- ፋብሪካዎቹ በተለምዶ የኮቴ በሚል በአንድ መኪና 5ሺ ብር ይከፍሉ የነበረው አሁን 90ሺ ብር ደርሷል
ዋዜማ- የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ መስከረም ዲባባ ተፈርሞ ሰኔ 5 ቀን 2016 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የገቢ ታሪፍ ክፍያ መክፈል ግዴታ መሆኑን ይጠቅሳል።
ዋዜማ የተመለከተችው 32 ገጽ ደንብ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የክልሉ 23 ከተሞችን ስም በመጥቀስ የደንቡን አስፈላጊነት እና የክፍያ ተመን ገልጿል።
በደንቡ መሰረት የለስላሳ መጠጦች በአንድ ሳጥን ከ30 ብር እስከ 50 ብር እንዲሁም የቢራ መጠጦች በአንድ ሳጥን ከ50 ብር እስከ መቶ ብር ድረስ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻል።
ይህንን ደንብ ተከትሎ ምርቶቻቸውን በየክልሉ ለማከፋፈል መቸገራቸውን እየገለጹ ካሉት አንዱ የኮካኮላ ፋብሪካ ሲሆን በተጠቀሰው ደንብ መሰረት የኮቴ በሚል የሚከፈለው ክፍያ ፈተና ሆኖብናል ይላል።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክልሎች ምርቶቻቸውን በሚያጓጓዙበት ወቅት የኮቴ በሚል በአንድ መኪና እስከ 5ሺ ብር ክፍያ ይጠየቁ እንደነበር የሚናገሩት የኮካ ኮላ ፋብሪካ ሰራተኞች በአዲሱ ደንብ ግን በአንድ መኪና 90 ሺ ብር እንዲከፍሉ ተገደዋል።
” በፌደራል ደረጃ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ግብር የሚከፍል ድርጅት ሆኖ በየክልሉ ደግሞ ታሪፍ ክፍያ ከተጨመረ ተደራራቢ ወጪ ይሆናል “ ይላሉ የድርጅቱ ሰራተኞች።
የታሪፍ ክፍያውን ምክንያት በሚጠይቁበት ወቅት ከክልሉ የተሰጣቸው ምላሽ ለሚጠቀሙት መንገድ ተብሎ የሚከፈል መሆኑ ቢጠቀስም በፌደራል ደረጃ የሚከፈለው ግብር በክልል ያለውን የመንገድ መሰረተ ልማት መጠቀም እንደሚቻል ነው የምናውቀው ብለዋል።
የኮካኮላ ፋብሪካ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ፣ ባህርዳር ፣ሰበታ እና ድሬደዋ ፋብሪካዎች ያሉት ቢሆንም የምርት ስርጭቱ በኦሮሚያ ክልልም በስፋት ይከፋፈላል።
” የኮቴ በሚል የሚከፈለውን ክፍያ በመደመር ተጠቃሚው እንዲከፍል ቢደረግ በትንሹ በአንድ የለስላሳ መጠጥ 1 ብር ከ50 ያስጨምራል። ነገር ግን መንግስት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የኤክሳይዝ ታክስ እና የግብአት ዋጋ መናር መሰረት ብቻ ራሱ በእያንዳንዱ የለስላሳ መጠጦች ላይ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ስለሆነ ድጋሚ ዋጋ መጨመር ህበረተሰቡን ማማረር ይሆናል ሲሉ የድርጅቱ ሰራተኞች የገቡበትን አጣብቂኝ ያብራራሉ።
በተመሳሳይ የሐይኒከን ኢትዮጵያ የኮርፖሬት ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ መቅደስ ኃይለ ማርያም “የቢራ ፋብሪካዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በግለሰቦች እንዲንቀሳቀሱ ከተፈቀደ በፈረንጆች 2011 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን ሲያልፍ መቆየቱን ተናግረዋል። ከጅምሩ የነበረ እና አሁንም የቀጠለው ዋነኛው ችግር የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲሆን የቢራ ማስታወቂያ መከልከሉ ደግሞ ሌላኛው ፈተና ነበር” ብለዋል።
ያለፉት አመታትን ችግሮች እንዳሉ ሆነው በቅርቡ ይፋ የተደረገው የኤክሳይዝ ታክስ ደግሞ ለኢንዱስትሪው ፈተና ሆኗል ብለዋል። [ዋዜማ]