Photo-FILE

ዋዜማ- የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ አማፅያን ጋር ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት የሱዳን ወታደሮች ድንበር ተሻግረው የኣኢትዮጵያ ይዞታ የነበሩ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸው ይታወቃል። ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ ዋዜማ የድንበሩ አካባቢ ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ሞክራለች። 

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚወዘጋቡበት አካባቢ፣ የአልፋሽጋ ሦስትዮሽ ተብሎ የሚጠራው ሰፊ ለም መሬት ሲሆን፣ ይህ መሬት ምስራቃዊ ሱዳን ገዳሪፍ ግዛትን እና በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ምዕራብ አማራ ክልልን ያዋስናል።

የሱዳን ወታደሮች፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ ቋራ እና መተማ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ነግረውናል። አንዳንዶቹ አካባቢዎች በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን የተያዙ ናቸው ያሉት ነዋሪዎቹ፣ አንዳንዶች ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስ ጀምሮ የተያዙ መሆኑናቸው ገልጸዋል። 

በአካባቢው በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ አንድ አርሶ አደር እንደነገሩን፣ በቋራ ወረዳ ነፍስ ገበያ እና ዝንጀሮ ገደል የሚባሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ የግጦሽ ቦታዎች እንዲሁም የዱር እንስሳት መጠለያዎች ዛሬም በሱዳን ወታደሮች ቁጥጥር ስር ናቸው። 

በእነዚህ ቦታዎች ላይ ያሉት የሱዳን ወታደሮች፣ ከቋራ ወረዳ ወደ ሱዳን የሚያደርሳቸውን ድልድይ ሽንፋ ወንዝ ላይ መስራታቸውን የገለጹት አርሶ አደሩ፣ ከዚያ ቀደም የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር መለያ ወንዙ እንደነበር ይናገራሉ። የሱዳን ወታደሮችን ከቦታው ለማስለቀቅ “የአካባቢው ሚሊሻዎች እና ነዋሪዎች በቂ ነበሩ” የሚሉት አርሶ አደሩ፣ ሆኖም ትንኮሳ የሚፈጽም አካል ካለ ወድያውኑ በአካባቢው ባሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እንደሚያዝ ገልጸዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር በበኩላቸው፣ የሰሜኑ ጦርነት በተለይ በመተማ እና በቋራ ያሉ ቦታዎችን ሱዳናውያኑ ወታደሮች እንዲቆጣጠሯቸው ዕድል ሰጥቷቸዋል ይላሉ። ይህን ተከትሎ በቋራ ወረዳ እንዲሁም በመተማ ወረዳ ጀበር ስኳር የሚባል ቦታን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ድረስ ወታደሮቹ መኖራቸውን ገልጸው፣ ኢትዮጵያውያን በሱዳኖች ወደተያዙት ቦታዎች እንዲቀርቡ እንደማይፈቀድላቸው ተናግረዋል። 

“በአካባቢው ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው እንድንጠጋ አይፈቅድልንም” ሲሉም ክልከላውን ለዋዜማ ነግረዋታል። በቦታው ካሉ የሱዳን ወታደሮች በቅርብ ርቀት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መኖሩን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ የኹለቱም አገር ወታደሮች ከአንድ የውሃ ጉድጓድ ሲጠቀሙ ማስተዋላቸውን ነገረውናል።  

በቋራ ወረዳ ያለው ለም የእርሻ ቦታ፣ በሱዳን ወታደሮች ከመያዙ በፊት በእርሻ ሥራ ለሚሰማሩ 60 ለሚጠጉ የአካባቢው ተወላጆች እና በውጭ ለሚኖሩ ባለሃብቶች ተሰጥቶ እንደነበርም ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል። ሆኖም እስካሁን ድረስ በየትኛውም ወገን በኩል የእርሻ መሬቶቹ ሰብል እየለማባቸው አይደለም ብለውናል። አካባቢው ከፍተኛ ሰብል የሚሰበሰብበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በዋናነት ሰሊጥ፣ ጥጥ እና አኩሪ አተር የሱዳን ወታደሮች መሬቱን ከመያዛቸው በፊት ሲለማበት እንደነበር አስታውሰዋል። 

እነዚሁ አርሶ አደሮቹ እንደሚሉት፣ የሱዳን ወታደሮች አካባቢውን መቆጣጠራቸው በተለይ ዘንድሮ አንድ መልካም ዕድል ይዞላቸው መጥቷል። የሰሊጥ ምርት ተሰብስቦ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አካባቢውን የተቆጣጠሩት የሱዳን ወታደሮች የአካባቢው ገበሬዎች ሰሊጥን ከዚህ በፊት ሸጠውበት በማያውቁት ዋጋ እየገዟቸው ነው። 

“ዘንድሮ የእነሱ መኖር ነው ገበሬውን የታደገው” ያሉን አንድ አርሶ አደር፣ “አንድ ኪሎ ሰሊጥ ከ120 ብር በላይ ሸጠን የማናውቀውን፣ ዘንድሮ በ150 ብር እየገዙን ነው” ብለውናል። 

የሱዳን ወታደሮች፣ በአካባቢው ባቋቋሙት አንድ የግብይት ማዕከል አማካኝነት ሰሊጥን ጨምሮ ሌሎችንም የግብርና ምርቶች ከኢትዮጵያ ገበሬዎች በመግዛት በጭነት መኪኖች ወደ ሱዳን እያሻገሩ ነው ሲሉም ገልጸዋል። አርሶ አደሩ እንደሚሉት፣ ከዚህ በፊት የግብርና ምርቶችን በገሃድ ለሱዳን መሸጥ የተፈቀደ አልነበረም። 

