EU flagየአውሮፓ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ክንፍ የሆነው የአውሮፓ ኮሚሽን አራት ኮሚሽነሮች በድርቅ የተጎዱ ቦታዎቸን በመጪው ሳምንት ሊጎበኙ ነው። ኮሚሽነሮቹ ቦታዎቹን የሚጎበኙት በአፍሪካ ህብረት እና በአውሮፓ ኮሚሽን መካከል በሚደረግ የጋራ ስብሰባ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ይሆናል።  በዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁት አራቱ ኮሚሽነሮች መጋቢት 30 በሶማሌ ክልል የሚገኘውን ሲቲ ዞን ለመመልከት ቀጠሮ ይዘዋል።

ሲቲ ዞን ድርቅ ክፉኛ አጥቅቷቸዋል ከሚባሉ አካባቢዎች በመጀመሪያ ረድፍ የሚቀመጥ ነው። ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የደረሰውን ድርቅ አሳሳቢነት ለማሳየት ከሚመርጧቸው ቦታዎች ሲቲ ዋነኛው ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለስራ ጉዳይ በአካባቢው የነበረ የዋዜማ ምንጭ እንደሚናገረው ከሆነ ከዓመት በላይ ዝናብ በጠፋበት በዚያ ቦታ አሁንም የዝናብ ምልክት አይታይም።

“ችግሩ ብሷል። ህዝቡ በጣም ተቸግሯል። እርዳታ ግን እየተከፋፈለ ነው” ይላል በሲቲ ዞን ስላየው ሲናገር።
“አካባቢውን በጨለማ እንዲዋጥ የሚያደርግ አቧራም ነበር።”

በዚህ አካባቢ በአካል ተገኝተው የችግሩን መጠን ይገመግማሉ ተብለው ከሚጠበቁት ኮሚሽነሮች አንደኛው በምክትል ፕሬዝዳንትነት ደረጃ ያሉ ናቸው። ቫልዴስ ዶምብሮቭስኪ የሚሰኙት እኚህ ኮሚሽነር የማህበራዊ ውይይት ክፍልን የሚመሩ ናቸው። አብረዋቸው የሰብዓዊ እርዳታና የአደጋ አስተዳደር፣ የዓለም አቀፍ ትብብር እና ልማት እንደዚሁም የማህበራዊ ጉዳዩች ኮሚሽነሮች ወደ ቦታው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።