Shiferaw Jarso, Director of Ethiopia Sugar Corporation
Shiferaw Jarso, Director of Ethiopia Sugar Corporation

በኢትዮዽያ መንግስት የተጀመረውና ብዙ የተባለለት ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክት ከፍተኛ አስተዳደራዊ ምስቅልቅልና በሚሊየን ዶላር የሚቆጠር ብክነት እየገጠመው ነው። የገዢው ፓርቲ ኩባንያዎች በስፋት የሚሳተፉበት ይህ ፕሮጀክት ሙስናና ከፍ ያለ የብቃት ማነስ የታየበት ሲሆን፣ በቢሊየን ዶላር የተያዘለት የስኳር ፕሮጀክት ለአየር ንብረት ቀውስ ተጋላጭ መሆኑ የሀገሪቱን ውጥን መና እንዳያስቀረው ያስጋል።

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን ዘገባ መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል። እነሆ አድምጡት]

ሰሞኑን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፤ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙ ግንባታዎችን መሰረት አድርጎ የሰራውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ካካተታቸው 215 ፕሮጀክቶች ውስጥ በውሃና መስኖ ግንባታ ለተፈጸመው ሙስና፤ የተንዳሆን ግድብና መስኖ ፕሮጀክት በማሳያነት አንስቷል፡፡

የተንዳሆ ፕሮጀክት ሲታቀድ ጠቅላላ ወጪው 840 ሚሊየን ብር ይሆናል ተብሎ ቢጀመርም፣ በተደጋጋሚ ተሠርቷል በተባለ የዲዛይን “ማሻሻያ” ምክንያትነት ተጨማሪ 577 ሚሊየን ብር ወስዶ በ1.4 ቢሊየን ብር መገንባቱ ተወስቷል፡፡ የኮሚሽኑ ጥናት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ “ተለባብሶ የቀረበ በመሆኑ እንጂ እውነታው ሌላ ነው” ይላሉ ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ያላቸው ሰዎች፡፡ በዓመት 619 ሺህ ቶን ስኳር እና 55 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ኤታኖል እንደሚያመርት፣ ሙሉ ግንባታውም ከሁለት ዓመት በፊት እንደሚጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የተንዳሆው ፕሮጀክት ፤ በአሁኑ ወቅት እንኳን ስራው ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ የኢትዮጵያን የስኳር ገበያ አቅርቦት ከፍ ለማድረግም ኾነ ገበያውን ለማረጋጋት ጠብ ያደረገው ነገርም የለም፡፡

ዓመታዊው የኢትዮጵያ የስኳር ፍላጎት 6.5 ሚሊየን ኩንታል ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ጥቅል ምርት ከ4 ሚሊየን ኩንታል መብለጥ አልቻለም፡፡ በመኾኑም ቀሪው 2 ሚሊየን ኩንታል የሚሸፈነው ከውጪ ገበያ በመግዛት ነው።

በኢትዮጵያ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለሸንኮራ አገዳ ምርት እንደሚውል መንግሥት ያደረገው ጥናት ይጠቁማል፡፡ይህንን መሰረት አድርጎም ነበር ኢሕአዴግ በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ 10 የስኳር ፕሮጀክቶችን አሳካለሁ ብሎ የተነሳው፡፡ተጠሪነቱ በቀጥታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የነበረውም የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተሰኘው መስሪያ ቤት በአዋጅ የተመሰረተውም ይህንኑ ግብ ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡

በእቅዱ መጀመሪያ ሰሞን ኢትዮጵያ ከዓለማችን ከፍተኛ አስር ስኳር ላኪ አገራት አንዷ እንደምትሆን በባለሥልጣናቱ ተደጋግሞ ሲገለጽ ነበር፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ፍላጎቷን ሙሉ በሙሉ እንደምታሟላ፣ በ2015 አጋማሽ ደግሞ ከራሷ አልፋ 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለውጪ ገበያ እንደምትልክ በመንግስት ሲነገር ቢቆይም አንዱም አልተሳካም፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ተጠናቀው በሙሉ ኃይል ሥራ ይጀምራሉ ከተባሉት ፕሮጀክቶች አንዳቸውም ለምረቃ ባይበቁም ከአስሩ ሶስቱ በዘንድሮው ዓመት ስራ ይጀምራሉ ሲል መንግስት ቃል እየገባነው፡፡

ወረቀት ላይ በሰፈረው እቅድ መሰረት ከሁለት ዓመት በፊት የራሷን ፍላጎት ታሟላለች የተባለችው ኢትዮጵያ ዛሬም በየዓመቱ 200 ሺህ ቶን ስኳር ከሱዳን፣ ከዱባይና ከሌሎችም አገራት እያስገባች ነው፡፡ “ኤክስፖርት አደርጋለሁ” ሲል የነበረው የስኳር ኮርፖሬሽን ከአንድ ወር በፊት በአገር ውስጥ የስኳር ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ 1,515. ብር ይሸጥ የነበረው የአንድ ኩንታል ስኳር ዋጋ ከ300 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቶ 1,830 ብር ገብቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተከሰተውን ጭማሪ ለዋጋ ንረቱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ መንግስት ድጎማውን ቢያነሳ የስኳር ዋጋ ከዚህም በላይ እንደሚንርም ጠቁመዋል፡፡

የስኳር ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ያለመጠናቀቃቸው ሰበቡ ብዙ ቢኾንም፣ለግንባታው ስራ ልምዱም ሆነ ዕውቀቱ የሌላቸው የገዢው ፓርቲ ኩባንያዎች ሥራውን እንዲረከቡ መደረጉን ለክሽፈቱ የመጀመሪያ መነሻ አድርገው የሚያቀርቡ አሉ፡፡እንደምሳሌም የጣና በለስ እና ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ማሽነሪ ተከላ ያለ ጨረታ ለመከላከያ እና ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ (ሜቴክ) እና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ መሰጠቱ እዚህ ላይ በአብነት ይጠቀሳል፡፡

