Anuak people from Gambella
Anuak people from Gambella

የፌደራሉን መንግስት የሚመራው ኢህአዴግ በጋምቤላና ሌሎች አንዳንድ ክልሎች ውስጥ ያለው የሚቃረን ፍላጎትና በጎረቤት ሀገራት ያለው የፀጥታ ሁኔታ በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ግጭቶች    ምክንያት እየሆነ ነው። በቅርቡ በጋምቤላ የተከሰተው ግጭትም ፈርጀ ብዙ ሰበቦች ያሉት ቢሆንም የብሄር ፌደራሊዝሙ የወለዳቸውና ገዥው ፓርቲ ሊፈታቸው ያልቻሉ ችግሮችእንዳባባሱት ይታመናል ። ቻላቸው ታደሰ ያሰናዳውን ዘገባ አድምጡት

 

 

በጋምቤላ ክልል በጥር ወር ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በአኝዋክ እና ኑዌር ብሄረሰቦች መካከል በቅርቡ የተነሳው ግጭት መነሻው የግለሰቦች ጥል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ወረዳዎችን ሁሉ ባዳረሰው በዚህ ግጭት የሟቾች ቁጥር አስራ አራት ብቻ መሆኑን መንግስት ቢያምንም የመብት ተሟጋቾችና የውጭ መገናኛ ብዙሃን ግን ቁጥሩን ወደ ሃምሳ ከፍ ያደርጉታል፡፡ በግጭቱ ሳቢያም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለበርካታ ቀናት ዝግ ሆነው ነበር፡፡

ግጭቱን ተከትሎ የፌደራል መንግስቱ የክልሉ ፀጥታ ሃይሎች በግጭቱ ጎራ ለይተው መታኮሳቸውን ስለደረስኩበት ትጥቃቸውን አስፈትቼ ክልሉ በፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር እንዲሆን አድርጊያለሁ ብሏል ፡፡ የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚንስቴር እንደገለጸው የክልሉ ፖሊስ እና ከአንድ ሺህ አራት መቶ በላይ ወታደሮችን ያቀፈው የክልሉ ልዩ ኃይልም ትጥቃቸውን ፈትተው ስልጠና እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ምንም እንኳ ግጭቱን የቀሰቀሱትን ሃይሎች ማንነት ባይገልፅም መጠነ-ሰፊ ግጭት ለመቀስቀስ ታስቦ እንደነበር መንግስት አክሎ አስታውቋል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ በወህኒ ቤት የነበሩ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም ማምለጣቸውን እንደ ማስረጃ አድርጎ አቅርቦታል፡፡ ግጭቱ በወረዳዎች ብቻ ሳይወሰን ወደ ፉኒዶ ስደተኞች መጠለያ ተጋብቶ ለአራት ሰደተኞች ሞት ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የአንዋክ ተወላጅ የሆኑ ስደተኞችም መጠለያውን ጥለው በመውጣት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ነበር፡፡

እንደ ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር አባባል ከሆነ የክልሉ ፀጥታ ችግር የተባባሰው የክልሉ ነዋሪዎች ከደቡብ ሱዳን የሚገባ የጦር መሳሪያ በብዛት በመታጠቃቸው ነው፡፡ ስለሆነም ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ ህዝቡንም ትጥቅ ማስፈታት ጀምሪያለሁ ይላል፡፡ ፌደራል ፖሊስ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መነሻቸው እና ለምን ዓላማ ሊውሉ እንደታሰቡ ያልታወቁ ህገ ወጥ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪዎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል፡፡ ያም ሆኖ ሀገሪቱ እስካሁንም የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግ አላወጣችም፡፡

መንግስት ግጭቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማቆም እየሰራ መሆኑን ቢገልጽም ከአስራ አራት ዓመታት በፊት ተቀስቅሶ በነበረው መጠነ-ሰፊ የጎሳ ግጭት ማግስትም ተመሳሳይ ቃል ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለሁለቱ ብሄረሰቦች ግጭት ግን ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለያዩ ክልሎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱት የብሄረሰብ ግጭቶች የሚያሳዩት መንግስት ግጭት ለመፍታት የሚያስችለው መዋቅርም ሆነ ፖሊሲ እንደሌለው ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ፌደሬሽን ምክር ቤት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከሚገኘው ሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ሀገር ዓቀፍ የግጭት ካርታ ቢያዘጋጅም በይፋ ግን በፖሊሲ ሰነድነት አልፀደቀም፡፡

