Fano Members -FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ትናንት በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ውጥረት መቀስቀሱን የክልሉ የዋዜማ ዘጋቢ ያደርሰን ሪፖርት ያመለክታል።

የሞጣ ከተማ የፋኖ መሪ በመንግስት መታሰሩን ተከትሎ በፋኖ አባላትና በክልሉ መንግስት መደበኛ የፀጥታ ሀይል መካከል ከባድ ተኩስ የነበረበት ግጭት ተፈጥሯል።

በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የፋኖ አባላት እያካሔዱት ያለውን ወታደራዊ ስልጠና እንዲያስቆም ሲጠየቅ ፍቃደኛ ያልሆነውን የሞጣ ከተማ የፋኖ መሪ የአካባቢው ታጣቂዎች ማሰራቸውን ተከትሎ በተነሳ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ዋዜማ ከቦታው ሰምታለች።

በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር ዋዜማ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለችም። እማኞች እንደሚናገሩት ግን የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸውን እስከ ስድስት ግለሰቦች ተመልክተዋል።

የሞጣ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ይህ ዘገባ ከወጣ አስር ሰዓታት በኋላ ባወጣው መግለጫ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ እና “በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ” ያላቸው ታጣቂዎች ትናንት በሞጣ ከተማ በፈጸሙት ጥቃት አራት የመንግሥት ጸጥታ ኃይል አባላት እንደተገደሉና ሌሎች ደሞ እንደቆሰሉ አስታውቋል።

ግጭቱን ተከትሎ ትናንት ምሽት ላይ ተጨማሪ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው በመግባቱ መረጋጋት መፈጠሩን ተረድተናል። በክልሉ መንግስትና በፋኖ መካከል ያለው ውጥረት አሳሳቢ እንደሆነና በቅርቡም የፋኖ ስልጠናችሁን ማቆም አለባችሁ በሚል በዞኑ በግንደ ወይን፣ በየጁቤና በቢውኝ ወረዳዎች ግጭቶች ተፈጥረው እንደ ነበር ስምተናል።

የፌደራል መንግስት ፋኖን ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ብሎ ሊያፈርሰው ይፈልጋል በሚል በአማራ ክልል ከፍተኛ ስጋት ያለ ሲሆን በአማራ ክልልም ይሁን በፌደራል መንግስት በኩል የፋኖ አደረጃጀትን የማፍረስ ዕቅድ እንደሌለ ሲነገር ቆይቷል።

ከመንግስት ጋር ባለው አለመተማመን ሳቢያ በበርካታ አካባቢዎች የሚደረጉ የፋኖ ስልጠናዎች በህቡዕ መደረግ መጀመራቸውን ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰበችው መረጃ ይጠቁማል።

የአዘጋጁ ማስታወሻ፡ ይህ ዘገባ መጀመሪያ ከወጣ በኋላ የክልሉ መንግስት ምላሽ ታክሎበታል። [ዋዜማ ራዲዮ]