Tana Beles Sugar Factory

ዋዜማ- ወደ ምርት ስራ ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ ከ6 መቶ በላይ የሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞቹን ወደ ሌሎች አምስት ስኳር ፋብሪካዎች መበተኑንና ከሠራተኞቹ ጋር የገባውን ውል ማፍረሱን ዋዜማ ሰምታለች።

ፋብሪካው፣ በቅርቡ ወደ ምርት ሂደት ይመለሳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ የሚጎድሉት በርካታ ነገሮች ባለመሟላታቸው ምክንያት ሠራተኞቹን ለመበተን ሲገደድ፤ በዚህ ዓመት ጭምር ምርት እንደማይጀምር እንደተነገራቸው ሠራተኞቹ ለዋዜማ ነግረዋታል።

ሠራተኞቹ የተበተኑት፣ በዚህ ወቅት ወደ ስኳር ማምረት ለመግባት በሂደት ላይ ወዳሉትና በምርት ላይ ባሉት ወንጂ ሸዋ፣ መተሐራ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለትና ቁጥር ሦስት እንዲሁም ወደ ፊንጫ ፋብሪካዎች መሆኑን ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል።

በ’ያንዳንዳቸው ፋብሪካዎች 120 ሠራተኞች መመደባቸውን የገለጹት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች፣ ከነዚህ ውስጥ ባለመስማማት ወደተመደቡበት ፋብሪካ ያልሄዱ መኖራቸውን ሰምተናል።

ወደ ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የተመደቡ ሁሉም ሠራተኞች ደግሞ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይሄዱ መቅረታቸውን ገልጸዋል። የተበተኑት ሠራተኞች በፋብሪካው ደረጃ አሰጣጥ መሰረት፣ ከደረጃ ስምንት እስከ ደረጃ ሃያ ሁለት ያሉት መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ እነዚህም የማሽን ኦፕሬተር፣ ሱፐርቫይዘር፣ ቡድን መሪና ሌሎቹ አብዛኞቹ ደግሞ ሞያዊ ሥራዎችን የሚሰሩ ናቸው ተብሏል።

ከደረጃ ሰባት በታች ያሉትን ቋሚ የፋብሪካው ሠራተኞች ደግሞ ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ያልከፈላቸውን ውዝፍ የአራት ወራት ደምወዝ፣ የሥራ ማፈላለጊያና ጥቅማጥቅም ሰጥቶ ማሰናበቱን ሰምተናል።

እነዚህ ሠራተኞች ከተስማሙ በፋብሪካው ውስጥ እንደ ቀን ሰራተኛ በቀን 150 ብር እየተከፈላቸው አሊያም ውላቸውን ሳያቋርጡ ፋብሪካው ምናልባት ወደ ሥራ የሚመለስ ከሆነ መመለስ የሚችሉበት ሌላ አማራጭ ቀርቦላቸዋል ።

እነዚህ ከደረጃ ሰባት በታች ካሉት ተሰናባች ሠራተኞች አብዛኞቹ፣ ዋናውን ቴክኒሻን ወይም ማሽን ኦፕሬተር የሚያግዙ ረዳቶች  መሆናቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

ፋብሪካው ሠራተኞቹን ሲያሰናብትና በአራቱም ስኳር ፋብሪካዎች እንዲበተኑ ሲያደርግ፣ ለእያንዳንዳቸው 6 ሺ ብር በብድር መልክ ክፍያ መፈጸሙን፣ ገንዘቡም በተመደቡበት ፋብሪካ ሥራ ሲጀምሩ ከወር ደምወዛቸው ላይ ተቆራጭ የሚደረግ መሆኑ ተጠቁሟል።

