Konso
Konso

(ዋዜማ ራዲዮ)- በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚኖሩት ኮንሶዎች ቀደም ሲል በልዩ ወረዳ አስተዳደደር ስር የነበሩ ቢሆንም ከሦስት ዓመት ወዲህ ግን የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በተሰኘ አዲስ ዞን በወረዳ ደረጃ ተወስነው ተቀምጠዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የዞን አስተዳደር ይገባናል ጥያቄ አንስተው ከክልል እስከ ፌደራል መንግስት አቤቱታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም በዞን የመደራጀት የመብት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡

ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በማንነትና አስተዳደር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመፍታት ረገድ ጥሩ ታሪክ የለውም፡፡ የኮንሶዎች ጥያቄ ህገመንግስታዊ ቢሆንም አወንታዊ ምላሽ መስጠት አንድምታዎች ስላሉት ጥያቄውን ማዳፈኑን መርጧል፡፡ እንደ ኮንሶ ሁሉ በደቡብ ክልል ያሉ ሌሎች ብሄረሰቦችም ተመሳሳይ የአስተዳደራዊ ለውጥ ጥያቄ እንዳያነሱ ስጋት የገባው ይመስላል፡፡ ከኮንሶ ሌላ በክልሉ እስካሁንም የሚንከባለሉ ተመሳሳይ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የአስተዳደርዊ ጥያቄ ለብሄረሰቡ ተወላጆች ራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር፣ ከስራ ዕድል፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ከበጀት ድጎማ ጋር የሚቆራኝ ስለሆነ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳ አስተዳራዊ አከላልና የማንነት ጥያቄዎች በክልሉ የግጭት ምክንያት ቢሆኑም እስካሁን የኮንሶዎች ጥያቄ ወደ ይፋዊ ግጭት አላመራም፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ግን የኮንሶዎች ጥያቂ በቀላሉ የሚቀለበስ አይመስልም፡፡

ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አዘጋጅቷል-አድምጡት

 

ህገ መንግስቱ ከፀደቀ ጀምሮ በብሄር ፌደራሊዝም አወቃቀር ሳቢያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ብሄረሰቦች በአስተዳደር አከላለልናማንነት ዙሪያ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ኖረዋል፡፡ ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ግን በማንነትና አስተዳደር ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመፍታትረገድ እምብዛም ጥሩ ታሪክ የለውም፡፡ የብሄረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ፣ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚያከብር ሌትተቀን የሚሰብከው ኢህአዴግ ፣ለህጋዊ ጥያቄዎች ህገመንግስታዊ መፍትሄዎችን ከመስጠት ይልቅ በፖለቲካዊ እርምጃ ጥያቄዎችንማዳፈንን እንደሚመርጥ የሚያረጋግጡ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ በደቡብ ክልል እንኳ ከስልጤ ብሄረሰብ ማንነት ጥያቄ በስተቀርበሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ የተፈቱ ጥያቄዎች እምብዛም የሉም፡፡በተለይ በደቡብ ክልል አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎችቀዳሚ ከሚባሉት የግጭት ምክንያቶች የሚመደቡ እንደሆኑ በበርካታ ጥናቶች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

የሀገሪቱ ህገመንግስት ፀድቆ ደቡብ ክልል በክልል ደረጃ ከተዋቀረ ጊዜ ጀምሮ የኮንሶ ብሄረሰብ በልዩ ወረዳ አደረጃጀት ራሱን በራሱ ሲስተዳድር ቆይቷል፡፡ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ግን የክልሉ መንግስት ስምንት ብሄረሰቦችን በአንድ ላይ ያቀፈውን የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ሲያቋቁም ኮንሶ ከልዩ ወረዳነት ደረጃው ዝቅ ብሎ በወረዳ ደራጃ እንዲዋቀር መደረጉ ይታወሳል፡፡ የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በአሁኑጊዜ ያቀፋቸው ብሄረሰቦች ኮንሶ፣ አሌ፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ ደራሼ፣ ኩሱሜ፣ ሞሴና ማሽሌ ናቸው፡፡

ኮንሶዎች ግን ድሮ የነበራቸውን የልዩ ወረዳ አስተዳደራዊ ደረጃ ተነፍገው ከሌሎች ሰባት ወረዳዎች ጋር በአዲሱ ዞን ስር በወረዳ ደራጃእንዲተዳደሩ መደረጋቸው “ህገመንግስታዊውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ይጋፋል” በማለት በተከታታይ ቅሬታ ማሰማታቸውበተለያዩ የውጭ እና ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ አሁኑ ገፍቶ የመጣው የኮንሶዎች ጥያቄ ግን “የቀድሞው ልዩ ወረዳአደረጃጀት ይመለስልን” የሚል ሳይሆን “የዞን አስተዳደር ይገባናል” የሚል በመሆኑ ክልሉን ለሚመራው ደኢህዴንም ሆነ ለኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ራስ ምታት እንደሆነባቸው ግልፅ ነው፡፡

