በመስፍን ነጋሽ [ከዋዜማ ራዲዮ]

PM Abiy Ahmed with Sec States Mike Pompeo in Addis Ababa Feb 18/2020

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ላይ ለመነጋገር የጀመሩት ድርድር ወደ መቋጫው እየደረሰ ይመስላል። ድርድሩ ሳይቋጭ ቢቀር የሚመኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት ባይሆንም፣ ያለንበት ሁኔታ ድርድርን አንጠልጥሎ ለመተው የሚያስችለን አይመስልም። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲሳባ የመጡትም “ድርድሩን ቋጩ” ብለው ጫና ለማሳደር ነው። እንዲያውም አሜሪካና የዓለም ባንክ ያዘጋጁትን የስምምነቱን “የመጨረሻ” ረቂቅ ይዘው መጥተዋል። ይህን ጽሑፍ ባሰፈርኩበት ምሽት፣ አዲሳባ ላይ፣ የኢትዮጵያ ቁልፍ ተደራዳሪዎች የአሜሪካው ልዑክ ይዞት የመጣውን የስምምነት ሰነድ በግራ መጋባትና በእልህ ሲመረምሩና ሲመክሩ ነበር።


በቅርብ ሳምንታት በዋዜማ ሬዲዮ እና በሌሎችም በኩል በአዲሳባ፣ በካይሮ፣ በካርቱም እና በዋሺንግተን ዲሲ ሲካሄዱ የሰነበቱትን ድርድሮች በማስመልከት የወጡት ዘገባዎች ሂደቱ ውስብስብ መሆኑን የሚያስጠነቅቁ ነበሩ። ዘገባዎቹ የድርድሩን ውጤት በዋናነት የሚቀርጹት በጠረጴዛ ዙሪያ የተሰበሰቡ ባለሞያዎች እውቀትና አርበኝነት ሳይሆኑ (ሀ) የኢትዮጵያ እና የግብጽ ውስጣዊ ሁኔታ፣ (ለ) ቀጣናዊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አሰላለፎች እና (ሐ) ወቅታዊ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች የሚቀርጹት ቁመናች መሆናቸውን ደጋግመው ያስታውሳሉ። ሆኖም ተደራዳሪዎቹን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአርበኝነት ስሜት ወይም/እና በእውቀት መጉደል የሚጠረጥሩ፣ የሚወቅሱ፣ የሚከሱ ድምጾች ሞልተዋል።


በማንኛውም ድርድር ውስጥ ተደራዳሪዎቹን ወገኖች/አገሮች ወክለው ድርድሩን የሚያደርጉት ሰዎች እውቀትና ልምድ በሂደቱና በውጤቱ ላይ ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል። ይሁንና ድርድሩ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ የድርድሩ ሂደትም ሆነ ውጤት በዋናነት የሚወሰነው በፖለቲካዊ ጥቅሞችና አቅሞች ይሆናል። ይህ የሕዳሴው ግድብ አሞላል ድርድርም የሚወሰነው በዚሁ ነው። የዚህን ድርድር ሒደትና ውጤት በቴክኒካዊ ተደራዳዊዎቹ አቅምና አድማስ ብቻ መወሰን የድርድሩን ክብደት አለመረዳት ነው።


ለመሆኑ የሕዳሴው ግድብ ሲጀመር የነበሩት ሁኔታዎች ማለትም (ሀ) የኢትዮጵያ እና የግብጽ ውስጣዊ ሁኔታ፣ (ለ) ቀጣናዊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አሰላለፍ እና (ሐ) ወቅታዊ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችና ቁመናችን ዛሬ ካለው ጋራ ተመሳሳይ ናቸው? የትኛው ሁኔታ ተለወጠ፣ የተለወጠውስ የኢትዮጵያን የመደራደር ቁመና በሚያጠነክር መልኩ ነው ወይስ በሚጎዳ አቅጣጫ? እነዚህን ጥያቄዎች በርትእና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ለመመለስ መሞከር የድርድሩን ሒደትና ውጤት ከአርበኝነት መንፈስ በዘለለ፣ የፖለቲካ ነጥብ ከማስቆጠር በራቀ መንገድ ለመረዳት ይርዳን ይሆናል። በሁሉ ጉዳዮች ላይ ወደ ዝርዝር መግባት ሳያስፈልግ፣ እስቲ ነገሩን በንጽጽር ለማየት እንሞክር።