በአኝዋኮችና ኑዌሮች መካከል የሚነሳው ግጭት ለዘመናት የቀጠለ ነው፡፡ በተለይ የክልሉ ነባር ነዋሪዎች የሆኑት አርብቶ አደሮቹ አኝዋኮች በግብርና የሚተዳደሩትን ኑዌሮችን እንደ መጤ ይቆጥራሉ፡፡ በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል በተፈጥሮ ሃብት እና የፖለቲካ ስልጣን ሽኩቻዎች ይታያሉ፡፡

አኝዋኮች የጋምቤላ ነባር ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ በመንግስት ለውጥ ዋና ተወናይ መሆናቸውንና በታሪክም ከማዕከላዊ መንግስቱ ጋር ያላቸውን ረዥም ግንኙነት በማጣቀስ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት መቆጣጠር እንደሚፈልጉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

እኤአ በ2003 ዓ.ም በአኛዋኮችና በደገኞች መካከል በተቀሰቀሰ ከባድ ግጭት መከላከያ ሰራዊት በአንዋኮች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ እንደሆነ የተነገረለትን እርምጃ በመውሰዱ አኝዋኮች በመንግስት ላይ ቅሬታ ቋጥረው እንደቆዩ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

በ2007ቱ ህዝብ ቆጠራ መሰረት ኑዌሮች ከጋምቤላ ጠቅላላው ህዝብ 47 በመቶውን ሲይዙ አኝዋኮች ደግሞ 22 በመቶውን ይሆናሉ፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ጀምሮ የኑዌሮች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩን በአካባቢው ለረዥም ጊዜ ጥልቅ ጥናት ያደረገው ዶክተር ደረጀ ፈይሳ ይገልፃል፡፡ ኑዌሮች ዜግነታቸውን እንደ ተጨባጭ ሁኔታው አመቺነት ስለሚቀያይሩ አኝዋኮች ቅሬታ አላቸው፡፡ በተለይ ክልሉን ለ13 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት የአኝዋክ ተወላጁ ኡመድ ኡባንግ ከሦስት ዓመታት በፊት ከስልጣናቸው ተነስተው ምክትላቸው የነበሩት የኑዌር ተወላጁ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ቅሬታቸውን እንዳባባሰው ታዛቢዎች ይገልፃሉ፡፡ የኑዌር ተወላጅ ክልሉን በፕሬዝዳንትነት ሲመራ የአሁኑ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያው ናቸው፡፡

በአካባቢው በምሁራን የተደረጉ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጋምቤላ ክልል ብሄረሰብ ፖለቲካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከደቡብ ሱዳን ግጭት ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ እንዲያውም “የደቡብ ሱዳን አፍንጫ ሲመታ የጋምቤላ ዓይን ያለቅሳል” ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሶስት ዓመት በፊት በደቡብ ሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ 250 ሺህ ያህል ደቡብ ሱዳናዊያን ስደተኞች በዓለም ዓቀፉ ስደተኞች ድርጅት አማካኝነት በጋምቤላ ስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ስደተኞችም የኑዌር ተወላጆች መሆናቸው የአኝዋኮችን ስጋት እንዳባባስው ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልፃሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በስደተኞች ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ኑዌሮች ከስደተኛ ጣቢያዎች ውጭ ስራ ስርተው፣ ከነዋሪው ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ስለሚፈቅድ ኑዌሮች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲይዙ ዕድላቸውን አስፍቶታል፡፡

በተለይ በዶክተር ሪክ ማቻር የሚመራው የደቡብ ሱዳኑ ዋነኛ አማፂ ቡድን በአብዛኛው የኑዌር ተወላጆች ስብስብ በመሆኑ መዘዙ ወደ ጋምቤላ እንዳይጋባ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ስጋት ይዞት ቆይቷል፡፡ በአንፃሩ በዲንቃ ጎሳ የበላይነት የተያዘው የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሱዳን ሰላም ድርድር ሂደት በአማፂያኑ ላይ የተለሳለሰ አቋም አሳይቷል በማለት ቅሬታ መያዙ በወቅቱ ሲዘገብ ነበር፡፡ ወደፊትም የጋምቤላ ፀጥታ ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ሰላም ላይ የሚወሰን ይመስላል፡