በምስራቅ ጎጃም ትራንስፖርት እንደተቋረጠ ነው፣ በምዕራብ ጎጃም መደበኛ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በአብዛኛው የአማራ ክልል የሚደረግ የመኪና ትራንስፖርት ላይ የዝርፊያ፣ ዕገታና የህገወጥ ኬላ ችግሮች ተባብሰዋል።

ዋዜማ- በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከነሐሴ 07/2016 ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰኞ ነሐሴ 20/2016 ከቀትር በኋላ ድረስ ዝግ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። 

ይህ የሆነው ከነሐሴ 07 እስከ ነሐሴ 17 ድረስ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ጥለውት በነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት ቆመው የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች ወደ መደበኛ ሥራቸው ለመመለስ እያንዳንዳቸው “3 ሺሕ ብር እንድንከፍል ተጠይቀናል” ሲሉ ነግረውናል።

ነዋሪዎቹ፣ ታጣቂዎች ጥለውት በነበረ ክልከላ ቆመው የነበሩ መኪኖች ዕገዳው ከተነሳ በኋላ ለመንቀሳቀስ 3 ሺሕ ብር ክፈሉ መባላቸውን እና ይህን የሰሙት ታጣቂዎች ደግሞ “ለመንግሥት የከፈላችሁትን እጥፍ እናስከፍላችኋለን” ስላሏቸው መቆማቸውን ነግረውናል። 

ይህን ተከትሎ በተለይ በምስራቅ ጎጃም ዞን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ላለፉት 14 ቀናት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደቆመ ነው። 

በዚህም ከነሐሴ 07 ጀምሮ ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ ወደ ወረዳዎችም ይሁን ወደ ክልሉ መዲና ባህር ዳር የሚደረግ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩን ዋዜማ ተገንዝባለች። 

በዞኑ ባሉ ከተሞች ቅጣት አንከፍልም ያሉ መኪኖች ወደ መነሃሪያዎች ገብተው እንዳይጭኑ የታገዱ ሲሆን፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች ግን ባብዛኛው ወደ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል ተብሏል።  

በዞኑ ዋና ከተማ ባለፈው ሳምንት ሱቅ ዘግተው የነበሩ ነጋዴዎችም ተመሳሳይ ቅጣት እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው አሁንም ድረስ ሱቆች እንደተዘጉ ናቸው። 

ስለጉዳዩ የጠየቅነው የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ እንደሌለውና የኮማንድ ፖስቱ አስተያየት ቢስጥበት ይሻላል ብሎናል። የፌደራሉ መከላከያ ቃል አቀባይ ለተደጋጋሚ የስልክ ጥሪያችን ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ግን ወደ ባህር ዳር እንዲሁም ከወረዳ ወደ ወረዳ የሚደረጉ የመኪና ጉዞዎች ታጣቂዎች ጥለውት የነበረውን እገዳ አንስተናል ካሉበት ባለፈው ሳምንት ዐርብ በኋላ ተጀምሯል። 

ባለፈው ሳምንት ከጎንደር ወደ ባህር ዳር ተቋርጦ የነበረው የመኪና እንቅስቃሴ አሁን ላይ የተመለሰ ቢሆንም፣ መንገድ ላይ በሚፈጸም ዝርፊያ እና እገታ ምክንያት ተጓዦቹ ከፍተኛ ስጋት አላቸው ተብሏል። 

ከጎንደር ወደ መተማ እና ወደ ሌሎች የምዕራብ ጎንደር እና የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች በሚደረጉ የመኪና ጉዞዎችም በሚፈጸሙ ዕገታዎች ምክንያት ሹፌሮች እና ተጓዞች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጸም ዋዜማ ሰምታለች።

በተለይ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች በአውሮፕላን ለመጓዝ መገደዳቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። 

በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ግጭት ከሰሞኑም በተለያዩ አካባቢዎች በኹለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደነበር ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች።

ለአብነትም እንደ ቋሪት፣ ቲሊሊ አካባቢ፣ ጎንጅ ቆለላ እና ሌሎችም የጎጃም ቦታዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ውጊያዎች ሲደረጉ ነበር ። [ዋዜማ]