(ሀ) የኢትዮጵያ እና የግብጽ ውስጣዊ ሁኔታ
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር ግብጽ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ነበረች። የፖለቲካ አመራሩ ግንባታውን በተመለከተ ወጥ የሆነ ስልት ነድፎ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ውስጣዊ መረጋጋት አልነበረው። ነባሩን ፕሬዚዳንት አስሮ፣ አዲስ የተመረጡትን የኋላ ኋላ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ግዞት በማውረድ በሚጠናቀቅ ውስጣዊ ማዕበል አቅሉን ስቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያን ግድብ መሥራት በተመለከት በተቀጣጣይ ቃላት አርበኝነትን ከመግለጽና ከመፎከር ያለፈ ዲፕሎማሲያዊም ይሁን ሌላ የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ሳይችል ቀረ። የፖለቲካ ቀውሱ ያቀጣጠለው የኢኮኖሚ ድቀት፣ ከነአሜሪካ ፊት መንሣት ጋራ ተጣምሮ የግብጽ ኢኮኖሚም የአገሪቱን አመራሮች እንቅልፍ የሚነሣ ሆኖ ሰነበተ። በዲፕሎማሲው መስክም ሌላው ቀርቶ በአረቡ ዓለም ጭምር ግብጽ ተሰሚነቷ ተቀዛቀዘ፤ አልፎም የእጅ አዙር የቀጣናዊ ፖለቲካ የፍልሚያ ሜዳ ሆነች ።


ካይሮ እንዲህ ስታጣጥር፣ ኢትዮጵያ ግድቡን ያለማንም ፈቃድ በማስጀመር ግዳይ ልትጥል ስታደባ ነበር። ተሳካላት። ኢትዮጵያ መጠኑ ቢለያይም በኢኮኖሚ እድገት ላይ ነበረች። በቀላሉ የሚገኘው የቻይና ብድር ኢኮኖሚውን ያንቀሳቅሰው ነበር። የውጭ ብድራችንም ቢያጎብጠን እንጂ የሚሰብረን ደረጃ አልደረሰም ነበር። የፖለቲካ አፈናው እየበረታ ቢሔድም የሕዝብ ተቃውሞ መንግሥትን የሚያርበተብት ደረጃ ገና አልደረሰም ነበር። የፖለቲካ አመራሩ በአንድ በኩል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የኅይል አቅርቦት ለማሟላት ዘላቂ መፍትሔ ፍልጋ ሲዳክር፣ በሌላ በኩል ትልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመር ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባልተናነሰ አመራሩ ከተዘፈቀበትን የቅቡልነት እጦት ለመውጣትም እንደሚረዳው የተረዳበት ወቅት ነበር። ስለዚህ በኢትዮጵያ በኩል የግድቡን ሥራ በቶሎ ለመጀመር የሚያነሳሱ በቂ ውስጣዊ እና ውጫዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መግፍኤዎች ነበሩት ማለት ነው። በዲፕሎማሲ መስክ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁልፍ ከፍተኛ ተሰሚነት ካላቸው የአኅጉሪቱ መሪዎች ተርታ የተሰለፈችበት ጊዜ ነበር። ብዙ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም፣ እዚህ ከሞላ ጎደል ምቹ ሊባል በሚችል ከባቢ ውስጥ ነው ፣ “ከዚህ የተሻለ ጊዜ አናገኝም” በሚል ፖለቲካዊ ስሌት፣ የውጭ ብድር ባልተገኘበት በራሳችን አቅም እንገነባዋለን ተብሎ ወደ ግንባታ የተገባው።


