ዋዜማ- የቤንሻንጉል ጉሙዙ ተቃዋሚ የምክር ቤት አባል ዮሐንስ ተሰማ አዲስ የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባቸው ዋዜማ ሰምታለች፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ቦዴፓ) ተወካዩ ዮሐንስ ተሰማ፣ ከሽብር ጋር በተያያዙ ክሶች ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን ከፈቀደላቸው በኋለ፣ ከመሬት ሊዝ ጋር በተያያዘ ነባር ክስ የእስር ቅጣት የተጣለባቸው ዮሃንስ፣ አሁን ደሞ ሦስት አዲስ ተደራራቢ ክሶች እንደቀረቡባቸው ዋዜማ ተረድታለች።

የክልሉ ዓቃቤ ሕግ በዮሐንስ ላይ ያቀረባቸው ኹለቱ ክሶች ከሽብር ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፣ አንዱ ክስ ደሞ በመተከል ላይ ከሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ “የክልሉን የግዛት አንድነት የመንካት” ወንጀል ነው። ዮሐንስ አዲስ ክስ የተመሰረተባቸው፣ ከአወዛጋቢው የክልሉ ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ላይ በተያያዘ በተጠረጠሩበት ወንጀል ዋስትና ከተፈቀደላቸው ከአንድ ወር በኋላ ነው፡፡

የአሶሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓርብ፣ መስከረም 23፣ 2018 ዓ፣ም ባዋለው ችሎት፣ ዮሐንስ በመጀመሪያዎቹ ክሶች በ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ ማሳለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡


የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳበት ክስ በተጨማሪ፣ ከከተማ መሬት ሊዝ ይዞታ ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰባቸው የቆየ ክስ አምስት ዓመት ከ10 ወር እስር ስለተፈረደባቸው ከእስር ሳይፈቱ እንደቀሩ አይዘነጋም፡፡

ዮሐንስ የዋስትና መብት ካገኙባቸው “የክልሉን ሕገመንግሥት ለመናድ የመንቀሳቀስ” እና “ከውጭ ኃይሎች ጋር ግንኙነት የመፍጠር” ወንጀሎች በተጨማሪ፣ በሦስት ተደራራቢ ወንጀሎች ተከሰዋል፡፡


የክልሉ ዓቃቤ ሕግ በዮሐንስ ላይ ተደራራቢ ክሶችን ያቀረበው፣ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለአሶሳ እና አካባቢዋ ተዘዋዋሪ ችሎች መሆኑን ዋዜማ የተመለከተችው የክስ መዝገብ ያስረዳል፡፡

የክልሉ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው አንደኛው ክስ፣ የሺናሻ ብሄረሰብ ጥቅም በክልሉ ውስጥ እየተከበረ አይደለም” በሚል፣ “መተከል ዞንን ከአማራ ክልል ጋር በመቀላቀል በኋላ ላይ ከክልሉ ነጥለን አዲስ ክልል እንመሰረታለን” በሚል አጀንዳ ዙሪያ የመተከል አስመላሽ ከተባለው ኮሚቴ አባላት ተነጋገረዋል የሚል እንደሆነ ተረድተናል።

ዮሐንስ መተከል ዞንን ወደ አማራ ክልል “ለማስገንጠል” ከመተከል አስመላሽ ኮሚቴ እና ያለለት ወንዲዬ ከተባለ ጋዜጠኛ ጋር ከ2013 እሰከ 2015 ዓ፣ም ድረስ እንደተገናኙ ክሱ ያብራራል፡፡ ዮሃንስ፣ መተከልን ወደ አማራ ክልል “ለመቀላቀል” አድርገውታል የተባለው እንቅስቃሴ፣ ሕገመንግሥቱን የሚጻረር ስለመሆኑ በክስ መዝገቡ ላይ በዝርዝር ተገልጧል፡፡

ተከሳሹ “የሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ እና ፌደሬሽኑ እንዲከፋፈል የሚያደርግ ተግባር” በመፈጸም እና “የሀገሪቱን የፖለቲካዊና የግዛት አንድነት በመንካት” ወንጀል እንደተጠረጠሩ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ አስረድቷል፡፡

ዮሐንስ የቀረቡባቸው ተጨማሪ ኹለት ክሶች የሽብር ወንጀሎች ሲሆኑ፣ ክሶቹ የቀረቡባቸው የሽብር ወንጀል ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ መሠረት ነው። በዚሁ የሽብር መዝገብ በኹለተኛነት የቀረበው ክስ፣ ተጠርጣሪው የፓርቲያቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የክልሉ ሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት፣ “የኦነግ-ሸኔ አሸባሪ ቡድን” አባል ነው ለተባለ የአጎታቸው ልጅ መረጃ ሰጥተዋል የሚል ነው፡፡

ዮሐንስ፣ የሽብር ቡድኑ አባል ነው ለተባለው የአጎታቸው ልጅ ጃል ህረቡ ገነቲ (ወይም በረዳ ሙለታ ገርቢ) ስለ መንግሥት ኦፕሬሽን ውሳኔ መረጃ በመስጠት ተጠርጥረዋል ይላል ክሱ። ተጠርጣሪው በ2105 ዓ፣ም በሥም ለተጠቀሰው የታጣቂ ቡድኑ አባል፣ “የመከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አባላት እየመጡ ስለሆነ፣ ካላችሁበት አካባቢ ሽሹ” በማለት እና በ2016 ዓ፣ም በተመሳሳይ በቡለንና ድባጤ ወረዳዎች የሰፈሩ የቡድኑ ታጣቂዎች “እንዲደመሰሱ” የጸጥታ አካላት የወሰኑትን ወሳኔ በስልክ በማስተላለፍ ለሽብርተኛ ቡድን በመረጃ እገዛ በማድረግ ወንጀል እንደተከሰሱ መዝገቡ ያብራራል።


በሦስተኛ የክስ መዝገብ የቀረበባቸው የሽብር ወንጀል ክስ፣ የሕገመንግሥት ትርጉም ከጠየቁበት የክልሉ ሕገመንግሥት ማሻሻያ መጽደቅ ጋር በተያያዘ፣ በግል የፌስቡክ ገጻቸው አሰራጭተውታል ከተባለ መረጃ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ዮሐንስ የክልሉ ምክር ቤት የካቲት 17፣ 2017 ዓ፣ም የጸደቁ የተለያዩ አዋጆችን መነሻ በማድረግ ያሰራጩት ቅስቀሳ፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት መሆኑ በክሱ መዝገብ ዝርዝር ላይ ተመላክቷል።

በዮሃንስ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ቅስቀሳ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል ከተባሉት ሦስት ሰዎች በተጨማሪ፣ የሽብር ወንጀል እንዲፈጸም በማነሳሳት ጭምር ተከሰዋል። የክልሉ የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ወንበር ብዛት ከ99 ወደ 165 ከፍ ማድረጉን ተከትሎ ነበር ዮሃንስ እና ሁለት የቦዴፓ ፓርቲን በክልሉ ምክር ቤት የሚወክሉ ተወካዮች በማሻሻያው ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ በማንሳት በፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት አቤቱታ ያቀረቡት። [ዋዜማ]