ዋዜማ- በአማራ ክልል ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለ10 ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ግንቦት 28 ካበቃ በኋላ ለተጨማሪ ወራት ባይራዘመም፣ አዋጁ አስቀድሞ የጣላቸው ክልከላዎች አሁንም ተግባራዊ መደረግ ቀጥለዋል። 

ዋዜማ በክልሉ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ባደረገችው ማጣራት በዚህ ወቅት በከተሞች ለሰዎች እና ለተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የሰዓት እላፊ ገደብ የተቀመጠ ሲሆን፣ በየከተሞች የሚጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ እንደአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ የተለያየ ነው። 

ለአብነትም በጎንደር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ አይችሉም። በከተማዋ ባሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ሊሰሩ ይችላል። ይህ ግን በህግ የሚያስጠይቀ በመሆኑ ክልከላዎችን ተላልፈዋል በሚል ለእስር የተዳረጉ በርካታ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ሰምተናል። 

በደብረማርቆስ ከተማ እንዲሁ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ የሰውም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የተከለከለ ነው። 

በክልሉ መዲና ባህር ዳር በተመሳሳይ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎች ደግሞ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ነው ፈቃድ የተሰጣቸው። 

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት በተመሳሳይ በተያዘው ወር ውስጥ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዳይንቀሳቀሱ ክልከላ ጥሏል። 

በክልሉ ባሉ የወረዳም ሆነ የዞን ከተሞች ከምሽቱ ኹለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ለሰውም ሆነ ለተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ እንደማይቻል ዋዜማ ተገንዝባለች። 

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ ወራት በግልጽ ባይራዘምም፣ አዋጁ በነበረበት ጊዜ የነበሩ ክልከላዎች አሁንም መቀጠላቸውን ይገልጻሉ።

ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ፣ በምሽት መንቀሳቀስ እና መሰል ተግባራት የተከለከሉ ናቸው። 

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላትም ሆኑ የፋኖ ታጣቂዎች እነሱ ከማይፈልጉት ኃይል ጋር ግንኙነት አለው ብለው የጠረጠሩት ማንኛውንም ሰው ላይ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ እስር፣ ድብደባ እና አስገድዶ መሰወር ይፈጽማሉ። 

በዚህ ወቅት በክልሉ የሰዓት እላፊ ገደቡን የሚጥሉትም ሆነ የሚያነሱት ወይም ሰዓቱን የሚያሻሽሉት የአካባቢው የመንግሥት አስተዳደሮች በቦታው ካሉ የፌደራል መንግሥቱ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ነው። 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አንድ የህግ ባለሙያ ለዋዜማ እንደገለጹት፣ የከተማ አስተዳደሮችም ሆኑ የየአካባቢ የመንግሥት መዋቅሮች በኮማንድ ፖስት ብቻ የሚጣሉ ክልከላዎችን መጣል አይችሉም። 

በየከተሞች የሚጣሉ የሰዓት እላፊ ክልከላዎችን ለመጣል የከተማ አስተዳደሮቹ ምንም ዓይነት የህግ ድጋፍ የላቸውም ያሉት ባለሙያው፣ ይህ ዓይነቱ አሰራር የተጀመረው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ነው ብለዋል። 

ወረርሽኝ እና መሰል አደጋዎች ሲጋጥሙ የክልል ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚችል ሲሆን፣ የጸጥታ ችግሮች ሲያጋጥሙ አስቸኳይ ጊዜ የሚያውጀው የፌደራል መንግሥት ብቻ ነው።

አሁን በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታ ሲገልጹም <de’facto state of emergency> የሚባለው የአቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በህግ ሳይታወቅ አስፈጻሚ አካል ብቻ የተቀመጠለት አሰራር እንደሆነ ገልጸዋል። 

ባለሙያው እንደሚሉት ይኼኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከዋናው (በህግ ከሚታወጀው) የበለጠ አደገኛ ነው። ምክንያቱም በምክር ቤት ክትትል እና ምርመራ ስለማይደረግበት የሰብዓዊ መብቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው። አሰራሩ በህገመንግሥቱም ሆነ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። 

አክለውም፣ ለተወሰነ ጊዜ ተጥሎ የነበረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይራዘም ከቀረ እንደተነሳ እንደሚቆጠር እና በዚህ ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ የነበሩ ተግባራትን ማስቀጠል የህግ ጥሰት መሆኑን ነግረውናል። 

የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ በክልሉ አቅም የማይፈታ ከሆነ ህግን ጠብቆ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማራዘም እንደሚቻል አንስተውም፣ ህግን የተከተለ አሰራር ሲኖር ተጠያቂነት እንዲኖር ያስችላል ይላሉ። 

አሁን ላይ ያለው አሰራርም በህገመንግሥቱ ምዕራፍ ሶስት ላይ የተካተቱ መብቶችን በሙሉ እንዲሁም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የሚጥስ ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይጣል የመንቀሳቀስ መብትን መገደብ የመብት ጥሰት ነው። የሰዎች አካላዊ ነጻነት፣ በህይዎት የመኖር፣ ያለፍርድ ቤት የመያዝ መብታቸው ሁሉ ይጥሳል። 

በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቀን ካለቀበት ግንቦት 28 ጀምሮ ሥራውን አቁሟል።

በአማራ ክልል ከቀጠለው የእንቅስቃሴ ገደብ እና መሰል ተግባራት ጋር በተገናኘ ቦርዱ ክትትል እያደረገ እንደሆነ ሃሳብ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው፣ የቦርዱ አባል የነበሩት አብርሃም በርታ (ዶ/ር) ቦርዱን የሚመለከት ማንኛውንም ጉዳይ መናገር እንደማይቻል በመግለጽ ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል።  

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ መደበኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሌለ አስተያየት ለመስጠት እንቸገራለን በማለት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራት እየቀጠሉ ያለው በመሉ ክልሉ ነው ወይስ በተወሰኑ ቦታዎች የሚለውን እና የፈጠሩትን ጫና በተመለከተ ኮሚሽኑ በቀጣይ በሚያወጣው ሪፖርት ሃሳብ ይሰጣል ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ከአማራ ክልል በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የሚገኙ ሰባቱም ወረዳዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት የሚመሩት በኮማንድ ፖስት ነው። በወረዳዎች የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች የምሽት እንቅስቃሴ የተገደበ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ወዘተ የሚሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎች ላለፉት ዓመታት ተጥለዋል።  

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎችም ላለፉት ኹለት ዓመታት ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ ተጥሎባቸዋል። በየአካባቢው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች ባስቀመጡት ክልከላ መሰረት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋት 11 ሰዓት መንቀሳቀስ አይቻልም።  

በሥራ ላይ ያለው ህገመንግሥት አንቀጽ 93 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡ 

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ እንደሚችል ተደንግጓል። [ዋዜማ]