Ashley-Madisonከትዳራቸው ውጪ ለሚወሰልቱ አገልግሎት ሲሰጥ የከረመው አሽሊ ማዲሰን የተባለ ድረገፅ በመጠለፉ በርካቶች ሰው “መሳይ በሸንጎ” የሚስብላቸውና ገመናቸውን አደባባይ ያዋለ ክስተት ተፈጥሯል። 40 ሚሊየን የሚቆጠሩ ደንበኞች የስም ዝርዝርና የክሬዲት ካርድ መረጃ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በዝርዝሩ የነማን ስም እንዳለ ለማወቅ ብርበራው ቀጥሏል። ከኛስ ሀገር የነማን ስም በዝርዝሩ ይኖር ይሆን? የሚለው ጥያቄም ልብ አንጠልጣይ ሆኗል። መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን ይንገራችሁ አድምጡት

 

አሽሊ ማዲሰን የሚባለውን ለውስልትና የመቃጠሪያ ድረገጽ ያጠቁት ጠላፊዎች የድረገጹን ደምበኞች ምስጢር ይፋ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል። የድረገጹም ሀላፊዎች የደምበኞቻቸውን ምስጢር የያዘ መረጃ በጠላፊዎቹ እንደተወሰደባቸው አምነዋል።
የድረገጹ መረጃ ይፋ የኾነው ድረገጹ እንደተጠቃ ከታወቀ ከ1 ወር በኋላ ሲኾን፥ ጠላፊዎቹ አንስተውት የነበረው ጥያቄ በድረገጹ ሀላፊዎች እምቢተኛነት ሳይመለስ በመቅረቱ መረጃው ሊለቀቅ እንደቻለ ተነግሯል። የጠላፊዎቹ ጥያቄ አሽሊ ማዲሰን የሚባለው ድረገጽና አዛውንት ወንዶች ደምበኞቻቸውን ከወጣት ሴት ልጆች ጋር የሚያቃጥሩበትን Established Men የሚባለውን ሌላውን የድርጅቱን ዌብሳይት እንዲዘጋ የሚጠይቅ ነበረ።
የተጠለፈው መረጃ የደምበኞቻቸውን ሙሉስምና አድራሻ ከመያዙም በላይ ከፊል የክሬዲት ካርድ መረጃና የሚፈልጉት የፍቅር ጨዋታ አይነት የሚያሳይ ዝርዝርም ይገኝበታል።
ይህ ጠለፋ በዝርዝሩ ውስጥ ያሉትን 40 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ክብር በመንካት ማጋለጡ ብቻ አይደለም ስጋቱ ከውርደቱ በተጨማሪም መረጃው ይፋ የኾነባቸው ግለሰቦች ከዚህ በኋላ ለሚደረግ የኢንተርኔት ማጭበርበርና የመሳሰሉ ጥቃቶች መጋለጣቸውም ሌላው ችግር ነው።
Impact Team ተብሎ የሚጠራው ጠላፊ በዝርዝሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ደምበኞች ኾነው ከጋብቻቸው ውጭ የወሰለቱ ሰዎች ላይኾኑ ይችላሉ ብሏል። አንዳንዶች በድረገጹ ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ለመመዝገብ ያህል ብቻ የተመዘገቡ ሊኾኑም እንደሚችሉ ጠቁሟል። ሀሰተኛ ማንነቶችና የማጭበርበር ሙከራዎችም በውስጡ በብዛት ሊገኙ እንደሚችሉም ማሰብ እንደሚገባም መክሯል።
ያም ኾኖ ጠለፋው የብዙ ሰዎችን ድብቅ ማንነት በማጋለጥ ለብዙ ትዳር ፈተና እንደሚያመጣም ይጠበቃል። ስንት የተከበሩ ሰዎችን በማጋለጥ “ሰው መሳይ በሸንጎ” ሊያስብላቸው እንደሚችልም ይገመታል። ይህ እንግዲህ የኢንተርኔቱ ዓለም አዲሱ ገጽታ ነው። ሰዎች ተደብቀው ያደረጉትን ጉዳይ ማጋለጥ በቴክኖሎጂው ዓለም የሚያመጣው ዝና እና ብዙ የገንዘብ ትርፍ ብቻ ሳይኾን ከሚያምኑበት ጉዳይ ጋር በተጻራሪ የቆመን ግለሰብም ይኹን ድርጅት በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ማጥቃት አዲሱ የፍልሚያ ወረዳም ኾኗል። የኢንተርኔቱም ዓለም ከእንግዲህ ወዲያ እጅ እንደመራ የሚኬድበት ቀና መንገድ መኾኑ ቀርቶ ብዙ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ና ቀድሞ ማሰብን የሚጠይቅ ነገር ኾኗል።