ሠራተኞቹ አዲስ ወደ ተመደቡበት ፋብሪካ ሲያቀኑ፣ እንደ አዲስ ውል የሚፈጽሙ መሆኑ እንደተነገራቸው የገለጹ ሲሆን፣ ደምወዙም ቀድሞ ከሚሰሩበት ፋብሪካ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ለዋዜማ ነግረዋታል። ለአብነትም፣ ዋዜማ ያነጋገረችው በጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በረዳት ሱፐርቫይዘርነት ሲሰራ የነበረ አንድ ባለሙያ የተጣራ ወርኃዊ ደምወዙ 17 ሺ ብር እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ አሁን በተመደበበት ፋብሪካ ግን 12 ሺ ብር የተጣራ ክፍያ እንደሚከፈለው በውሉ ላይ መስፈሩን አስረድቷል።

ስኳር ፋብሪካዎቹ ለቋሚ ሠራተኞቻቸው ከምግብ በስተቀር መኖሪያ ቤትን ጨምሮ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን እንዲያሟሉላቸው መመሪያ ቢኖርም፣ ሠራተኞቹ አሁን ወደ ተመደቡባቸው ፋብሪካዎች ሲያቀኑ፣ ጊዜያዊ ማረፊያ እንኳን እንዳልተሰጣቸው ለዋዜማ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት አምስትና ከዚያ በላይ በመሆን ቤት ለመከራየት መገደዳቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ እሱንም ከፋብሪካው ረጅም ርቀት በመጓዝ ካልሆነ በቀር የሚከራይ ቤት እንደማይገኝ አብራርተዋል።

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ካለው 1350 አካባቢ ቋሚ ሠራተኞች ውስጥ፣ አሁን ላይ የቀሩት 421 ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውን ያስረዱት የዋዜማ ምንጮች፣ እነሱም ከደረጃ ሃያ ሁለት በላይ ያሉ የአሥተዳደር፣ የመሬት ዝግጅትና የሸንኮራ አገዳ ልማት ሠራተኞች መሆናቸውን ነግረውናል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ኤሌክትሪሺያኖችና የፋብሪካው የጥበቃ ሠራተኞች በተመሳሳይ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ከተወሰነላቸው ሠራተኞች መካከል መሆናቸውንም ሰምተናል።

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ እስከ አሁን ድረስ የ2017 ዓ.ም በጀት ከመንግሥት እንዳልተለቀቀለት የተገለጸ ሲሆን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ጣቢያው ላይ በተደጋጋሚ የሚደርስ ዝርፊያ፣ የመለዋወጫ ዕቃ አለመኖርና ተያያዝ ችግሮች ለፋብሪካው ሥራ ማቆምና ሠራተኞቹን እስከ መበተን ለመድረሱ ዋና ምክንያት መሆናቸውንም ተረድተናል።

ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ፣ የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፤ የግንባታ ሥራው ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተጠናቆ የሙከራ ምርት መጀመሩ ይታወሳል። ሆኖም ከተመረቀ በኋላ እስከ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ብቻ ለሁለት ዓመታት በሥራ ላይ እንደነበር የነገሩን ምንጮች፣ በዚያ ወቅትም በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ እንደነበር ዋዜማ ተረድታለች።

ከሳምንታት በፊት እንደ አገር ካሉ ስምንት ፋብሪካዎች መካከል በሥራ ላይ ያለው አንድ ስኳር ፋብሪካ ብቻ መሆኑን ዋዜማ ዘግባ እንደነበር ይታወሳል። የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በበኩሉ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ለዕቃ መለዋወጫ ግዢ የሚውል 27 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድቦ፣ ከዚህ ውስጥ እስካሁን 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ የመለዋወጫ ግዢ መከናወኑን መግለጹ ይታወሳል። በዚህም ምርት አቁመው የነበሩ ስድስት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ መደበኛ ሥራቸው መመለሳቸውን፣ ይኸው የፌደራል መንግሥቱ ተቋም ተናግሯል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ጋር በገባው ስምምነት መሰረት፣ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል የማዛወሩ ሂደት በቀጣዩ ታኅሳስ ወር 2018 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ፣ መንግሥት እና ይኸው አበዳሪ ተቋም የገቡበት አንድ የስምምነት ሰነድ ላይ መጠቀሱ ይታወሳል። [ዋዜማ]