- መመሪያው በቀበሌ ቤት ግቢ ለ40 ዓመት የኖሩ ዜጎችን ያፈናቅላል፡፡
- የቀበሌ ቤት ከግለሰብ የተከራዩ ግለሰቦች ቤቱን ‹‹መውረስ›› ይችላሉ፡፡
ዋዜማ ራዲዮ-ከ42 ዓመታት በፊት ትርፍ የከተማ ቤትና ቦታን በተመለከተ የወጣው አዋጅ ቁጥር 47/67ን ተከትሎ ከግለሰቦች የተወረሱ በርካታ ቤቶችን በተመለከተ የኢህአዴግ መንግሥት ግልጽ የሆነ መተዳደሪያ ሳያቀርብ ላለፉት 26 ዓመታት አሳድሮታል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር የተላከ መመሪያ በአወዛጋቢ አንቀጾች የተሞላ በመሆኑ የአስሩን ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር ባለሞያዎች ጭምር እያነጋገረ ነው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተፈርሞ የወጣው ይህ አዲሱ መመሪያ የቀበሌ ቤትን በውክልና የማደስ፣ የማውረስ፣ ለደባል ነዋሪ ከፊል የነዋሪነት መብትን የማጎናጸፍ፣ የምትክ ባለቤቶችን መብት የማረጋገጥ አንቀጾችን በተሻለ ግልጽነት ያቀፈ ሲሆን ለዓመታት ባልተፈቱ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ግን አወዛጋቢ አንቀጾችን ይዟል፡፡
በተለይም የቀበሌ ንግድ ቤትን ሸንሽነው የሚያከራዩ ዜጎች መብታቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው በመስጠታቸው የተከራይ ተከራዮች ንግድ ቤቶቹን ‹‹የመውረስ›› እድል እንዳላቸው የሚጠቁም አንቀጽን መያዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ይህም የሆነው የተከራይ ተከራዮች የቀበሌ ንግድ ቤት ቀዳሚ ተከራይን አልፈው ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር ውል ማሰር እንደሚችሉ የሚያመላክት አንቀጽን በውስጡ ይዟል፡፡
በ1988 በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የንግድ ቤት ከቀበሌ ተከራይ የተከራዩ ግለሰቦች በቀጥታ ቤቱን ከመንግሥት እንዲከራዩ የሚያደርግ መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ በተለይም ንግድ ሱቆች አካባቢ በአከራይ ተከራይ መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህን መመሪያ ተከትሎም ቤቴን መልስ አልመልስም በሚል በአከራይና ተከራዮች መካከል ሕይወት እስከመጠፋፋት የደረሱበት አጋጣሚም ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በቀበሌ ቤት ውስጥ ተጠግተው ባገኙት ክፍት ቦታ ላይ በራሳቸው ወጪ ቤት ገንብተው ለዘመናት ሲኖሩ የነበሩ ዜጎች ‹‹ሕገ ወጦች በመሆናቸው እንዳይስተናገዱ›› ሲል ይኸው መመሪያው ያዛል፡፡ በመልሶ ማልማት ጊዜም ቢሆን ሲፈርሱ ምንም ዓይነት ምትክ ቦታን እንዳያገኙ ያስጠነቅቃል፡፡ ይህ አንቀጽ ባለፉት 40 ዓመታት በቀበሌ ቤት ግቢ ውስጥ በደባልነትም ሆነ በግል ወጪ ከቀበሌ ቤት በመጠጋት ባገኙት ክፍት ቦታ ደሳሳ ጎጆዎችን ቀልሰው የሚኖሩ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ እንደሆነ የከተማ መሬት ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ሥርዓት በጦርነትም ሆነ በተለያየ መንገድ ከአገሪቱ የለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ባዶ ቦታ በመንግሥት እየተመሩ ጊዝያዊ ጎጆ ቀልሰው እንዲኖሩ ተደርገው በዚያው የተዘነጉና ለአስተዳደር እንዲመች በሚል ብቻ በቀበሌ ቤትነት ተቆጥረው ለረዥም ዘመን የኖሩ ዜጎች ‹‹የግል ይዞታ›› ተደርገው እንዳይቆጠሩ ይኸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መመሪያ ያዛል፡፡ መመሪያው እንደሚያስገነዝበው ከሆነ ባለፉት 42 ዓመታት አንድ ቦታ በማንኛውም ምክንያትና ሁኔታ ለአንድም ቀን ቢሆን በቀበሌ ቤትነት ከተዳደረ ይዞታው የቀበሌ ቤት ሆኖ ይታሰባል ይላል፡፡