በድምሩ፣ ግድቡ ሲጀመር የነበረው ሁኔታ ለኢትዮጵያ ምቹ ነበር። የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በውሳኔያቸው ስልታዊንት ሊመሰገኑ ይገባል። እንዲያም ሆኖ፣ ዕድል ከእርሳቸው ጋራ እንደነበረችም አለመዘንጋት ነው። “ጎበዝ ጀነራል እንደሆነ አውቃለሁ፤ ለመሆኑ እድለኛ ነው?” ብሎ ጠየቀ አሉ ናፖሊዎን ቦናፓርት፣ ስለአንዱ ጀነራሉ።


ዛሬ ያለው የሁለቱ አገሮች ውስጣዊ ሁኔታ ያለፈው ተቃራኒ ነው። ዛሬ የግድቡ ውሃ አሞላል ድርድር በሚካሄድበት ድባብ ግብጽ የፖለቲካ ማዕበሏን “ጸጥ አድርጋ” ተረጋግታለች፤ የፖለቲካ አመራሩም በግብጽ ብሔረተኝነትና በወታደራዊ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ጥቅም በተሳሰረ ቡድን እጅ ውስጥ ተጠቃሎ ገብቷል። ስለዚህ አመራሩን መገዳድርና ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን መፍጠር ቀርቶ፣ የአል ሲሲን አትኩሮት የሚያናጥብ ዝንብ ካይሮ ላይ አይበርም። በኢኮኖሚውምና በዲፕሎማሲውም ግብጽ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች መለዋወጥ የተነሣ ድምጿም አቅሟም እየጨመረ ነው።


በተቃራኒው፣ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ለውጥ ወጀብ እየተዋከበች ያለች አገር ነች። ከፍጹማዊ አፈና ወደ ተሻለ ሥርዓት ለመሸጋገር ቃል በተገባበት የሽግግር ሙከራ ተስፋና መዘዞች የተወጠረች፣ በፖለቲካ ምኅዳሯ ብዙ ተገዳዳሪዎች እንዳሻቸው የሚርመሰመሱባት፣ ወደ ፊት ለመራመድ በማመንታት ላይ ያለች አገር ነች። የፌደራሉን መንግሥት ይሁነኝ ብለው ለማዳከም የሚሠሩ የፖለቲካ ኅይሎች እና አክራሪ የዘውግ ብሔረተኞች የአገሪቱን ኅልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉበት ዕድል አካል ገዝቶ ግዘፍ ነስቶ የሚታይባት አገር ነች፣ ስለግድብ አሞላል የምትደራደረው ኢትዮጵያ። ለእነዚህ ኅይሎች የግድቡ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማሳጣት የሚጠቀሙበት የፖለቲካ መሣሪያ እንጂ በፖለቲካቸው ውስጥ ስታራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ አይደለም።


የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን የተቆጣጠረው አመራር በአንድ በኩል አገራዊ ብሔረተኝነትንና አንድነትን ለመኮትኮት ሲጥር፣ በሌላ በኩል ከአክራሪ የዘውጌ ብሔረተኞቹ ጋራ በራሳቸው የጨዋታ ቀመር ለማሸነፍ የሚውተረተር ነው፣ ገና ረግቶ ረግጦ ያልቆመ ቡድን ነው። አመራሩ፣ ጸጥታን ለማስከበር በመረጠው ስልት ከፍ ያለ የፖለቲካ ዋጋ እየከፈለ ያለም ነው። አመራሩ ግድቡን ማስጨረስና ለፍሬ ማብቃት ኢኮኖሚያዊም ፖለቲካዊም ጥቅም ስለሚገኝበት ሥራው ቢያጓጓው የሚገርም አይሆንም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራር፣ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ የማይናቅ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አለው። ይህ ድጋፍ በዋናነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋራ የተያያዘ ቢሆንም አንድ የመደራደሪያ አቅም ምንጭ መሆኑ አያጠራጥርም። በዲፕሎማሲው ኢትዮጵያ አሁንም የማይናቅ ተሰሚነት አላት። ልዩነቱ አሁን ግብጽም አንሰራርታ፣ ጊዜም ረድቷት አቅሟን በጣም እያፈረጠመች ነው።


የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፈተና የበለጠ የሚያባብሰው ደሞ የኢኮኖሚው ውጥንቅጥ ነው። የውጭ ምንዛሪ እጥረታችን ብቻውን ትልልቆቹን የኢኮኖሚ ዘርፎች ከሚያቀዛቅዝበት ደረጃ ደርሷል፤ ሥራ አጥነት በአንድ በኩል ለፖለቲካ ቀውሱ ማገዶ ሲያቀርብ፣ እዚያ በዚያው ደሞ የኢኮኖሚ ሸክም ሆኖ እየገዘፈ ነው። አዲሱ አመራር፣ አገሪቱ የተበደረችው ብድር ራሱን መሸከመ ከማይችልበት ደረጃ በመድረሱ፣ ቻይናም ፊት መንሣት በመጀመሯ፣ ፊቱን ወደ ምዕራባውያኑ አበዳሪዎች መመለሱ ብዙ ምርጫ ያለው ጉዳይ ሆኖ አልታየውም። ርዕዮተ ዓለማዊው ዝርዝር ይቆየንና፣ የኢሕአዴግ አመራር በሕይወቱ የመጨረሻ ወራት ኢኮኖሚውን ለውጭ ባለሃብቶች መክፈት እንደሚገባ አምኖ ኑዛዜውን ትቶ ነበር። እነሆ እየሆነ ያለውም እርሱ ነው፤ ለውጡ አዲሱ የመኪናው ሹፌር ፈጥኖ ማሽከርከሩ ብቻ ይመስላል። ይህ ያስፈነጠዛቸው የምዕራቡ አበዳሪዎችና ኮርፖሬሽኖች ለመኪናው ነዳጅና መለዋወጫ እያቀረቡ ነው። ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ያገኘችው ለሦስት ቢልዮን ጥቂት ፈሪ ብድር ሌላው ቀርቶ ዜናው ራሱ ከባድ ነበር። የፖለቲካ አመራሩ ይህ ብድር የሚፈልገው ብቻ ሳይሆን ሊተወው የማይችለው ጭምር እንደሆነ በማመን፣ ከነጓዙ ከነጉዝጓዙ በእልልታ ተቀብሎታል። እልልታው ግን ብድሩ ኢኮኖሚውን ያተርፈዋለ፣ ያሳድገዋለ በሚል ተስፋ ለወደፊት ስኬት የተሰጠ ቀብድ ነው።


እዚህ ላይ አንድ መሠረታዊ ልዩነት መጠቀስ አለበት። ግብጽ በውስጣዊ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ ጣልቃ በመግባት ግብጽን የባሰ የማዳከም ታሪካዊ ልምድም ሆነ ምቹ ስልታዊ ሁኔታ ያላትም። በተቃራኒው ግን፣ ግብጽ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በመርዳትና በማስታጠቅ አገሪቱን ለማዳከም የመሞከር ታሪካዊና የቅርብ ልምድም፣ ፍላጎትም አቅምም አላት። አሁን በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋት ለማቀጣጠል አትፈልግም፣ አትሠራም ብሎ ማመን ነሆለልነት ይሆናል። እኔ እንደውም የምሰጋው፣ ግብጽ ከዚህ ድርድር ውጤት ባሻገርም በፖለቲካችን ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎቷ ሊጨምር ይችላል ብዬ ነው።


በድምሩ ዛሬ የግድቡ አሞላል ድርድር ሲካሄድ፣ ግብጽ እጅግ በተሻለ ውስጣዊ መረጋጋትና ጥንካሬ፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ አቋም ላይ ናት።

(ለ) ቀጣናዊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አሰላለፎች

ኢጋድ፣ አፍሪካ ኅብረት እና መካከለኛው ምሥራቅ። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ቀድሞም አሁንም የኢትዮጵያ ጠንካራ ምሽጎች ናቸው።


የሕዳሴ ግድብ ሲጀመር ኢትዮጵያ በቀጣናው አልፎም በአፍሪካ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላት አገር ነበረች ። ከኤርትራ ጋራ ከነበረው ውጥረት እና የእጅ አዙር መጎነታተል ውጭ፣ ኢትዮጵያ የክፍለ አኅጉሩ ትልቅ አገር ተደርጋ ትቆጠር ነበር። በዚህ ተጽዕኖ ነበር ኤርትራን በኢጋድ እና በተመድ ሳይቀር እንደትነወር ለማድረግ ያደረገችው ጥረት የተሳካላት።


