Jawar Mohamed- FILE
  • ምርጫ ቦርድም ኦፌኮ ጃዋርን በምን ህጋዊ ማስረጃ አባል አድርጎ እንደተቀበለ እንዲያብራራ ጠይቋል


ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ በቅርቡ ፓርቲውን የተቀላቀለው ጃዋር መሀመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዳለው የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ደብዳቤ እንደፃፈለት ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የቀድሞው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ስራ አስኪያጅ ጃዋር መሀመድ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ሲሆን የውጪ ዜግነቱን መልሶ የኢትዮጵያ ዜግነት ለመውስድ እየሞከረ እንደነበር ከወራት በፊት ገልጿል። ይሁንና የዜግነቱ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲን ተቀላቅሎ መታወቂያም ወስዷል።


ጉዳዩን በተመለከት ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ለኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ ድብዳቤ ፅፎ ማስረጃ የጠየቀ ሲሆን ፓርቲው በበኩሉ ጃዋር ማስረጃ እንዲያቀርብ በደብዳቤ አሳስቧል። የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና ይህን መረጃ ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

“የኛ አባል ሲሆን ለምን ይህ ጥያቄ እንደተነሳ ባይገባኝም እኛ ደብዳቤ ፅፈንለታል” ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና።

እንዴት ለዜግነቱ ማረጋገጫ ሳያቀርብ በህግ ባልተፈቀደ መልኩ ጃዋር መሀመድ ፓርቲውን እንዲቀላቀልና መታወቂያ እንዲወስድ እንደተፈቀደለት ከዋዜማ ላነሳንላቸው ጥያቄ መረራ ጉዲና ሲመልሱ ” እኛ የምናውቀው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው፣ የሀገሩን ቋንቋ ይናገራል፣ ፊቱም ኢትዮጵያዊ ይመስላል፤ መንግስትም ይህን ያውቃል” ሲሉ ቀልድ አዘል ምላሽ ስጥተዋል።

በጃዋር ዜግነት ላይ ከመንግስት የሚነሳው ጥያቄ ፖለቲካዊ ፍላጎትንም ያካተተ ሊሆን ይችላል ያሉት መረራ ጉዲና ጃዋር በቅርብ ዜግነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉና ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድም በጊዜው ምላሽ እንደሚሰጡ ነግረውናል።


ፓርቲያቸው ከጃዋር መሀመድ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳለው ያመለከቱት መረራ ፓርቲውንም የተቀላቀለው ከዚህ ቀደም በነበራቸው ትብብርና መቀራረብ የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ።


በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ መብት የለውም። ጃዋር መሀመድ ከሶስት ወራት በፊት በመጪው ምርጫ ለመወዳደር መዘጋጀቱን ግን ደግሞ ለየትኛው የስልጣን ወንበር እንደሚወዳደር እንዳልወሰነ ሲገልፅ ተደምጧል።

ጃዋር መንግስት ባደረገለት ከፍተኛ የአቀባበል ስነስርዓት ከአንድ አመት ተኩል በፊት ወደ ሀገር ቤት መግባቱ ይታወሳል። በወቅቱም በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት እቅድ እንዳለው በማወጅ የድረ ገፅ ዘመቻ ሲያደርግበት የነበረውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር የትግሉን መገባደድ ተምሳሌትነት እንዲሆን በማለት በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለነበሩት ለማ መገርሳ በሚሊኒየም አዳራሽ በህዝብ ፊት ማስረከቡ አይዘነጋም። [ዋዜማ ራዲዮ]

Comment to the editors wazemaradio@gmail.com