በጅቡቲ የሃያላን ሀገራት ጂኦፕለቲካዊ ፍላጎት እየጨመረ መሄድ ኢትዮዽያን ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዋጋ እያስከፈላት ነው። የኢትዮዽያ የባህር በር አልባ መሆን ለገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ሳይቀር ትልቅ የራስ ምታት መሆኑ የጓዳ ምስጢር ከሆነ ሰነባበተ። የቻላቸው ታደስ ዘገባን አድምጡት
ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ወደብ ከገበያ የሚገዛ ሸቀጥ ነው ሲል በኤርትራ መገንጠል ኢትዮዽያ ያጣችውን የአሰብ ወደብ የባለቤትነት መብት ዝቅ ለማድረግ ይሞክራል። የቀድሞ መሪ መለስ ዜናዊ በጉዳዮ ላይ ስድብ ቀረሽ ማስተባባያ ከመስጠት አላመነቱም። ይህ የፓርቲው አቋም አርቆ አሳቢነት የጎደለው ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው። ለዚህም ይመስላል ኢትዮዽያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ያላት ጥገኝነት ወደብ ከገበያ የሚገዛ ሸቀጥ ሳይሆን የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ሆኖ ብቅ ያለው።
ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ ኣምስት ዓመታት በዋና ወደብንት የምትጠቀምባት ጅቡቲ የሃያላን ሀገሮችን ትኩረት ከሳብች ሰነባበተች። የዓለማችን ግዙፍ ባህር ንግድ መተላለፊያ በሆነው ባብ ዔል መንደብ ጎን የምትገኘው ጅቡቲ ከሩሲያ በስተቀር ሁሉም ሃያላን ሀገሮች ጦር ሰፈራቸውን አቋቁመውባታል። ፱፻ ሺህ ህዝብ ብቻ ያላት ጅቡቲ የጦር ሰፈር ኪራይና የወደብ አገልግሎት ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች።
ከነፃነቷ ጀምሮ በፈረንሳይ ዳጎስ ያለ የኢኮኖሚ እርዳታና ወታደራዊ ከለላ የሚደረግላት ጅቡቲ ከሃያላን ሀገሮች ጦር ሰፈር ኪራይ፣ ከወደብ አግልግሎት ፣ ከውጭ ርዳታና ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በርክታ ገቢ ታግኛልች። ዓመታዊ ጠቅላላ ምርቷም ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ። ያም ሆኖ በብልሹ አሰራርና በሃብት ክፍፍል እጦት ሳቢያ አብዛኛው ህዝቧ ዛሬም ከበረከቱ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።
በጠቅላላው ሲታይ ጅቡቲን በዓለም መድረክ ተፈላጊ ካድርጓት ነገሮች መካከል የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድግት፣ በህንድ ውቂያኖስ ላይ የተስፋፋው የባህር ላይ ዘረፋ፣ የአልቃይዳና አልሸባብ መስፋፋትና በቅርቡም በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላችው የየመን ሁቱ ጎሳ አማፂያን ተጥቃሽ ናቸው ።
ጅቡቲ ባሁኑ ስዓት የአሜሪካን፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይና አውሮፓ ህብረት ጦር ሰፈሮችን እያስተናገድች ትገኛለች። በቅርቡም ቻይና በታሪኳ በውጭ ሀገር የመጀመሪያዋ የሆነውን ጦር ሰፈር ጅቡቲ ላይ ለመክፈት ስምምንት ላይ ደርሳለች።
ሊሞኔር ካምፕ የተባለው የአሜሪካው ጦር ሰፈር ከተቋቋመ አስር ዓመት ያሳቆጠር ሲሆን አሜሪካ ውሏን በያዝነው ዓመት ለተጨማሪ አስር ዓመት ኣድሳልች። አራት ሺህ ያህል ወታደሮችን የያዘው ጦር ስፈር ለአሜሪካ በአፍሪካ ያላት ቁልፍ ቋሚ ጦር ሰፈር ነው። ጦር ሰፍሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የያዝ ሲሆን እነዚህ አዎሮፕላኖችም በየመንና ሱማሊያ የሚገኙ በርካታ የኣልቃይዳና ኣልሸባብ ሽብርተኛ ተጠርጣሪዎችን እያደነ የሚግድለው ከዚሁ ጣቢያ በመነሳት ነው። በነገራችን ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ይህ ጦር ሰፈር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሆን ጎትጉተው ሳይሳካላቸው እንደቀረ ታማኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
ጅቡቲ ከቻይናም ጋር ያላት ትብብር ጠንካራ መሆኑ የሚያሳየው ባለፈው ዓመት ወደቡን የማስተዳደር ሃላፊነቱን ከዱባዩ ዓላማቀፍ ወደቦች ድርጅት ነጥቃ ለቻይና መስጠቷ ነው። በሌላ በኩልም ቻይና በአፍሪካ ካፈሰሰችው ሁለት መቶ ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ዘጠኝ ቢሊዮኑን የጅቡቲን ወደብ ለማስፋፋት፣ ሲቪል አውሮፕላን ማረፊያዎችን ለመገንባትና ከኢትዮጵያ ጋር የሚገናኘውን ባቡር መስመር ለመዘርጋት እያዋልችው ትገኛለች። ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ታጁራ ወደብም የምትገነባው ቻይና ነች።