በወቅቱ በግብጽና በኢትዮጵያ ግንኙነት የማይናቅ ሚና የምትጫወተው ሱዳን፣ ከሞላ ጎደል ሁል ጊዜም ከኢትዮጵያ ጋራ የነበራት ግንኙነት ጥብቅ ነበር። በአባይ ተፋሰስ አገሮች ድርድሮችም ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ብቻ ሳይሆን ሱዳንን ጭምር ከጎኗ ለማሰለፍ የቻለችበት ዘመን ነበር። የመለስ እና የአልበሽር መቀራረብ ሳይዘነጋ፣ ሱዳን የኢትዮጵያ የስጋት ምንጭ የመሆን እድሏ ዜሮ ነበር። ኢትዮጵያ ለቀጣናው እና አልፎም ለአኅጉሩ ጸጥታ የምታበረክተው አስተዋጽኦም እውቅና የሚሰጠው ነው። ይህ እንደቀጠለ ነው።


ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም ጋራ ቢሆን ኢትዮጵያ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ነበራት። ግብጽን መገዳደር የሚፈልጉት አገሮች ኢትዮጵያን ለማማለል መፈለጋቸው ዛሬም የቀጠለ ነው። ኢትዮጵያ ሚዟኗን ጠብቃ ለመጓዝ ሞክራለች። የመከከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለኢትዮጵያ ብቸኛ የባህር ወደብ የምታቀርበውን ጂቡቲን ለመቀራመት የሚደረገው ፉክክር ስትራቴጂካዊ ፋይዳና ዳፋ የሚተርፋት ቢሆን ነገሩን በዝግታ ለመያዝ የሞከረች ይመስላል፤ ቢያንስ ወደ ግጭት አልገባችም፣ አገልግሎቱም አልተቋረጠባትም።


በቀጣናዊ ጉዳዮች እና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋራ በተያያዘ ኢትዮጵያ ያላት ቦታ አሁንም በመሠረቱ አልተቀየረም። ከኤርትራ ጋራ የተጀመረው አዲስ ግንኙነት የሚያስከትለውን ክፍለ አኅጉራዊ ለውጥ አሁን ደምድሞ መገምገም ያስቸግራል። አሁን ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያን አቋም የሚያኮስስ አይመስለኝም።


አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚሞክሩት ክፍለ አኅጉራዊ ትብብርን የማጠናከር አጀንዳ በአገሮቹ ማካከል የነበረውንና የሚቀጥለውን መልከ ብዙ ፉክክር እንዴት እንደሚቀርጸው ገና የምናየው ነው። አሁን ባለበት ግን የኢትዮጵያን ቦታ ከግብጽ ፍላጎት አንጻር የሚጎዳ አይመስልም።


አሁን ባለው ሁኔታን በግድቡ ጋራ በቀጥታ የሚገናኝ ነበር ቢኖር የሱዳን ውስጣዊ ለውጥ ያስከተለው የሱዳን የአቋም መሸጋሸግ ነው። ሱዳንን የሚመራው አዲስ አመራር አገሪቱ የተጣለባትን ፈርጀ ብዙ ማዕቀብ ለማስነሣት፣ የአገሪቱን ስም “ከነውር” መዝገብ ለማስፋቅ ደጅ እየጠና፣ እጅ መነሻ እያቀረበ ነው። አልበሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኖች ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመስጠ የተስማማውም በዚሁ ቀመር ነው። አዲሱ የሱዳን አመራር ከእሥራኤል ጋራ የጀመረው ድሪያ ሱዳን ለረጅም ዓመታት አይታው ወደማታውቀው “ሽርሽር” እየገባች ለመሆኑ የማያሻማ ማረጋገጫ ነው። እዚህ ሒሳብ ውስጥ፣ ሱዳን በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ሚዛኗን ጠብቃ ለመጓዝ ትሞክር ይሆናል፤ አሜሪካ እና እሥራኤል ከግብጽ ጎን ሲቆሞ ግን ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋራ ትቆማለች ብሎ መጠበቅ አይገባም።(በቀጣዩ ክፍል እመለስበታለሁ።) ከዚህ አንጻር፣ የግድቡ ድርድር በተመለከተ፣ በሦስቱ አገራት መካከል የነበረው የኢትዮጵያ/ሱዳን የአቋም መቀራረብ ተለውጦ ሱዳን አቋሞቿን እያስተካከለች በድርድሩ ከግብጽ ጎን ትቆም ይሆናል። በቅርቡ አንዲ የሱዳን ተደራዳሪ ቡድን አባል ለቢቢሲ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ልብ ላለ ይህን ግምት እንደተፈጸም ሊቆጥረው ይችላል። [ንባብዎን ከታች ይቀጥሉ]