የብሄረሰቡ ተወካዮች ከጥቂት ጊዚያት በፊት እንደገና በተጠናከረ መንገድ ጥያቂያቸውን ቢያቀርቡም የክልሉ መንግስት በድጋሚ ውድቅአድርጎባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን በህገመንግስታዊ አግባብ እንዲፈታ በደቡብ ክልል ብቻ የተቋቋመው የብሄረሰቦች ምክርቤትም “አሁን ባላችሁበት አስተዳደራዊ አደረጃጀት ቀጥሉ” የሚል ውሳኔ ሰጥቷቸዋል፡፡ ተወካዮቹ በክልሉ ሳይወሰኑ ጉዳያቸውንለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡም “ጥያቄያችሁን በክልሉ መንግስት በኩል አልፎ መምጣት አለበት” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውይገልፃሉ፡፡

በህገመንግስቱ መሰረት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ለማቅረብ ከጠቅላላ ህዝቡ ውስጥ አምስት በመቶ ፊርማ ማሰባሰብ በቂነው፡፡ ኮንሶዎች ግን ከሃምሳ ሺህ ፊርማ በላይ በማሰባሰብ ከመስፈርቱ አልፈው በመሄድ ብቻ ሳይሆን ጥያቄውን በወረዳቸው ምክር ቤትበማፀደቅ ጥያቄው የብዙሃኑ ይሁንታ ያለው መሆኑን ለማሳየት ችለዋል፡፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የህገመንግስት ባለሙያዎች ግንውሳኔው የክልሉን ህገመንግስት የሚጥስ ኢፍትሃዊ ውሳኔ ነው በማለት ይተቹታል፡፡

ጥያቄው በክልሉ በሙሉ በሚኖረው ያልተፈለገ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣ አስተዳደራዊና የበጀት አንድምታ የተደናበረ የሚመስለውደኢህዴን እና በደኢህዴን የሚመራው የክልሉ መንግስት የህዝቡን እንደራሴዎች በሃሰት ፖለቲካዊ ክሶች እየወነጀለ ማሰሩን፣ ከስራማባረሩንና ማስፈራራቱን እንደተያያዘው ተወካዮቹ በተደጋጋሚ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ “ጥያቂያችን ሰላማዊናህጋዊ ሆኖ ሳለ የክልሉ መንግስት ልዩ ታጣቂ ኃይል አሰማርቶ ወከባና ማስፈራሪያ እያደረሰብን ነው” በማለትም ቅሬታቸውን ያሰማሉ፡፡

ኮንሶዎች በአዲሱ የሰገን አካባቢ ዞን ከተካተቱት ሌሎች ሰባት ብሄረሰቦች አንፃር ሲታዩ ከፍተኛ የህዝብ ብልጫ አላቸው፡፡ ስለሆነምበዞኑ መንግስታዊ ቢሮክራሲ ስር የሚገኙትን የስራ ዕድሎች፣ ፖለቲካዊ ሹመቶችንና ፌደራል መንግስቱ የሚመድበውን የበጀት ድጎማበቁጥር አናሳ ከሆኑት ብሄረሰቦች ጋር ለመጋራት ለመጋራት ስለተገደዱ ቀደም ሲል ያጣጥሙት የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትናፖለቲካዊ ስልጣን ሸርሽሮባቸዋል፡፡ ይህም የተጎጂነት ስሜት እንደፈጠረባቸው ዓሌ የማይባል ነው፡፡

Map of Konso
Map of Konso

ጥያቄው ህገመንግስታዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከህጋዊው መስፈርቶች አንፃርም ቢታይ ኮንሶዎች በዞን ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸውማስተዳደር የሚበዛባቸው አይደሉም፡፡ ከጠቅላላ ህዝቡና የተማረ ሰው ኃይላቸው ብዛት፣ ከመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ ከቆዳ ስፋት፣ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ከማንነት አኳያ ሲመዘን በዞን አስተዳደራዊ ዕርከን ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደርየሚያንሱ እንዳልሆኑ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡ ከአስር ዓመት በፊት በተደረገው ህዝብ ቆጠራ የኮንሶ ብሄረሰብ ህዝብ ብዛት ከሦስትመቶ ሺህ በላይ ነበር፡፡

ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ኮንሶዎች ላነሱት “የዞን ይገባናል” ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ቢሰጥ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስታዊ፣አስተዳደራዊ እንዲሁም የበጀት አንድምታዎች እንደሚኖረው ካለፉት ልምዶቹ እንደተገነዘበ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላልፍትሃዊውን ጥያቄ ማዳፈን የመረጠው፡፡

ደኢህዴን/ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ለኮንሶዎች ዞን አስተዳደርን ቢፈቅድ “ተመሳሳይ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ላሏቸው ሌሎችብሄረሰቦች ቀዳዳ መክፈት ይሆንብኛል” ብሎ ይሰጋል፡፡ ክልሉ ከሃምሳ ስድስት በላይ ብሄረሰቦችን በማቀፉ የራስን ዕድል በራስ የመወሰንጥያቄዎች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ለአብነት ያህል በወረዳ ደረጃ ተወስኖ የሚኖረው የጎፋ ብሄረሰብ ራሱን በዞን ደረጃ ለማስተዳደር አቤቱታ ካቀረበ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም የክልሉ መንግስት ግን “የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ” እንዳለ ነው፡፡

የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞንከመዋቀሩ በፊት የደራሼ ብሄረሰብ ራሱ እንደ ኮንሶ ሁሉ በልዩ ወረዳ ደረጃ ራሱን በራሱ ያስተዳድር ስለነበር አሁን ለኮንሶ ዞን ይገባኛልጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ቢሰጥ ደራሼዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ የማያነሱበት ምክንያት የለም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የፌደሬሽን ምክርቤት የዘጠኙንም ክልሎች ግጭት ካርታ ሲያስጠና  የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ትላልቆቹ ኮንሶ እና ደራሼ ብሄረሰቦች ይሁንታቸውንሳይሰጡበት በክልሉ መንግስት ውሳኔ ብቻ በጥድፊያ ስለመቋቋሙ  በቂ መረጃዎች አሉ፡፡

በሌላ በኩል ግን በደቡብ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች ከኮንሶዎች ያነሰ ህዝብ ብዛት እያላቸውም እንኳን በዞን አስተዳደር ራሳቸውንበራሳቸው የሚያስተዳድሩ ብሄረሰቦች መኖራቸው የደኢህዴን/ኢህአዴግ መንግስት መርህ አልባ፣ በተቃርኖ የተሞላና ራስን በራስየማስተዳደር መብትን እንደ አመቺነቱ የሚሸራርፍ መሆኑን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮንሶዎች ለህዝብ ተወካዮችምክር ቤት እና ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በደኢህዴን/ኢህአዴግ ጥላ ስር ያስመረጧቸው ተወካዮቻቸው ጥያቄውን ተፃረው በመቆማቸውህጉ ሚጠይቀውን ፊርማ አሰባስበውውክልናቸው እንዲነሳላቸው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውለኢህአዴግ-መራሹን መንግስት ተቃርኖ ሌላኛው ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

 

በዞን ደረጃ ራስን በራስ ማስተዳደር ከደቡብ ክልል በስተቀር በሀገሪቱ ሌሎች ክልሎች ህገመንግስታዊ ዕውቅና የለውም፡፡ በሀገሪቱህገመንገስት መሰረት እውቅና ያላቸው መንግስታዊ እርከኖች ፌደራል መንግስት፣ ክልላዊ መንግስት እና ወረዳ ብቻ በመሆናቸው ሌሎች ክልሎች ዞንን እንደ መንግስታዊ ዕርከን ያቋቋሙት ለአስተዳደራዊ አመቺነት ሲሉ ብቻ ነው፡፡ በደቡብ ክልል ብቻ ዞን ህገመንግስታዊየአስተዳደር እርከን ሆኖ የተደራጀው በሽግግሩ ዘመን የነበሩት አምስት ክልሎች በኋላ ላይ ተዋህደው የአሁኑን ደቡብ ክልል ሲመሰርቱትላልቅ ብሄረሰቦች ቢያንስ በዞን ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር እንዲካሱ ለማስቻል ታስቦ ነበር፡፡

ፌደሬሽን ምክር ቤት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከሚገኘው የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ደቡብ ክልልን ጨምሮበዘጠኙም ክልሎች የግጭት ካርታ እና ግጭት ትንተና ጥናት በበማካሄድ ዳጎስ ያለ ሰነድ ቢያዘጋጅም እስካሁን የብሄረሰብ ግጭትዓይነቶችንና ምክንያችን መሰረት ያደረገ ብሄራዊ የግጭት አፈታት ፖሊሲ መንደፍ አልቻለም፡፡ በሀገሪቱ እስካሁንም የብሄረሰብ ግጭቶችየሚፈቱት በፖለቲካዊና አስተዳደራዊ መንገድ ብቻ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም፡፡

ምንም እንኳን በብሄረሰቦች መካከልም ሆነ በብሄረሰቦችና በመንግስት መካከል የሚነሱ ግጭቶችን የመፍታት ህገመንግስታዊ ስልጣንየፌደሬሽን ምክር ቤት ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ፈጥኖ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን የሚወስደው ግን የስራ አስፈፃሚው አካልየሆነው ፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚንስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከፌደሬሽን ምክር ቤትጋር ተደራራቢ የሆነ ስልጣን ስለተሰጠው ተቋማዊ አለመግባባትና የሃላፊነት መደራረብን እንዳስከተለ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናት ያካሄዱት እነ ፕሮፌሰር ሳራ ስሚዝ፣ ዶክተር አሰፋ ፍስሃና ዶክተር ፀጋዬ ረጋሳ በተለያዩ ጥናቶቻቸው ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላላው ሲታይ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አልመጡም፡፡ ከኮንሶ ሌላበትግራይና አማራ ክልል ገፍተው የመጡት የወልቃይትና ቅማንት ህዝቦች አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎችም ኢህአዴግ-መራሹንመንግስት ውጥረት ውስጥ የከተቱት ይመስላል፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድ የኮንሶዎች ጥያቄም በቀላሉ የሚቀለበስ አይመስልም፡፡.