የሰሜኑ ጦርነት የተጀመረ ሰሞን፣ የሱዳን ወታደሮች የአርሶ አደሮቹን ካምፕ ሲያቃጥሉ እንዲሁም ሰሊጥ እንዳይታጨድ ሲከለክሉና ንብረት ሲዘርፉ እንደነበር የጠቀሱልን አርሶ አደሮቹ፣ አሁን ላይ ይህ ድርጊታቸው መቆሙን ተናግረዋል። 

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ  የምዕራብ ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊ፣ የሱዳን ወታደሮች በዞኑ አሁንም ድረስ የያዙት ቦታ መኖሩን አረጋግጠው፣ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ከዚህ ባለፈም፣ ከቋራ እና መተማ ወረዳዎች እንዲሁም ከምዕራብ ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ዋዜማ ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም፣ ኃላፊዎቹ በጉዳዩ ላይ መልስ መስጠት ያለበት የፌደራል መንግሥቱ ነው በማለት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀዋል። 

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ፣ ‘ኢትዮጵያ እና ጎረቤቶቿ’ በሚል ርዕስ በቅርቡ መጽሐፋቸውን ያሳተሙት በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ የኹለቱ አገራት የድንበር ውዝግብ ከ100 ዓመት በላይ መሆኑን ለዋዜማ ገልጸዋል። ውዝግቡ እስካሁን ያልተፈታውም በኹለቱ አገራት ችግሮች እንዲሁም በአንዳንድ ውጫዊ ጫናዎች ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል። 

“በየጊዜው የነበሩ መንግሥታት ችግሩን ለመፍታት ቢሞክሩም፣ እነዚህን አዙሪቶች ማለፍ አልተቻለም” ያሉት በለጠ፣  “አሁንም ለመፍታት እየተሞከረ ነው” ብለዋል። 

አክለውም ኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በጉዌን የተደረገውን የቅኝ ግዛት ዘመን ማካለል በመርህ ደረጃ መቀበሏ፣ ሱዳኖች የሚጠይቋቸውን አንዳንድ ቦታዎች ለመስጠት ተስማምታለች ማለት ቢሆንም፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር ግን ብዙ ውስብስብ ነገሮች አሉ ሲሉ፣ ሁኔታው ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ያወሳሉ። 

የኹለቱ አገራት የድንበር ማካለል በአግባቡ ባልተከናወነበት ሁኔታ፣ “ሱዳኖች የኢትዮጵያን መሬት ይዘዋል የሚለው በአግባቡ መፈተሽ አለበት” ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል። 

ችግሩ የሚፈታው የኹለቱም አገሮች መንግሥታት የተረጋጋ ፖለቲካ ከመሰረቱ በኋላ፣ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መሆኑን የሚጠቅሱት በለጠ፣ በኃይልም ሆነ በሦስተኛ ወገን አጋዥነት የሚፈታ አይደልም ባይ ናቸው። 

የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታል አልቡርሃን በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተነሳበት ወቅት፣ 6 ሺሕ የሱዳን ወታደሮችን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማስጠጋታቸው፣ በወቅቱ ሲገብ ሰንብቷል። ወደ ድንበር የመጡት የሱዳን ወታደሮችም አልፋሽጋ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆዩ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን በማባረር አካባቢውን እንደተቆጣጠሩ በሱዳን መንግስት ጭምር ተነግሮ ነበር። 

ኅዳር 2013 ዓ.ም. ላይ፣ ድንበር አካባቢ ባሉት በኹለቱ አገራት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ በጅቡቲ የኢጋድ ስብሰባ ላይ የተገናኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና የወቅቱ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላህ ሃምዶክ ጉዳዩን ለማርገብ ውይይት እስከማድረግ ቢደርሱም መፍትሄ ሳያበጁ ተለያይተዋል። 

የካቲት 2013 ዓ.ም. ላይም፣ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢትዮጵያ በሱዳን ሉዓላዊ ግዛት ላይ ወታደር ማስፈሯን እና ድርጊቱም ጸብ አጫሪነት መሆኑን በመግለፅ የውግዘት መግለጫ አውጥቶ ነበር። 

ከሱዳን መግለጫ 7 ቀናት በኋላ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ድንበር መጣሷን ገልጾ፣ ይህም በሰሜኑ ጦርነት እጁን ማስገባት የሚፈልግ ሦስተኛ አካል መኖሩን ያመለክታል ሲል ድርጊቱን በአደባባይ ኮንኖት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም፣ የሕዝብ እንደራሴዎችን ጨምሮ በሌሎች መድረኮችም ላይ፣ ‘አስቀድማ ሱዳን ሰላም ትሁንና ከሱዳን ወንድም ሕዝብ ጋር ጉዳዩን በውይይት እንፈታዋለን’ ሲሉ ተደምጠውም ነበር። 

ከዚያ ጊዜ ወዲህም፣ ብዙዎች ሱዳን የኢትዮጵያን ግዛት በኃይል በመቆጣጠር የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንደጣሳች ቢገልፁም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንፈታዋለን” ከሚል ንግግር ውጪ፣ በዝምታው ቀጥሏል። [ዋዜማ]