Sudan PM Abdulla Hamdok and Secretary State Pompeo in Washington DC


በግብጽ በኩል፣ የሕዳሴው ግድብ ግንባት ሲጀመር፣ ከውስጣዊ የፖለቲካ ቀውሷ ጋራ በተያያዘ በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ የነበራት ተጽዕኖ ቀንሶ ነበር። አሁን ግብጽ ወደ ቀደሞው የዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ተሰሚነቷ ተመልሳለች፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ተጽዕኗቸውን በገንዘብ እየገዙ የሚያስፋፉትን የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ማቆም ባትችልም። ኢትዮጵያና ግብጽ ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ቢገቡ ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋራ ወዳጅነታቸውን ያጠነከሩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ኢትዮጵያን የእጅ አዙር ፍልሚያቸው ሜዳ ከማድረግ ባይቆጠቡም ቢያንስ አሁን ባሉበት፣ ስለግድቡ ከግብጽ ጎን ቆመው ጫና ስለማድረጋቸው አልተሰማም።


በድምሩ፣ በቀጣናዊ ፖለቲካና ጸጥታው ላይ ይህ ነው የሚባል የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም የሚያዳክም ለውጥ አልታየም፤ ከሱዳን የቅርብ ቀናት የአቋም መሸጋሸግ በቀር። እዚህ ሰፈር፣ ለኢትዮጵያ ብዙው ነገር አልተለወጠም። ግብጽ ግ ን ወደ ቀደመ የዲፕሎማሲና የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ አቋማ ተመልሳለች ማለት ይቻላል።

(ሐ) ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ቁመናችን
ስለ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳዎች ሲነሳ ብዙ ጉዳዮችን መዳሰስ ይቻላል። ሆኖም ለአሁኑ ድርድር የኅይል አሰላለፍ ቀጥተኛ ፋይዳ አለው ባልኩትን የአሜሪካ ሚና ላይ ብቻ አተኩራለሁ።


የግድቡ ሥራ ሲጀመር ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚመራው “ጸረ ሽብር ዘመቻ” የአፍሪካ ቀንድ ዋና “አጋር” ነበረች። ሱማሊያ የሽብርተኞች መናኸሪያ እንዳትሆን የመጠበቁ ሥራ በውክልና የተሰጠው ለኢትዮጵያ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጠ/ሚ መለስ በኢኮኖሚ ፖሊሲ እና በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት ከምዕራቡ ዓለም የሚያጡትን እገዛ መልሰው “የሚሸምቱበት” “መገበያያ” ስሙ “ዓለም አቀፍ የጸረ ሽብርተኝነት አጋርነት” ይባል ነበር። ከዋሺንግተን የወቀሳ ጥሪ በደረሳቸው ቁጥር፣ በሞቃዲሾ ስታዲየም ሰፍሮ ከነበረው የኢትዮጵያ ጦር ጥቂቱን በመመለስ ያስፈራሩ ነበር እየተባለ ይቀለድ ሁሉ ነበር።


