ዋዜማ ራዲዮ- በቀድሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመራ ቡድን ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች የምትጠቀምበትን ሁኔታ ማጥናት እንደጀመረ ከኢትዮጵያ የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያሳያል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሀገሪቱ ካሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገሪቱ አሁን ላይ የምጽዋ ወደብን በተቻለ ፍጥነት ወደመጠቀም እንደምትገባም ተናግረው ነበር ። ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች የምትጠቀምበትን ሁኔታ አስመልክቶ ጥናት የሚያደርግ የተለያዩ ዘርፍ ባለሙያዎችን የያዘ የጥናት ቡድንን የቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አምባሳደር ግርማ ብሩ እየመሩት ነው ። በጥናቱ ውጤት ላይም ኢትዮጵያ ምጽዋና አሰብን ስትጠቀም ምን አይነት ስትራቴጂ ይኖራታል ? ሁለቱ ሀገራትስ ከወደብ አንጻር ምን አይነት ግንኙነት ነው የሚኖራቸው ? የሚለው ጉዳይ ግልጽ ተደርጎ እንደሚቀመጥም ምንጮቻችን ነግረውናል ።
የወደቦቹ ኢኮኖሚያዊ አዋጭትነስ ምን ይመስላል ? የሚለው ጉዳይም እየተፈተሸ እንደሆነ ስምተናል ። የጥናቱን ሂደት ከሚያውቁ ባለሙያዎች እንደተረዳነው ኢትዮጵያ የአሰብንና ምጽዋ ወደብን መጠቀም ብትጀምር በጅቡቲ ላይ ያላትን ጥገኝነት ይቀንሰዋል። ባለሙያዎች ግን ዓስብና ምፅዋን መጠቀም እንደሚታሰበው ለኢትዮጵያ አዋጭ ላይሆን ይችላል።
ከምክንያቶቹ አንዱ የኤርትራ ወደቦች አሁን ላይ ያላቸው ይዞታና ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በፊት የነበራት የገቢና ወጪ ንግድ መጠን በእጅጉ ይለያያል። ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት እጅግ እያደገ ከመጣው የገቢና ወጪ ንግድ አንፃር የመርከቦቿ የጭነት አቅምም ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ ጨምሯል ።
ጅቡቲም በወደብ ላይ ብዙ ኢንቨስት ያደረገችው ከኢትዮጵያ የምታገኘውን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ።
ኢትዮጵያም ከዲፒ ወርልድ(DP World) ጋር በርበራ ድርሻ ወስዳ በአመት 1.3 ሚሊዮን ኮንቴነር የሚያስተናግድ ወደብ ለማልማት የተዘጋጀችውም ለዚሁ ነው ።
የኤርትራ ሁለቱ ወደቦች ደግሞ የኢትዮጵያን ግዙፍ የገቢ ንግድ በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተናገድ ብዙ እንደሚቀራቸው የሚሰራውን ጥናት በቅርበት የሚያውቁ ምንጮቻችን ያስረዳሉ ።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ካሏት 11 መርከቦች ዘጠኙ በእለት ከእለት ስራ ውስጥ ናቸው ። የሀገሪቱ ህዝብ ፤ የግንባታው እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ የገቢ እቃዎች ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ የመርከቦች የመሸከም አቅምም ጨምሯል ። የመርከቦች የመሸከም አቅም ሲጨምር ደግሞ በወደቦች ዳርቻ ያለው የማንሳፈፊያ ውሃማ ቦታ መርከቡን እንዲያንሳፍፍ ዝቅ ብሎ እንዲለማ ማድረግ ያስፈልጋል ፤ ካልሆነ መርከቡ ከመሬት ጋር ይላተማል ።
ጅቡቲ በቻይናውም ሆነ በዲፒ ወርልድ ያለማቻቸው የወደብ ዳርቻ ጭነታቸው የከበዱ መርከቦችን ማንሳፈፍ በሚያስችል ሁኔታ ጥልቀት እንዲኖራቸው ሆኖ ተሰርቷል። አሰብና ምጽዋ ግን የድሮ የኢትዮጵያን መርከቦች የመሸከም አቅምን ከግንዛቤ ያስገቡ ናቸው ።
በሌላ በኩል የወደቦች ዳርቻ በአንዴ የሚያራግፉ መርከቦችን የመያዝ አቅማቸውም ዝቅተኛ ነው። የጅቡቲ ወደብ በአንዴ 14 መርከቦችን እንዲያራግፉ የሚያስችሉ በርዞች (መቆሚያና ዕቃ ማራገፊያ) አሉት ። የኤርትራው የአሰብ ወደብ ግን የመርከቦች ክብደት ውስንነቱ እንዳለም ሆኖ ሰባት መርከቦች በአንዴ የሚያራግፉበት ዳርቻ ነው ያለው።
እነዚህ ሁሉ ጉድለቶች ቢኖሩም ኤርትራ ምጽዋ ወደብን ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዝግጁ ለማድረግ እየተጣደፈች ነው።
ኢትዮጵያም ወደቡን ለመጠቀም ዝግጁ ናት መባሉ የተጀመረው ዲፕሎማሲ ለመደገፍ ያለመ እንጂ የሀገሪቱን ንግድ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኤርትራ ለማዞር ዕቅድ እንደሌለ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመሩትና ከማሪታይም ጉዳዮች ባለሰልጣንና ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተው የጥናት ቡድንም እነዚህን የወደቦቹን ጎድለቶች እንዴት ማሻሻል ይቻላል የሚሉ ጉዳዮችን ጨምረው እየተመለከቱ ነው።
ምናልባትም ኢትዮጵያ ከወደቦቹ ላይ ድርሻ በመውሰድ ልታለማ የምትችልበት አማራጭ አብሮ እንደሚታይ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ስትጠቀም በክፍያ ይሁን አይሁን እስካሁን ባይገለጽም የጥናት ቡድኑ የወደብ ታሪፍ ጉዳይንም እንዲያጠና ታዟል ።
.ሁለቱ ሀገራት በእንዲህ አይነት መሰረተ ልማቶች ሲተሳሰሩም የሚመሩባቸውን ዝርዝር የፖሊሲ ሰነዶች ማዘጋጀት አምባሳደር ግርማ ብሩ ከሚመሩት ቡድን የሚጠበቅ ነው ።
[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]
https://youtu.be/8Aj_A8_r6x0