ዋዜማ-የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር በትናንትናው ዕለት በመጀመሪያ ዙር ቁጥራቸው ከ14 ሺሕ የሚበልጡ ተፈናቃዮችን ወደ አላማጣ ከተማ መመለሱንና እና በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ተጨማሪ አምስት ሺሕ ገደማ ሰዎችን ከተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ወደ አካባቢው “እንደሚመልስ” በጊዜያዊ አስተዳደሩ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ተደርገው የተመደቡት ዝናቡ ደስታ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ከንቲባው፣ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን በማይጨው ከተማ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ከ270 በላይ አባዎራዎች እንዲሁም በማግስቱ አርብ እና ቅዳሜ ደግሞ መቀሌ የሚኖሩ 2 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ወደ አላማጣ ለማምጣት ዕቅድ መውጣቱን ገልጸዋል።
ወሳኝ የተባለው የመጀመሪያ ዙር ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ትናንት መከናወኑን የጠቀሱት ከንቲባው፣ የተመለሱት ከ14 ሺሕ በላይ ሰዎች በመሆኒ እና ኩኩስቶ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ከ1 ዓመት ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠሩ ተፈናቃዮች እንደነበሩ ተናግረዋል።
ተፈናቃዮችን በሦስት ዙር የመመለሱ ሥራ እየተከናወነ ያለውም በአካባቢው ካሉ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች ጋር በመናበብ ነው ብለዋል።
በመከላከያ እና በፌደራል ፖሊስ ፈቃድ ትናንት ከተመለሱት ከ14 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች አብዛኞቹ አላማጣ ከተማ ሲገቡ የተወሰኑት ወደ ዋጃ እና ጥሙጋ መሄዳቸውን ከንቲባው ተናግረዋል።
ተመላሾቹ በአካባቢው ቀድሞ ቤት እና ንብረት የነበራቸው እንደሆኑ ገልጸው፣ መኖሪያ ቤታቸው በሌሎች አካላት መኖሪያ ሆኖ የጠበቃቸው ተፈናቃዮች በመኖራቸው በቀጣይ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የማስመለስ ሥራ ይጀመራል።
ተፈናቃዮችን መመለስ ተከትሎ ከየትኛውም ወገን የሚቀርብ ቅሬታ ተቀባይነት እንደሌለው በማንሳትም፣ የአማራ ክልል መንግሥት ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ሊፈቅድም ሆነ ሊከለክል አይችልም ብለዋል።
ከንቲባው እንደሚሉት፣ ተፈናቃዮች እየተመለሱ ያሉት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና በፌደራል መንግሥቱ ንግግር መሰረት በመሆኑ፣ የስምምነቱ አካል ያልነበረው የአማራ ክልል መንግሥት ይህ ጉዳያ አይመለከተውም።
ከ19 ሺሕ በላይ ተፈንቃዮች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ፣ ኑሮ እንዲመሰርቱ የማቋቋም ሥራዎች እንደሚቀጥሉ ነግረውናል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ቅድሚያ ሰጥቶ ወደ ቀድሞ ቀያቸው እየመለሰ ያለው በመጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ተፈናቃዮችን ሲሆን፣ ወደ መኖሪያቸው መመለስ የሚገባቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችም አሉ።
አካባቢው አሁንም በኮማንድ ፖስቱ እንደሚተዳደር የገለጹት ዝናቡ፣ እኛ የኮማንድ ፖስቱ አንድ አካል ሆነን በመተጋገዝ እየሰራን ነው ብለዋል።
ከጦርነቱ በኋላ አካባቢውን ሲያስተዳደር በነበረው በአማራ ክልል መንግሥት ተሹመው የነበሩት የቀድሞ የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ኃይሉ አበራ፣ ግን ዛሬ ወደ አላማጣ እንዲገቡ የተደረጉት ሰዎች በተፈናቃይ ስም <ወራሪ ኃይሎች> ናቸው ሲሉ ለዋዜማ ገልጸዋል።
ኃይሉ፣ ድርጊቱ ቀይ መስመር ያለፈ ነው፣ ተፈናቃዮች ከሰባት ወር በፊት ተመልሰዋል አሁን እየገቡ ያሉት ታጣቂ እና ወራሪ ኃይል ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል።
ጉዳዩን እየተፈጸመ ያለው ያለአማራ ክልል እውቅና እና ፈቃድ ነው ያሉት ኃይሉ፣ የአማራ ክልል የሚወስደውን እርምጃ እንጠብቃለን ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት ጉዳዩን አልሰማም ማለት አይቻልም እኛም ለሚመለከተው አካል አሳውቀናል፣ የክልሉ መንግሥት ቢያንስ መግለጫ ያወጣል ብለን እንጠብቃለን ነው ያሉት።
ኃይሉ፣ እየተደረገ ያለው ነገር በማህበረሰቡ ዘንድ ሌላ ግጭት ለመፍጠር ነው ሲሉ ኮንነው፣ በቦታው ያሉ የመከላከያ አመራሮችን ተጠያቂ አድርገዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌትናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ሐምሌ 06 ቀን 2016 ዓ.ም ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ያልተሳካበት ዋነኛ ምክንያት “በእኛ በትግራይ በኩል ሳይሆን፣ በአማራ ክልል በኩል የተደረገው ዝግጅት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብለው ነበር።
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል መንግሥትን ምላሽ ለማካተት ለክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ብትደውልም ስልካቸው ባለመስራቱ ሳይሳካ ቀርቷል። [ዋዜማ]