ለዋዜማ በስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የመሬት ባለሞያ ይህ አንቀጽ ‹‹ዜጎችን በእኩል ዓይን ያልተመለከተ ነው፣ ነባራዊ ሁኔታዎችንም አላስተዋለም›› ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ‹‹ባለፉት 42 ዓመታት ከ10ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በሰፋፊ የቀበሌ ቤቶች በደባልነት ሲኖሩ ባገኙት ክፍት ቦታ ላይ ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ቤት ቀልሰው ኖረዋል፡፡ ወልደው ከብረዋል፣ ግብር ከፍለዋል፡፡ በምርጫ 97 ዋዜማ መሬትን በጠራራ ፀሐይ ወረው የያዙ ዜጎች ‹‹ሬጉላራይዝ›› እየተደረጉ ሕጋዊ ካርታ እየተሰጣቸው ለ40 ዓመት የኖረን ዜጋ በአንድ መመሪያ ከቤት ንብረቱ ማፈናቀል አግባብ አይመስለኝም‹‹ ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በግለሰብ ቤቶች ግቢ ውስጥ የግል መኖርያ ቤቶች ሲገኙ የይዞታ ጥያቄዎቻቸው በተነጻጻሪ ካርታ ሲስተናገዱ የቆየ ሲሆን በዚህም የተነሳ ባለሐብቶች ቦታዎቹን በተናጥል ለማልማትም ሆነ ከቀበሌ ቤት ጋር የሚጎራበቱ ይዞታዎችን አስፍቶ ለማልማት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ኾኖም ይህ ችግር በሚቀጥለው ወር በሚጸድቀው አዲሱ የሊዝ አዋጅ መልስ እንደሚያገኝ ተመላክቷል፡፡
“የተነፃፃሪ የመሬት ድርሻ ይዞታ ካርታ” ማለት በአንድ ግቢ ውስጥ የሚገኙ የመሬት ባለይዞታዎች የግል የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሲጠይቁ ይዞታቸውን ከፍሎ ካርታ ለመስጠት የማይቻል ሲሆን ይዞታው ሳይከፋፈል ባለበት ሁኔታ የድርሻቸውን መጠን በመጥቀስ የመሬት ይዞታ ካርታ መስጠት ግዴታ ሲሆን ነው፡፡
በአንጻሩ በቀድሞው ጊዜ በሥራ ዝውውር ምክንያት የግል የዞታቸውን ለመንግሥት በማስረከብ ለሥራ በሚዘዋወሩበት ክልል በምትኩ የቀበሌ ቤት ያገኙ የነበሩ ግለሰቦች ይዞታቸውን በተመለከተ ካርታ እንዲያገኙ አዲሱ ውሳኔ ይደነግጋል፡፡ ይህም በተለምዶ ‹‹ማካካሻ ቤት›› ተብሎ የሚጠራው ነው፡፡
የቀበሌ ቤቶች በደብተር ካርታ ሲስተናገዱ የቆዩ ሲሆን መንግሥት ባለፉት 26 ዓመታት ምን ያህል የቀበሌ ይዞታዎች እንዳሉ መረጃ ለማጠናቀር ሞክሮ እምብዛምም አልተሳካለትም፡፡ ለ30ሺህ የቀበሌ ቤቶች ሕጋዊ ካርታ ለማዘጋጀት ከሁለት ዓመት በፊት እንቅስቃሴ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል፡፡ ኾኖም በአዲስ አበባ ብቻ ከ170ሺ የማያንሱ የቀበሌ ቤቶች እንዳሉ ይገመታል፡፡ የቀበሌ ቤቶችን በሕጋዊ ካርታ መለየት አለመቻሉ በአንዳንድ የመንግሥት ሹመኞች በማዕከላዊ ከተማ ውስጥ የሚገኙ በጥሩ ይዞታ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ እድሉን ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የቀበሌ ቤቶች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየተመናመነ እንደሚገኝ የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡
መንግሥት የቀበሌ ቤቶችን ባለቤትነትን በጽኑ የሚያጤነው በመልሶ ማልማት ወቅት ምትክ የቀበሌ ቤት ለማፈላለግ ሲገደድ ብቻ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ የቀበሌ ቤቶች በመልሶ ማልማት ሲፈርሱ ነዋሪዎቹ ባለ አንድ ወይም ባለ ሁለት መኝታ ቤት እንዲገዙ አልያም ወደ ሌላ የቀበሌ ቤት እንዲዛወሩ እድሉ ይመቻችላቸዋል፡፡ ኮንዶሚንየም የመግዛት አቅም ከሌላቸው ደግሞ አዲስ የቀበሌ ቤት ተፈልጎ እስኪገኝ ለሁለት ዓመት የሚሆን መጠነኛ የቤት ኪራይ አበል ይሰጣቸዋል፡፡ በአዲስ አበባ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ዜጎች ኮንዶሚንየም ለመግዛት አቅም ስለሚያንሳቸው በመልሶ ማልማት ጊዜ ለከፍተኛ እንግልት ይጋለጣሉ፡፡
የቀበሌ ቤቶች የሚኖሩ ዜጎች አዲስ ቤት ቢኖራቸውም እንኳ ለመልቀቅ ፍቃደኞች አይሆኑም፡፡ በርካታ የቀበሌ ቤቶች በመንግሥት ትንንሽ ሹመኞች መያዛቸው ደግሞ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ለዓመታት የቀበሌ ቤት በመጠባበቅ ላይ ያሉ ዜጎች ቢኖሩም የመንግሥት ሹመኞች በግል ያስገነቧቸው ቤቶችን እያከራዩ በቀበሌ ቤቶች መኖርን ስለሚመርጡ ድሀ ዜጎች ተራ የማግኘት እድላቸው የጠበበ ነው፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቀበሌ ቤቶች ተለቀው የነበረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ዋዜማ ኤርትራዊያን ከአገር እንዲለቁ በተገደዱበት ወቅት መሆኑ ይታወሳል፡፡
የቀበሌ ቤት ኖሯቸው አጎራባች የቀበሌ ቤቶችን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስፋፍተው የያዙ፣ ወደራሳቸው የቀበሌ ቤት ያካተቱ፣ ከቀበሌ ቤት የሚጎራበት የግል ቤት ኖሯቸው በጊዜ ሂደት የቀበሌ ቤቱን ግንብ አፍርሰው ወደራሳቸው ቤት አጠቃለው የያዙ፣ ይዞታን በሕገወጥ መንገድ ካስፋፉ በኋላም ለሦስተኛ ወገን የሸጡና በዚህም አላግባብ ጥቅም ለማግኘት የሞከሩ ዜጎች ቦታውን እንዲነጠቁ እንደሚደረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መመሪያ ያዛል፡፡ ኾኖም በክፍለ ከተማ የሚገኙ የመሬት ባለሞያዎች የዚህን አንቀጽ ተፈጻሚነት በጥርጣሬ ይመለከቱታል፡፡
‹‹የቀበሌ ቤቶችን ይዞታ ከራሳቸው ጋር አዳብለውና አስፋፍተው የያዙ ግለሰቦች ካርታ ተሠርቶላቸው ለሦስተኛ ወገን አስተላልፈዋል፤ ብዙዎቹ በዚህ ድርጊት ውስጥ የተዘፈቁት መካከለኛ የመንግሥት ሹመኞች እንደሆኑ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ እነዚህን ዛሬ ተነስቶ ተጠያቂ ማድረግ የማይመስል ነገር ነው›› ይላሉ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የኮልፌ ቀራንዮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ባለሞያ፡፡
በአቶ ደበበ አበራ በሚኒስትር ማዕረግ የካቢኔና ማኅበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ ፊርማ የወጣው ይህ መመሪያ ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ግንዛቤ ውስጥ ያላካተተ ከመሆኑም በተጨማሪ ለዘመናት በቀበሌ ቤቶች እየኖሩ ቤተሰብ ያፈሩ ዜጎችን ያለ ምንም ርህራሄና አማራጭ የሚያፈናቅል በመሆኑ ተግባራዊ የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
‹‹እኔ የሚገባኝ ወደተግባር ከመኬዱ በፊት መመሪያው ሊቀለበስ እንደሚችል ነው፣ ተግባራዊ እናርገው ብንልም የሚቻል አይደለም፣ አማራጮች መቀመጥ አለባቸው›› ይላል ቀድሞ በከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስትር ውስጥ የሚሰራና አሁን በአዲስ አበባ መስተዳደር የከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ባልደረባ፡፡