ግድቡ ሲጀመር ዓለም ባንክም ሆነ አሜሪካ ጥርጣሬና ስጋታቸውን ለኢትዮጵያ ሳይገልጹ አላለፉም ነበር። በወቅቱ ከዚያ ያለፈ እርምጃ የሚያስወስዳቸው፣ “ከጸረ ሽብርተኝነት አጋርነቱ” የሚበልጥ ፖለቲካዊም ሆነ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ግን አልነበራቸው።
ግድቡ ሲጀመር፣ ግብጽ በራሷ ውስጣዊ ንዝረት አረፋ እየደፈቀች ነው። የኦባማ አስተዳደር ለግብጽ መንግሥት የተለመደውን ዓመታዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳረጎት ለመስፈር እንኳን ያመነታበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ፣ ግብጽ ራሷን ከቀውስ ካዳነች ለአሜሪካ ሸክም እንዳቀለለች ያህል ተቆጥራ ነበር። የግብጽ ጀነራሎች በኦባም ቂም እንደቋጠሩ፣ ትራምፕን በእልልታ ተቀበሉ። እውነትም ትራምፕ ለግብጽ የዲፕሎማሲ ማንሰራራት ከሰማይ የተላከ መፍትሔ ነበር። ሲሲ እና ትራምፕ አምባገነንነታቸው ብቻ ሳይሆን ኮከባቸውም የገጠመ መሰለ። ለትራምፕ፣ ከእሥራኤል ጋራ ሰላም ያሰፈነ የአረብ አገር ሁሉ ስትራቴጂካዊ ወዳጃቸው ነው። የዚህ ወዳጅነት ውስጠ ወይራ ኢራንን መቃወምን ጭምር ሊያካትት ስለሚችል።


ለሲሲም ከእሥራኤል ጋራ መልካም ግንኙነት መቀጠል ታሪካዊው የግብጽ የተደማጭነት ምንጭ ነውና የሚተው አይደለም። በምላሹ አሜሪካ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለአገሮች ከምትሰጠው ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እገዛ ከአፍጋኒስታን ቀጥቶ ትልቁን ድርሻ የምትወስደው ግብጽ ነች። ትራምፕ ወታደሮቹን ከአፍጋኒስታን ጠቅልሎ ለማውጣት፣ ለውጭ የሚሰጠውን እገዛም ለመቀነስ በሚታትርበት በዚህ ወቅት፣ ግብጽ ተፈላጊነቷን ማሳደግ እንዳለባት አታጣውም። ጊዜም ከግብጽ ጋራ ይመስላል። የትራምፕ ሴት ልጅ ባል፣ አቶ ኩሽነር የእሥራኤልንና የፍልስጤማውያንን ጠብ ይፈታል ያለውን “የሰላም እቅድ” በአማቹ በትራምፕ በኩል አቅርቧል። ትራምፕ “የሰላም እቅዱ” መሳካት የዓለም አቀፍ አሻራቸው ቁልፍ ስኬት እንዲሆን ይመኛሉ አሉ። እንግዲህ ለግብጽ አዲስ የወረደው መና ይህንን “የሰላም እቅድ” ቀሪው የአረቡ ዓለም ሲሆን እንዲቀበለው፣ ካልሆነም እንዳይቃወመው ግፊት የማድረግና የማግባባት ሥራ ነው።


ትራምፕ ይህን የመስለ ሲሳይ ለግብጽ ይዘው ሲመጡ፣ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መደራደሪያዋ የነበረውን “ዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት ዘመቻ” ግን ገሸሽ እያደረጉት ነው። በቅርቡም አገራቸው ከዚህ መሰሉ ትልቅ ትብብር ጠቅልላ እንደምትወጣ ወይም በዝቅተኛ መጠን ብቻ እንደምትሳተፍ እቅድ መኖሩ ይፋ ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያን ከአሜሪካ “ስትራቴጂክ አጋርነት” ወደ አንድ ተራ አጋርነት የሚያወርዳት ሆኗል። የግድቡ ሥራ ሲጀመር “ስታቴጂክ አጋር” የነበረቸው ኢትዮጵያ ዛሬ የውሃ ሙሌቱ ሲያከራክር ወደ ተራ አጋርነት ወርዳለች። በተቃራኒው፣ ግድቡ ሲጀመር ከአሜሪካ ጋራ የነበራት ግ ንኙነት ተቀዛቅዞ የነበርቸው ግብጽ፣ የውሃ ሙሌቱን ስትደራደር በአሜሪካ (በአንጻራዊነት) በጣም የምትፈለግ ስትራቴጂክ አጋርነቷ የታደሰላት አገር ሆናለች። ሲሲም በዚህ ጉዳይ እድለኛው ጀነራል ናቸው።


ኢትዮጵያና ግብጽ አንድ አንድ “እድለኛ ጀነራል” ኖራቸው ማለት ነው?

