ዋዜማ ራዲዮ-መንግስት የተመረጡ የመንግስት ይዞታ ስር የነበሩ ድርጅቶችን በከፊል ለውጪ ኩባንያዎች ለመሸጥ መወሰኑን ከወራት በፊት አስታውቆ ነበር። ይህን ሂደት ለማቀላጠፍ የተሻሻለ የቴሌኮም አገልግሎት አዋጅ አስፈልጓል። አዲሱ አዋጅ የቴሌኮም ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እንዲቋቋም ያደርጋል። ኤጀንሲው ከፍ ያለ ስልጣን ይኖረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሊቀመንበር የሆኑበት የኢህአዴግ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አማካይነት ኢትዮ ቴሌኮም አብዛኛውን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው በአክስዮን ይሸጥ የሚል ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ይታወሳል።ይህን ተከትሎ የብዙ ሀገራት ግዙፍ የቴሌ ኮም አገልግሎት አቅራቢዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌ ኮም አገልግሎት ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው።
መንግስት የፕራይቬታይዜሽን ሂደቱን የሚከታተል ቴክኒካል ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ነው። የቴሌ ኮም አገልግሎት ላይ የግል ባለሀብቶች ወይንም ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ሁኔታ በአንድ አመት ውስጥ ጥርት ብሎ እንዲታወቅ አቅጣጫ መሰጠቱንም ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። ከዚያ በፊት ግን መወሰድ ባለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።
በሂደቱ ላይ ተሳትፎ እያደረገ ካለው የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጮቻችን እንደተረዳነው የቴሌ ኮም ዘርፉ ለነጻ ገበያ ክፍት ሲደረግ በርካታ ኩባንያዎች በተለያየ ዘርፍ አገልግሎት የመስጠት እድላቸው ሰፊ ስለሚሆን መንግስታዊ ሆኖ የሚቀጥለውን ኩባንያ ጭምር የሚቆጣጠር ተቋም ለማቋቋም እየተሰራ ነው።
በኤጀንሲ ደረጃ ሊቋቋም የሚችለው ተቆጣጣሪ ተቋም ተጠሪነቱ እንደከዚህ ቀደሙ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ሳይሆን በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን ታስቧል። በተቆጣጣሪ ኤጀንሲውና ተጠሪ በሆነለት አካላት መካከል የሀላፊነት ጣልቃ ገብነት አይኖርምም ተብሏል። ከዚህ ቀደም ኢትዮቴሌኮም በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ቁጥጥር ይካሄድበት እንደነበረ የሚታወቅና ይህም እንደማይቀጥል ተሰምቷል።
አዲስ የሚፈጠረው ተቆጣጣሪ ተቋም በኢትዮጵያ ወደፊት የቴሌኮም አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ኩባንያዎችን ከዋጋ ጀምሮ እስካልተገባ የገበያ ውድድር ውስጥ የመግባት አዝማሚያ ካለ ይቆጣጠራል። የተለያዩ የቴሌ ኮም አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ለኩባንያዎች ፍቃድ የመስጠት ስልጣንም ይኖረዋል። ከዚህም ሲያልፍ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የፍሪኩዌይሲ አሰጣጥ ጉዳይም በተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ሀላፊነት ስር ሊወድቅ ይችላል።
ለዚህም ሲባል ኢትዮጵያ እስካሁን ስትጠቀምበት የቆየችው የቴሌኮሚኒኬሽን አዋጅ እየተስተካከለ ነው። በአዋጁ ማስተካከያ ላይ ባለድርሻ አካላት ሁለት ጊዜ ውይይት አድርገዋል።
በአዋጁ ማሻሻያ ላይ ትልቁ ለውጥ የሚመጣው የሀገሪቱ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች እንዴት ነው በኩባንያዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት በሚለው ላይ ነው።እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ቢሊየን ዶላሮችን እያወጣች በተለያየ ጊዜ የቴሌኮም ማስፋፊያዎችን ሰርታለች። የትኛውም ኩባንያ የቴሌኮም አገልግሎት ሲሰጥ እነዚህን መሰረተ ልማቶች መጠቀሙ ስለማይቀር የመሰረተ ልማቶቹ አጠቃቀም በአዋጁ የሚመለስ ይሆናል።
ኢትዮ ቴሌ ኮም በእየአመቱ ከ25 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍን እያገኘ የመጣ ተቋም መሆኑ ይታወቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]