ዋዜማ- የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታ 97 ሚሊየን ኩንታል ይገመታል። ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ እናመርተዋለን ተብሎ የሚጠበቀው የስንዴ ምርት 117 ሚሊየን ኩንታል ነበር። ዋዜማ በዚህ ዓመት በየመንፈቁ ባደረገችው ዳሰሳ ግን አሁንም ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ወደ ሀገር እየገባ ወደ ገበያም እየቀረበ ነው። ይባስ ብሎም አርሶ አደሮች ከውጪ ከሚገባው ስንዴ ጋር በገበያ ተወዳዳሪ መሆን አቅቷቸው ችግር ውስጥ እንደሆኑ ነግረውናል። መንግስት ይህን ተቃርኖ እንዴት ይሆን የሚያስታርቀው? ብለን የመንግስትን ምላሽ ጠይቀናል።
ከሳምንታት በፊት በሁለት መርከቦች የተጫነ ስንዴ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል። ይህን ስንዴ ወደመሀል ሀገር በማጓጓዝ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችም እረፍት አልነበራቸውም፣ ከወትሮው እጥፍ ተሽከርካሪዎች ለዚሁ ስራ ተሰማርተው ነበር። የትራንስፖርት ድርጅቶቹ ይህን ስንዴ ከወደብ አንስቶ መጋዘን ከማድረሰ የዘለለ ስንዴውን ማን እንዳስመጣው ምንም መረጃ የላቸውም።
ዋዜማ እንደተገነዘበችው ምርቱ በአብላጫው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላሉ ዱቄት እና ምግብ አቀነባባሪ ፋብሪካዎች እየተከፋፈለ ነው።
ከውጭ የሚገባው ስንዴ ለሀገር ውስጥ ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች የዋጋ ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ፈተና ይዞ እንደመጣ ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮቿ ተረድታለች። ይህም ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች ላይ “ምርቱን ለማቆም የመገደድ ያክል” ጫና እየፈጠረባቸው እንደሆነም ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ ፤ ስንዴ በስፋት የሚመረትባቸው የኦሮምያ ክልል አርሲ ዞን አርሶ አደሮች ገልጸዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ባደረግነው ቅኝት ከውጭ የሚመጣው ስንዴ የትራንስፖርቱን ጨምሮ ለፋብሪካዎች በኩንታል በ5,400 ብር ገደማ እየተሸጠ ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የስንዴ አርሶ አደር ፤ እሳቸው እና መሰሎቻቸው ስንዴን ለማምመረት ከሚያወጡት ወጭ አንጻር አንድ ኩንታል ስንዴን ለፋብሪካ 5,400 ብር ማስረከብ እንደማያዋጣቸው ለዋዜማ ይናገራሉ። ይህም ሳያንስ ከውጭ ስንዴ አምጥተው ለፋብሪካዎች እንደሚያከፋፍሉ ነጋዴዎች ለኩንታል ስንዴ 5,400 ብርም እንደማያገኙ ነው የነገሩን። ይህንን ሲያስረዱም “እኛ ከገጠር አካባቢዎች አጓጉዘን ስንዴን ለፋብሪካ የማከፋፈል አቅም ስለሌለን ፤ እንዲሁም አብዛኛው አርሶ አደር ትንሽ ትንሽ ምርት ስለሚያመርት የምናመርተውን ስንዴ ለፋብሪካዎች እና ሌሎች ገበያዎች ለሚያቀርቡ ነጋዴዎች ነው የምንሸጠው”
“ከእኛ የሚገዙት ነጋዴዎች ከውጭ ስንዴን አምጥተው ከሚያከፋፍሉ ነጋዴዎች ጋር ተወዳድረው ስለሆነ የሚያከፋፍሉት ከኛ ገበሬዎች ላይ ስንዴውን ግፋ ቢል በኩንታል 4,500 ብር (በኪሎ 45 ብር) አካባቢ ገዝተው ነው ለፋብሪካዎች የሚሸጡት ” ብለውናል። “አብዛኛው አርሶ አደር ደግሞ ሌሎች ወጪዎች ስላሉበት ምርቱን የግድ ይሸጣል” ሲሉ ገልጸውልናል።
ሌላ አስተያየታቸውን ለዋዜማ የሰጡ የዚሁ የአርሲ ዞን ሎዴ ሄጦሳ ወረዳ ስንዴ አምራች አርሶ አደር “አሁን ላይ ስንዴን ለማምረት አርሶ አደሩ እያወጣ ካለው ወጭ አንጻር አንድ ኩንታል ስንዴን በ4,500 ብር መሸጥ በፍጹም አዋጭ አይደለም ” ይላሉ።