ከወጪ ቀሪ
ነገራችንን ለመጠቅለል፣ የሕዳሴው ግድብ ግንባት የተጀመረበት ከባቢ እና ዛሬ የውሃ አሞላሉ ድርድር የሚካሄድበት የየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች የተለያዩ ናቸው። ከውጪ ቀሪ፣ ግድቡ ሲጀመር የነበረውን ሁኔታ ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በሚገባ በዝብዛዋለች። አትርፋበታለች።


በግድቡ ሥራ መጓተት የተነሣ የገባንበት የውሃ አሞላል ድርድር ወቅት ግን ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ይልቅ ለግብጽ የተመቸ ነው። ይህንን እውነታ መቀበል ላቃተው ሰው፣ ኢትዮጵያ የአሜሪካና የዓለም ባንክን አደራዳሪነት ተገዳ መቀበሏ እውነት አይመስለው ይሆናል። የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቂልነት የገቡበት ምርጫ መስሎ የሚታያትም አትጠፋም። ድርድሩ አቋርጦ መውጣ ራሱ ዋጋ የማያስከፍል፣ የአርበኝነት ስሜት ብቻ የሚበቃው ምርጫ ይመስልም ይሆናል። ይህ ሁሉ አርዳድ ትክክል አይመስለኝም። (ወደ ኋላ ተመልሶ መከራከር ካስፈለገ፣ ክርክሩ መሆን ያለበት የነዓለም ባንክን ብድር ሳንቀበል የኢኮኖሚ ቀውሱን ለመታደግ የምንችልበት አማራጭ ነበር ብሎ መከራከር ነው። ይህን ለባለሞያዎቹ እተዋለሁ። እርሱም ቢሆን፣ ቢያንስ ከግድቡ ድርድር ጋራ በተያያዘ የረፈደበት ክርክር ይመስላል።)


ከዚያ ይልቅ፣ አሁን መነሣት ያለበት ጥያቄ፣ ካለው ተጨባጭ ውስጣዊና ውጫዊ እውነታ አንጻር፣ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ሊያስጠብቁልን የሚችሏቸውና የሚገቧቸው ቁልፍ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው የሚለው ነው። የፖለቲካ አመራሩ (የቱንም ያህል በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ብንለያይ) አገራችንን ወክሎ ትልቅ ውሳኔ የሚያስተላልፍ ነውና ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች የቀነሱበትን የድርድር አቅም የሚያካክስ ሕዝባዊ ድጋፍና ጫና ያስፈልገዋል ባይ ነኝ። ተደራዳሪዎቻችንም እንዲሁ።


በመጨረሻ የድርድሩ ውጤት ምንም ቢሆን፣ ተደራዳሪዎቹ ያለፉበትን መናገራቸው፣ ነጥብ አስቆጣሪውም “በብዬ ነበር” ስሜት መሞላቱ፣ ተመራማሪዎችም ወደ ታሪክ ንጽጽር መመለሳቸው አይቀርም። የድርድሩን እውነተኛ ትርፍና ኪሳራ የምናውቀው በታሪክ መነጽር ወደኋላ ስንመለከተው ብቻ ነው። ኢትዮጵያም ሁለት ወሳኝ የታሪክ ወቅቶች (ግድቡ የተጀመረበት እና የአሁኑ ድርድር የሚካሄደባቸው) ከፈጠሩላት ምቹ ሁኔታዎች እና አስቸጋሪ ማነቆዎች የምታተርፈውን ይዛ ትቀጥላለች፤ ፍሬውን እየበላች፣ እዳውን እየከፈለች። አባይም፣ የማንሻገረው የውሃ፣ የፖለቲካና የሕይወት ወንዝ እንደሆነ ይቀጥላል! አባይን ተሸጋሮ አባይ አለ ወይ?

በመስፍን ነጋሽ [ከዋዜማ ራዲዮ]