባብቷል፡፡ በቅርቡም የጋራ ገንዘብ ፖሊሲ ስምምነት ለመተግበር እያውጠነጠነ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ደሞ ሀገራቱ የፖለቲካ ፌደሬሽን ይመሰርታሉ ብሎ ዕቅድ ይዟል፡፡ የቀጣነው ሀገራት ግን  በመሰረት ልማት ለመተሳሰር ያደረጉት ጥረት በጣም ውስን መሆኑ በዕቅዱ ላይ በረዶ የሚቸልስ ሆኗል፡፡

አፍሪካን የማዋሃድ ሃሳብ ጠረጴዛ ላይ ከተቀመጠም ሆነ በአደባባይ መወያያ መሆን ከጀመረ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያው አህጉራዊ ድርጅት የሆነው አፍሪካ አንድንት ድርጅት ግን ከቅኝ ግዛት እና አፓርታይድ ነፃ ለመውጣት በሚደረጉ ትግሎች፣ በድንበር ግጭት እና ቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ባመጣቸው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጣጣዎች ሲታመስ ስለኖረ አህጉራዊ ውህደትን የሚያፋጥንበት ዕድል አልነበረውም፡፡ ያም ሆኖ አንድ ግዙፍ መሰረት መጣሉ ግን አይካድም፡፡ እኤአ 1991 “የአቡጃ ስምምነትተብሎ የሚጠራውንየአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮምዩኒቲአህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጠና አፅድቋል፡፡ አፍሪካ ህብረት እስካሁንም እየወሰዳቸው ያሉት ዕርምጃቸዎች ይህንኑ አህጉራዊ ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡

አፍሪካ ህብረት እኤአ 2013 ያፀደቀው አህጉራዊ ፍኖተ ካርታ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡አጀንዳ 2063” የተሰኘው ፍኖተ ካርታ እኤአ 2063 የበለፀገች እና የተባበረች አንድ አፍሪካን ዕውን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

በጠቅላላው አፍሪካ አንድ መንግስት ሆና አፍሪካዊያን ከኬፕታውን እስከ ካይሮ፣ ከዳካር እስከ ዳሬሰላም በቀላሉ መዛዋወር፣ ሰርቶ መኖር ወይም ያለገደብ መነገድ የሚቻሉበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚለው ተስፋ አልተዳፈነም፡፡ ስጋቶች ግን ብዙ እና ውስብስብ ናቸው፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አውሮፕ ህብረት እየገጠሙት ያሉት ፈተናዎች አስጊ ሆነዋል፡፡ አፍሪካን ውህደት ሙጭጭ ብለው የያዙ ወገኖች ግን አፍሪካ ህብረት ከአውሮፓ ህብረት ፈተናዎች የሚማረው ነገር እንዳለ ይጠቁሙና የግድ ግን ፈለጉን አንድ በአንድ መቅዳት እንደሌለበት ይመክራሉ፡፡ አንድ ነገር ግን ርግጥ ነው፣ አህጉሪቷ ውህደት ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ፈተናዎችን መጋፈጥ እና ዓመታትንም መጠበቅ ይጠበቅባታል፡፡