ለዚህ ማስረጃ ሲያቀርቡም ” ለምሳሌ እኔ ስንዴን ለማምረት መንግስት በ3,500 ብር አቅርቤያለሁ የሚለውን ማዳበሪያ በተገቢው መንገድ ማግኘት ስላልቻልኩ በጥቁር ገበያ ኩንታሉን ማዳበሪያ በ6,500 ብር ነው እየገዛሁ ስንዴ ያመረትኩት ፤ በዚያ ላይ ተደራራቢ ግብርን ጨምሮ በርካታ ወጪዎች አሉብኝ ፤ በተለይ እንደኔ መሬት ተከራይቶ ለሚያርስ አርሶ አደር የአሁኑ ገበያ አያዋጣም ፤ ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በቀጣይ ወቅት ስንዴን አላመርትም “ብለውናል።
እኚሁ አርሶ አደር ሲያስረዱ”አንድ ገበሬ ስንዴን ሲያመርት በትንሹ ለአንድ ኪሎ ከ50 ብር በላይ ያወጣል ፤ ስለዚህ አንድ ኪሎ ስንዴን አሁን ባለው ገበያ ከ6000 ብር ጀምሮ ካልሸጠ አያዋጣም”
በከተማ አቅራቢያ ባሉ ገበያዎች አንዱ ኪሎ ስንዴ እስከ 65 ብር ቢሸጥም እነዚህ ገበያዎች ጋር አብዛኛው አርሶ አደር መድረስ ስለማይችል በርካሽ ዋጋ ለነጋዴ ማስረከብ ቀጥለዋል።
በሀገር ውስጥ ስንዴ አምራች አርሶ አደሮች ላይ ከውጭ የሚገባ ስንዴ ጫና ማሳደር የጀመረው ካለፈው አመት ጀምሮ መሆኑን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ ፤ በተለይ በተለምዶ ሚያዝያ እና ግንቦት ወር ላይ ምርት የማይሰበሰብበት ወቅት በመሆኑ በአንጻሩ ጥሩ የገበያ ዋጋ የሚገኝበት ወቅት ቢሆንም ፤ በጊዜው ከፍተኛ ስንዴ ከውጭ በመግባቱ አንድ ኩንታል ስንዴን አሁን ካለው ዋጋ በታች 4,000 ብር ደረስ ወርደን ስንሸጥ ነበርም ይላሉ። ስለሆነም የሀገር ውስጥ አርሶ አደሮች በምርታማነትም ሆነ በሌሎች መመዘኛዎችም ተወዳዳሪ ባለመሆናቸው መንግስት ሊያስብበት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ አመታት ወዲህ ለስንዴ ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቻለሁ ብሎ ከመኸር ወቅት በተጨማሪ በበጋ ወቅት በሚሊየን የሚቆጠር ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት የስንዴ ምርት እንዲመረት እየተደረገ ነው ማለቱ የሚታወስ ነው። በ2016 አ.ም ከበጋ ስንዴ ልማት እስከ 117 ሚሊየን ኩንታል ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መንግስት ተናግሮ ነበር። የተጠቀሰው ምርት ተመርቶ ከሆነም 97 ሚሊየን ኩንታል ነው ከሚባለው የኢትዮጵያ አመታዊ የስንዴ ፍጆታም በላይ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በ2015 ዓ/ም ኢትዮጵያ ስንዴን ለውጭ ገበያ መላክ መጀመሯ እና በአመት እስከ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያስወጣትን ስንዴ ማስገባት ማቆሟም ተገልጿል።
ስለጉዳዩ ሁለት የመንግስት ባለስልጣናትን ጠይቀናል። ሁለቱም በራሳቸው ምክንያት ስማቸውን መግለፅ አልፈለጉም።
የመጀመሪያው ሚንስትር “እኔ እስከማውቀውና በሪፖርቶችም እንደማየው ኢትዮጵያ ስንዴ አታስገባም። ርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ግን በዓለም አቀፍ ጨረታ ስለምንገዛ ብለው ለርዳታ የሚሰጡትን ስንዴ ከውጭ ያስገባሉ። ከዚህ በፊት ግዣቸው ተፈጽሞ ሳይገቡ የቀሩ ካልሆኑ በቀር የውጭ ግዥ የለም”
ሌላው ከሀገሪቱ የውጪ ንግድ ጋር ቅርበት ያላቸው ሚኒስትር ደግሞ ከውጪ ስንዴ እያስገቡ ያሉት በዱቄትና ምግብ ስራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ናቸው ይላሉ።
“የተቀረው ለጋሾች በርካሽ በጨረታ ገዝተው የሚያስገቡትና ለዕርዳታ የሚውል ስንዴ አለ። ሁሉንም ከሀገር ውስጥ እንዲገዙ በየጊዜው እያግባባን ነው። ምርጫው የነሱ ነው” ባይ ናቸው።
የገበሬዎቹ ስጋት “ነፃ ገበያ የፈጠረው መዋዠቅ” ሊሆን እንደሚችልና ራሱ ገበያው ያስተካክለዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ሚንስትሩ ገልፀዋል። [ዋዜማ]