admin zonesዋዜማ ራዲዮ-የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል መንግስታት ለወራት የግጭት ሰበብ ሆኖ የቆየውን ድንበር ለማካለል ስምምነት ተፈራረሙ።
የሁለቱ ክልል ፕሬዝዳንቶች- የኦሮሚያ ክልል ፕ/ት ለማ መገርሳና የሱማሌ ክልል ፕ/ቱ አብዲ መሀመድ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስትሩ ካሳ ተክለብርሀን ባሉበት ስምምነቱን ፈርመዋል።

በስምምነቱ መሰረት በ1997 ህዝበ ውሳኔ የተሰጠባቸው 420 ቀበሌዎች መሀከል 340 ቀበሌዎች በኦሮሚያ 80 ቀበሌዎች ደግሞ በሱማሌ ክልል እንዲተዳደሩ የተወሰነው ህዝበ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ከስምምነት ተደርሷል። በዛሬው ስምምነት መሰረትም በሁለቱ ክልሎች መሀከል የድንበር ማካለሉ ስራ በ3 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልፃል።
በሁለቱ ክልሎች መሀከል የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ በወቅቱ ተግባራዊ ባለማድረጋችን ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ለሌሎች ችግሮች ተጠያቂዎቹ የሁለቱ ክልል አመራሮች ነን ሲሉ የኦሮሚያ ፕ/ት ለማ መገርሳ መግለፃቸውንም ዋዜማ ሰምቷል።
በሁለቱ መሪዎች የሰላም ስምምነት የተደረሰባቸው ዝርዝር ነጥቦች 13 ሲሆኑ የሁለቱ ክልል ነዋሪ ኢትዬጵያዊያን ያለ ምንም ክልከላ እና ገደብ በመረጡት ቦታና የመረጡትን ስራ በፈቀዱት ቦታ በነፃነት እንዲሰሩ የሚል ነጥብ ይገኝበታል።