ዋዜማ- የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማኅበር፣ ጠበቆች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ዓመታዊ ግብር ለመክፈል የነጋዴዎች ዓይነት የሒሳብ መዝገብ እንዲኖራቸው እየተጠየቁና እየተጉላሉ ይገኛሉ በማለት አማሯል። 

ማኅበሩ የድሮው የቁርጥ ግብር ክፍያ አሠራር እንዲቀጥልለት ፍትህ ሚንስቴርን ጠይቆና ፍትህ ሚንስቴርም ጥያቄውን ለገንዘብ ሚንስቴር አስተላልፎ የነበረ ቢኾንም፣ ገንዘብ ሚንስቴር ግን የማኅበሩን አቤቱታ ሳይቀበል እንደቀረ ተናግሯል። 

ኾኖም ማኅበሩ ገንዘብ ሚንስቴር አዲሱ የግብር አከፋፈል ሥርዓት ተግባራዊነቱ እንዲቀጥል ለከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ሐምሌ 30 የጻፈውን ደብዳቤ እንዲያሻሽል ሊጠይቅ መኾኑን የማኅበሩ ዋና ጸሃፊ ዘሪሁን ጴጥሮስ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ማኅበሩ ሚንስቴሩን የሚጠይቀው፣ የፍትሕ ሚንስቴር፣ የገንዘብ ሚንስቴርና የከተማዋ ገቢዎች ቢሮ ተወካዮች ባሉበት በጉዳዩ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የተጀመረው አዲስ የጠበቆች የግብር አከፋፈል መመሪያ ዝግጅቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቀድሞው የግብር አከፋፈል ሥርዓት እንዲቀጥሉ እንዲፈቅድ መኾኑን ዋዜማ ሰምታለች።

ለረጅም አመታት የጥብቅና ስራ አገልግሎት እንደ ንግድ ስራ ታክስ የማይከፈልበት የነበረ ቢሆንም ከጥቂት አመታት በፊት ገንዘብ ሚኒስቴር የጥብቅና ስራ ላይ የሚደረጉ ወጪዎችን የሂሳብ መዝገብ በመያዝ ግብር መክፈል እንዳለባቸው መገለጹ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የበጀት ዓመቱን የግብር ግዴታቸውን ለመወጣት የሄዱ ጠበቆች “የተመዘገበ ካፒታል ካላቀረባችሁ አትስተናገዱም” በሚል መጉላላት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ በመግለጽ ቅሬታ በኢትዮጵያ ፌዴራል ጠበቆች ማሕበር ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በኩል አቅርበው ነበር።

ከዚህ ቀደም በተደረሰበት መግባባት መሠረት የጠበቆችን ታክስ አከፋፈል በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ወጥቶ ችግሩ ወጥ በሆነ መልኩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት ሲስተናገዱበት በቆየው ነባር አሰራር የ2016 በጀት ዓመት የግብር ግዴታቸውን እንዲወጡ ትብብር እንዲደረግ ፍትህ ሚኒስቴር የጠየቀ ቢሆንም ገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄውን አልተቀበለም።

አቶ ዘሪሁን  የግብር መክፈያ ወቅት እየተጠናቀቀ በመሆኑ ወደ ቅጣት ክፍያ ከመደረሱ በፊት የገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄያችንን ካልተቀበለ በመንግስት የተገለጸውን አሰራር የመከተል ግዴታ አለብን ብለዋል። [ዋዜማ]