Takele Uma- Addis Ababa Administration ,Deputy Mayor-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በስሩ የተጠቃለሉ የሶስት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮንትራትና የድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችን ሊያሰናብት ነው።
በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጽዮን ተሾመ ሰኔ 10 2011 አ.ም ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ፣ ኤጀንሲው የሚያሰናብታቸው የደጋፊና የኮንትራት ሰራተኞች በስሩ እንዲጠቀልላቸው የተወሰኑለት የሶስት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶች ማለትም ፣ የእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕርጀክት ጽህፈት ቤት ፣ የመናፈሻ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትና የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች እና የአየር ንብረት ማጣጣም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ናቸው።

ዋዜማ ሬዲዮ ያገኘችው የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የፈረሙበት ደብዳቤ ፣ ኤጀንሲው ሰራተኞችን የሚቀንሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት ባወጣው አዋጅ ቁጥር 64 /2011 መሰረት ባስጠናው የመሰረታዊ የስራ ሂደት አዲስ መዋቅር በማዘጋጀቱ መሆኑን ይገልጻል።


በዚህም መሠረት በእንጦጦና አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ፕርጀክት ጽህፈት ቤትና በመናፈሻ ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሲሰሩ የነበሩ የቴክኒክ ሰራተኞች ከከተማ አስተዳደሩ የሲቪል ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመነጋገር በኤጀንሲው በዴስክ ተመድበው እንዲሰሩ ፣ በሁለቱ ጽህፈት ቤቶች የድጋፍ ሰጭ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ግን በኮንትራት ሰራተኞች አስተዳደር መመሪያና በውላቸው መሰረት እንዲሰናበቱ ከወዲሁ አስፈላጊው ይደረግ ይላል ደብዳቤው። እዚህ ጋር ግልጽ ያልሆነው ነገር ግን የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቶቹ ድጋፍ ሰጭ የነበሩ ሰራተኞች በኮንትራት ሰራተኞች አስተዳደር መመሪያ መሰረት ይሰናበቱ ይላል እንጂ የኮንትራት ቅጥር ስለመሆናቸው አያሳይም።
በሌላ በኩል የወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች እና የአየር ንብረት ማጣጣም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮንትራት ሰራተኞች በኮንትራት ሰራተኞች አስተዳደር መመሪያና በውላቸው መሰረት እንዲሰናበቱ ከወዲሁ አስፈላጊው ይደረግ ይላል ደብዳቤው።ከስራ የማሰናበቱ ስራም ከሰኔ 10 2011 አ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆንም ይላል በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጽዮን የተፈረመው ደብዳቤ።የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በወሰደው እርምጃ ምክንያትም በርካታ ሰራተኞች ከስራ የሚሰናበቱ ይሆናል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከአረንጓዴ ልማትና ከመዝናኛ ልማት ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ እየተነገረ ባለበት በዚህ ጊዜ ብዙ ሰራተኞችን ማሰናበት ያልተጠበቀ ነው።


ከዚህም ሲያልፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ካለው ከዚህ ኤጀንሲ ባለፈ በርካታ ተቋማት በሽግሽግ እና መሰል ምክንያቶች ሰራተኞችን እያሰናበቱ ነው።የመሬት ነክ ተቋማት በተመሳሳይ ሰራተኞችን እያሰናበቱ ነው።

የዋዜማን ዝርዝር ዘገባ ለመድመጥ ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/WkbFqthDUZQ