ዋዜማ ራዲዮ- አሁን በምርጫ ቦርድ ተዘርዞ ህልውናው እንዲከስም የተደረገው ቀድሞ የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እና በማዕከላዊው መንግስት መካከል ጦርነት የተቀሰቀሰ ዕለት ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ምሽት ወደ ትግራይ መቀሌ በአሮጌው ብር እንዲቀየር በብሄራዊ ባንክ በአውሮፕላን የተላከው አዲሱ 1.3 ቢሊየን ብር መዳረሻው መታወቁን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


ከምንጫችን እንደሰማነው በአሮጌው ብር እንዲቀየር የተላከው 1.3 ቢሊየን ብር መቀሌ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ አንድ ክፍል ውስጥ ታሽጎ ነው የተገኘው።

ህወሀት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈፅሟል በተባለበትና ግጭቱ ወደለየለት ጦርነት በተሸጋገረበት በዚያ ዕለት አሮጌውን የብር ኖት እንዲተካ የተላከው ብር መዳረሻ አልታወቀም ነበር።


በወቅቱም መንግስት ገንዘቡን በትግራይ ክልል ላሉ የተለያዩ ባንኮች አከፋፍያለሁ ብሎ በብሄራዊው የቴሌቭዥን ጣብያ ማስነገሩ ይታወሳል። ማይጨው ፣ አደዋ ፣ሽሬ እንዳስላሴ እና አዲግራት ላሉ የተለያዩ ንግድ ባንኮች ብሩ ተከፋፍሏል ተብሎም ነበር። ሆኖም በወቅቱ በክልሉ ከነበረው ሁኔታ አንጻርና እንደተባለውም ብሩ በክልሉ ላሉ የባንክ ቅርንጫፎች እንዳልተከፋፈለ ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ አረጋግጣ መዘገቧ ይታወሳል።

የ1.3 ቢሊየን አዲሱን ብር እጣ ፈንታም የፌዴራል መንግስት የመቀሌ ከተማን ከተቆጣጠረም በሁዋላ በመቀሌ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ አዲስ ስራ እንኪጀምር አላወቀም ነበር ብለውናል ምንጫችን። ሆኖም ከሳምንታት ወዲህ በመቀሌ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫ እንደገና ስራ ሲጀምር ነው የቅርንጫፉ ሰራተኞች ብሩን በአንድ ክፍል ታሽጎ ያገኙት። ገንዘቡ ሲገኝም የመጠን ቅናሽ እንዳልነበረው ከምንጫችን መረዳት ችለናል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በክልሎች ብርን ለማሰራጨት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎችን በማእከልነት እንደሚጠቀም ይታወቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]