ሜቴክ የማሽን ተከላውን ብቻ ሳይሆን የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት ግንባታን መረከቡን የሚገልጹ ደግሞ በዲዛይን “ማሻሻያ” ሠበብ ባክኖ ለቀረው ገንዘብ ድርጅቱን ተጠያቂ ያደርጉታል፡፡ ለጥናት ብቻ 118.3 ሚሊየን ብር (6.4 ሚሊየን ዶላር) የፈጀው የኩራዝ ፕሮጀክት ለስድስት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ለእያንዳንዳቸው 225 ሚሊየን ዶላር የተመደበ ሲሆን፣ ሙሉ የኮንስትራክሽን ሥራውን የተረከበው ሜቴክ ነው፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ የግንባታው ቦታ ሳይታይ ዲዛይን መሰራቱ፣ ያልተጠናቀቀ ዲዛይን መቅረቡና ፣ ተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥ መደረጉ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የገባበት እንዳይታወቅና የስኳር ፕሮጀክቶቹም ወደ ሥራ እንዳይገቡ ማድረጉን እየተገለጸ ነው፡፡

ከጅምሩ 4.6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ይፈጃሉ የተባሉት ፕሮጀክቶች፣ በስኳር ኮርፖሬሽን በተደረገ “የድጋሚ ጥናት” ምክንያት ወጪያቸው ወደ 5.5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አድጓል፡፡ በኋላም 8 ሚሊየን ዶላር እንደሚፈጁ ተገልጿል፡፡ የስኳር ፋብሪካዎቹ በሚገባ ባለመጠናታቸውና ፕሮጀክቶቹ ያስከትላሉ በተባለው አካባቢያዊ ቀውስ የተነሳ አበዳሪ ባለመገኘቱ ፋይናንስ በማድረግ ላይ የሚገኙት የሕንድና የቻይና መንግስታዊ ባንኮች ብቻ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ያገኘው ጠቅላላ ገንዘብ 64 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር (ከ3 ቢሊየን ዶላር) ያላለፈ ሲሆን ፋብሪካዎቹ እስኪጠናቀቁ እስከ 2020 ድረስ ተጨማሪ 172 ቢሊየን ብር ያስፈልገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዩሮቦንድ ያገኘችው 1 ቢሊየን ዶላር ወደ እነዚሁ ፕሮጀክቶች የገባ ቢሆንም ከታሰበው አንጻር ገንዘቡ የሚያወላዳ አይመስልም፡፡

በስኳር ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ የሃገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል መባሉንም ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ መረጃዎችም ወጥተዋል፡፡ ለምሳሌ ከወንጂ ሸዋ 17 ሺህ ሠራተኞች ውስጥ 10 ሺህ የሚደርሱት በራሳቸው መሬት ላይ ለፋብሪካው ሸንኮራ አገዳ የሚያመርቱ ናቸው፡፡ በየሁለት ሳምንቱ በሚሰጣቸው እጅግ ትንሽ ክፍያ ለምሬት የተዳረጉት እነዚሁ ገበሬዎች ለሚያመርቱት 100 ኪሎ ግራም ሸንኮራ አገዳ 50 ብር ይከፈላቸዋል ቢባልም ተጣርቶ እጃቸው ላይ የሚደርሰው 14 ብር ብቻ እንደሆነ ዘ አፍሪካን ሪፖርት የዛሬ ዓመት አካባቢ ጠቁሟል፡፡ ገበሬዎቹ በምሬት ወደ በቆሎ ምርት መመለስ እንደሚፈልጉ ቢገልፁም መሬቱ የሚፈቀድላቸው ለሸንኮራ ምርት ብቻ እንደሆነም ከፋብሪካው ተገልጾላቸዋል ተብሏል፡፡

በኦሞ ግድብም ለሸንኮራ አገዳ በተዘጋጀ መስኖ ልማት ሳቢያ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ገበሬዎች መፈናቀላቸውም ተገልጿል፡፡ መቀመጫውን ዩኤስ አሜሪካ እንዳደረገው ኢንተርናሽናል ሪቨርስ አድቮኬሲ ቡድን ገለፃ የግድቡ ግንባታ ከአካባቢያዊ ጉዳቱ ባሻገር 500 ሺህ ሰዎችን አፈናቅሎ ለረሃብ አጋልጧል፡፡ የለንደኑ ሠርቫይቫል ኢንተርናሽናል ደግሞ ፕሮጀክቱን ተቃውመዋል በተባሉት የቦዲና ሙርሲ ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የመብት ረገጣ መፈጸሙን በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅና የወንዞች ውሃ ፍሰት መጠን ማነስ በመስኖ ላይ ለተመሰረቱት የስኳር ፋብሪካ ምርቶች ሌላ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የተመሰረቱት የመተሃራ፣ ወንጂ፣ ከሰም እና ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካዎች የችግሩ ዋንኛ ተጠቂዎችም እንደሚሆኑ ይገመታል፡፡ ያም ኾኖ የስኳር ኮርፖሬሽኑ ድረ ገፅ በኤል ኒኖ ምክንያት የተከሰተው ዝናብ እጥረት ችግር እንደማያስከትል ነው የሚገልጸው፡፡
ስኳር ትርፍ የሚያሳፍስ ሸቀጥ እንደመሆኑ ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያላቸው ነጋዴዎች ሥራውን እንዲቆጣጠሩ መደረጉም ችግሩን አወሳስቦታል፡፡