ሆኖም የሃያላን ሀገሮች ጅቡቲ ላይ ያሳዩት ወታደራዊ ፍላጎት በኢትዮጵያና በራሷ ጅቡቲ ላይ ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል። በጅቡቲ በኩል የሃያላን ሀገሮችን ከለላ ማግኝቷ ለሙስና፣ ለሰብዓዊ መብት ረገጣና ቤተሰባዊ መልክ ያለው ፖለቲካ ስርዓት እንዲሰፍን እንዳደረገ ተንታኞች ይናገራሉ። ይህም ወደፊት አለመረጋጋት እንዲሰፍን ምክንያት እንዳይሆን ስጋት ፈጥሯል። ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ደግሞ በጅቡቲ ላይ ያላት ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ወደፊት እየተመናመነ ሊሄድ እንደሚችል ጠቋሚ ነው።
ባለፈው ዓመት በነፃ ለሰላሳ ዓመት እንድትጠቀምብት የተፈቀደላት ግዙፍ የንፁህ መጠጥ ውሃም ይህንኑ የሃይል ሚዛን ለመጥበቅና ጅቡቲም የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በሚጎዳ ነገር እንዳትተባብር ለማባበል ታስቦ ሊሆን እንደሚችል ይታምናል። በሌላ መልኩ ሲታይ ግን ቻይና ጅቡቲ ውስጥ እጇን በሰፊው ማስገባቷ ምናልባት ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል የሚናገሩ አስተያየት ስጭዎች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያ ይህንን ታሳቢ በማድርግም እኤአ በ፪፻፰ ኤርትራ የጅቡቲን ድንበር ጥሳ በገባች ጊዜ መንግስት ሃያ አምስት ሺህ ያህል ወታደሮቹን ወደ ድንበር በማስጠጋት ለጅቡቲ ሉዓላዊንትና ለወደቡም ደህንነት የሚሰጠውን ትኩረት አሳይቷል።
ጅቡቲ ባሁኑ ጊዜ ከኣሜሪካ ጦር ሰፈር ኪራይ በዓመት ሰባ ሚሊዮን ዶላር ስታግኝ ከፈረንሳይና ጃፓን ደግሞ በድምሩ ስድሳ ሚሊዮን ዶላር ታግኛለች። በጠቅላላው በዓመት ከአንድ መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ዶላር በላይ በኪራይ መልክ እንደምታስገባ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ የሚያሳየው ከኢትዮጵያ የሚገኘው የወደብ አግልግሎት ክፍያ ብቸኛ የገቢ ምንጯ መሆኑ እንዳከተመ ነው። ተወደደም ተጠላም ይህ በኢትዮዽያ የመደራደር አቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖርዋል።
ጅቡቲ የሃያላን ሀገሮችን ትኩርት መሳቧ ወደቦቿን እንድታስፋፋም ረድቷታል። ባሁኑ ጊዜም በዘጠኝ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ወደቦቿን እያስፋፋች ትገኛለች። ሁሉም ማስፋፊያዎቿ እኤአ በሁለት ሺህ አስራ ሰባት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠብቃል። ያን ጊዜ የጅቡቲ ባለስልጣናት የወደቡ አጠቃላይ አቅም በአስራ አምስት በመቶ ያድግልናል ብለው ተስፋ ጥለዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የወደብ ዋጋ መናርና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን እንዲሁም ሀገሪቱ ባንድ ወደብ ላይ ያላትን ጥግኝነት ይቀርፉልናል ተብልው የሚጠበቁት የባቡር መስመር ግንባታው፣ደረቅ ወደቦች ግንባታና አማራጭ የጎረቤት ሀገር ወደቦች ናቸው። የአዲስ አበባ ባለስልጣናት በተለይ አማራጭ ወደቦችን ሲያስሱ መኖራቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው። በቅርቡም የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኣቶ ወርቅነህ ገበየሁ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት በሱማሌላንዷ በርበራ ወደብ በኩል ከአምስት እስከ አስር በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ገቢ እቃዎች ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። ባለፈው ግንቦት ወርም መንግስት በሱዳን ወደብ በኩል ነዳጅ ለማስገባት አዲስ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቆ ነበር። በእርግጥ እስካሁንም ለሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚሰራጨው ማዳበሪያ የሚገባው በሱዳን ወደብ በኩል ነው።
በጠቅላላው ግን የወደቦቹ አቅም ውስንነትና ርቀት ከባዱ ማነቆ ሆኖ ይቀጥላል። ሀገራችን ከጅቡቲ ጋር ከመሰረተችው ጥብቅ የመሰረተ ልማት ቁርኝትና ከወደቡም ዘመናዊነትና ቅርበት ኣንፃር የጎረቤት ሀገር አማራጭ ወደቦች ሊተኩት እንደማይችሉ ባለሙያዎች ያሳረዳሉ። ይህም ጅቡቲ ከሃያላን ሀገሮች የምታግኘው ድጋፍ ሲታከልበት ሀገራችን በወደቡ ላይ የሚኖራት ጥገኝነትና የሚጠይቃትም ከፍተኛ ወጭ ወደፊትም እንደሚቀጥል ያመላክታል።